Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​በጋምቤላ ክልል የእርሻ መሬታችንን ተነጠቅን ያሉ ኢንቨስተሮች አቤቱታ አቀረቡ

​በጋምቤላ ክልል የእርሻ መሬታችንን ተነጠቅን ያሉ ኢንቨስተሮች አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

በጋምቤላ ክልል የሚያለሙት የእርሻ መሬት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ለመገንባት ላቀደው የኢኮኖሚ ዞን እንዲለቁ የተወሰነባቸው ኢንቨስተሮች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

የክልሎችን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በውክልና ተረክቦ እንዲያስተዳድር የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን የሰጠው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ በአገሪቱ የተለያዩ አግሮ ኢኮሎጂ አካባቢዎች የግብርና ኢኮኖሚ ዞን የማቋቋም ዕቅድ አለው፡፡

ሚኒስቴሩ በሚያቋቁመው ኢኮኖሚ ዞን ሰፋፊ ሜካናይዝድ እርሻዎችን ለሚያካሂዱ ግዙፍ ኢንቨስተሮች መሬት በሊዝ የማከፋፈል ዕቅድ ይዟል፡፡ የኢኮኖሚ ዞኑ የመስኖ ግድቦች፣ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አውታሮች ተሟልተውለት ለኢንቨስተሮች የሚቀርብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዚህ መነሻ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ አኩላ ቀበሌና ጎግ ወረዳዎች ውስጥ ከአኩላ ወንዝ እስከ ኪሎ ወንዝ ድረስ የሚገኝ 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የማልማት ዕቅድ ተይዟል፡፡

ነገር ግን ይህ ዕቅድ ተግባራዊ በሚሆንበት መሬት ላይ ቀደም ብለው የእርሻ ሥራ ውስጥ የገቡ ወደ መቶ የሚጠጉ ኢንቨስተሮች እንዲነሱ ተወስኗል፡፡

በተለይ በአኩላ ቀበሌ የሚፈናቀሉ 31 ኢንቨስተሮች በተወካዮቻቸው አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት አቤቱታ፣ አሠራሩ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

‹‹ከ31 በላይ የምንሆን ባለሀብቶች የመንግሥት ፖሊሲና ጥሪ በመቀበል በጋምቤላ ክልል በአኙዋ ዞን በዲማ ወረዳ አኩላ ቀበሌ፣ የክልሉን የኢንቨስትመንት መሥፈርቶች አሟልተን በዲማ ወረዳ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሦስት ወራት የፈጀ ጥናት አድርጎ፣ ቦታዎቹ ከማንኛውም ይዞታ ነፃ የሆኑና በክልል ደረጃ ሊለሙ የሚችሉ መሆኑን አረጋግጦ፣ ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. መሬቱን አስረክቦናል፤›› በማለት የኢንቨስተሮቹ አቤቱታ ይገልጻል፡፡ ‹‹በዚህ መሠረት ክልሉ ጋር ለ50 ዓመታት የሚቆይ ሕጋዊ ውል በማሰር የመሬት ግብር አስቀድመን በመክፈል በፍትሕ ቢሮ በማፀደቅ ሕጋዊ ካርታ በመውሰድ ወደ ሥራ ገብተናል፤›› በማለት የሚተነትነው የቅሬታ አቅራቢዎች ደብዳቤ 65 ኪሎ ሜትር መንገድ በመጥረግ፣ የአኩላ ወንዝ ላይ 20 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ በመገንባትና ካምፕ በመቆርቆር የእርሻ መሬት ዝግጅት መከናወኑን ይገልጻል፡፡

ለእነዚህ ሥራዎች በርካታ ሚሊዮን ብሮች ማውጣታቸውን ኢንቨስተሮቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገቡት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

ነገር ግን የዲማ ወረዳ አስተዳደር በጻፈላቸው ደብዳቤ የተሰጣቸው መሬት የፌዴራል ኢኮኖሚ ዞን ክልል በመሆኑ፣ ከተሰጣቸው መሬት ላይ እንዲነሱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ለተነሽዎቹ ተለዋጭ ቦታ እንደሚሰጣቸው ወረዳው የጻፈው ደብዳቤ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ለጎግ ወረዳ ኢንቨስተሮችም ተመሳሳይ ደብዳቤ ባለፈው የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. መጻፉ ተገልጿል፡፡ የ31 ተፈናቃዮች ተወካይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጀንበሩና አቶ ኪሮስ በርሔ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በእርሻ መሬታቸው ላይ በርካታ ገንዘብ አውጥተዋል፡፡ መንግሥትን አምነው ያፈሰሱት ሀብት መና ሊቀር እንደማይገባ፣ በኢኮኖሚ ዞኑ ሊመረት የሚችለውን ምርት ማምረት የሚችሉ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን በአንክሮ እንዲመለከተው ጠይቀዋል፡፡

‹‹ለ50 ዓመታት በሕግ የያዝነውን መሬት በወረዳ አስተዳደር ደብዳቤ እንድንለቅ መደረጉ ፈጽሞ ሕገወጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ሕግና የፍትሐ ብሔር ሕጎች ያላገናዘበ፣ ከክልሉ ጋር ከተዋዋልነው ውል ጋር ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ፣ የሞራል ክስረትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ከፍተኛ ግፍ ነው፤›› በማለት ባለሀብቶቹ ባቀረቡት የቅሬታ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍትሕ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን ባለሀብቶቹ ለልማት እያዘጋጁት ያለው መሬት ቀደም ሲል በፌዴራል መንግሥት ለኢኮኖሚ ዞን የተከለለ ሆኖ ሳለ፣ በስህተት የክልሉ መንግሥት እንደሰጣቸው የፌዴራል መንግሥት ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ስህተት ምክንያት ችግሩ ተፈጥሯል፡፡ ያለው አማራጭ በሚሰጣቸው ተለዋጭ ቦታ ላይ ሥራቸውን መቀጠል ነው ተብሏል፡፡ ባለሀብቶቹ ግን ካፒታላቸውን ያፈሰሱበትን መሬት ካጡ በኋላ፣ እንዴት ሆነው ዳግም ወደ አዲስ ሥራ መመለስ እንደሚችሉ ግራ እንደገባቸው አስረድተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...