Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎች የሰብል ኢንሹራንስ ከለላ ሊያገኙ ነው

  ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎች የሰብል ኢንሹራንስ ከለላ ሊያገኙ ነው

  ቀን:

  ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥነት ያላቸውንና ወቅትን ጠብቀው የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችል የሰብል ኢንሹራንስ፣ ለባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎችን ሊሰጥ ነው፡፡

  የሰብል ኢንሹራንሱ የሰብሉን ክሎሮፊል ወይም አረንጓዴነት መጠን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  በብሔራዊ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰብል የሚበቅልባቸውን አካባቢዎች ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ በሳተላይት በሚያገኘው የአረንጓዴነት መረጃ ኢንሹራንሱ የተወሰነ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ እንደሚሉት፣ ሳተላይቱ አረንጓዴ ቦታዎችን በመመዝገብ በየአሥር ቀናት በ11 የቅርንጫፍ ዳይሬክቶሬቱ ሳተላይት መቀበያ አማካይነት ምዝገባ ያደርጋል፡፡ ይህ የሰብል ኢንሹራንስ ግብዓቶችን መሠረት ያደረገ እንደሆነ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድወሰን ኢተፋ ይገልጻሉ፡፡

  አርሶ አደሮቹ የሚጠቀሟቸውን ግብዓቶች እንደ ማዳበሪያ፣ ዘር፣ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ግብዓቶች ከአጠቃላይ ዋጋ ወደ አሥር በመቶ የሚሆነውን የሥጋት ፕሪሚየም (ዓረቦን) ክፍያ መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡

  የክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ የማይክሮ ኢንሹራንስ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ መገርሳ ምሬሳ እንደሚሉ፣ የክፍያው አፈጻጸም በተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አማካይነት የሚከናወን ይሆናል፡፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የግብዓት ምርቶቹን በብድር የሚያገኙበትን መንገድ ያዘጋጀ ሲሆን አርሶ አደሮቹ የግብዓት ምርቶቹ ከዚህ ኤጀንሲ በሚወስዱበት ጊዜ የመድን ሽፋኑንም በጭማሪ ይወስዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ያሉትን መረጃዎች ሲያስተላልፍ፣ አርሶ አደሮቹ የመድን ሽፋኑን ጠየቁም አልጠየቁ በሳተላይት መረጃው መሠረት ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡

  በዚህ ዓመት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 200 ሺሕ ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎችን፣ ይኼ የማይክሮ ክሬዲት ኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የክፍያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙኒር ዱሪ ገልጸዋል፡፡

  የሰብል ኢንሹራንሱ እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመጣመር ቢጀመርም ሊሳካ እንዳልቻለ አቶ ዱሪ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የነበረው በ1977 ዓ.ም. የነበረውን የሰብል ሁኔታ እንደ ዋና ነጥብ መወሰዱ መሆኑን አቶ ዱሪ አክለዋል፡፡

  ይኼንንም ሁኔታ ለማስተካከል በኔዘርላንድ ትዌንቲ ዩኒቨርሲቲ 60 አካባቢዎች ተመርጠው ለ16 ዓመታት ያለው ሁኔታ ተጠንቷል፡፡ በዚህም ጥናት ከ800 ሺሕ በላይ የተለያዩ ናሙናዎችን ተወስደዋል፡፡ ይኼም ጥናት የሰብሎቹን የአረንጓዴነት ሁኔታ ለመወሰን ግብዓት ላይ ውሏል፡፡

  አንድ የአገሪቱ ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬ በአንድ የሰብል ወቅት በአማካይ ከ2,500 እስከ 3,000 ብር ለግብዓት ወጪ እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ ወንድወሰን፣ ሰብሉ የወደመ እንደሆነ የተጠቀማቸው ግብዓቶች መቶ በመቶ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለአርሶ አደሩ እንደሚከፈል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይኼ የገበሬውን ችግር ሙሉ በሙሉ ያቃልላል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከግብዓት ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ቢያንስ ይከፈላቸው ለማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ 15 ሚሊዮን ባለአነስተኛ ይዞታ ገበሬዎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ጊዜያት ምርት ላይ ያተኮረ የመድን ሽፋን እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ ይኼ የሰብል ኢንሹራንስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን አሳትፏል፡፡ እነዚህም የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂስ፣ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲና የኔዘርላንድ ትዌንቲ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img