የዓድዋ ድልና ታሪካዊ ውርሱን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይበረዝ ለማሸጋገር እንዲቻል፣ በመጻሕፍትና በኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማስተላለፍ መንግሥት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ዓድዋ ላይ ድል የተቀዳጀበት 120ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ፣ የዓድዋ ድል አንድ ወጥ ኅብረተሰብ ለመፍጠርና በቅኝ ግዛት ለተያዙ የአፍሪካ አገሮች መነቃቃትን የፈጠረ በመሆኑ ድሉንና ታሪኩን በመጻሕፍትና በኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማስተላለፍ፣ እንዲሁም ድሉን የአፍሪካ ድል አድርጎ ለመዘከር የሚደረገውን ጥረት መንግሥት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው 120ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓል የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹ብዝኃነትን ያከበረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ የዓድዋ ድልን ሕያው ማድረግ ትችላለች!!›› በሚል መሪ ቃል በመላው አገሪቱ እንደሚከበር በዋዜማው መግለጫ ያወጣው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ ድሉ የመላ ኢትዮጵያውያን አንዱ የማንነት መገለጫና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል ብሏል፡፡
መግለጫው አያይዞም የዓድዋ ጦርነትና የኢትዮጵያውያን ድል ወራሪዎችን ያሳፈረ፣ በበርካታ ታዋቂ የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ጭምር ብዙ የተባለለት፣ በሌላም በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ መላ ጥቁር ሕዝቦችን ለነፃነት ተጋድሎ ያነሳሳ በመሆኑ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው ብሎታል።
እንዲሁም በዓድዋ የታየው ለቅኝ ገዥዎችና ወራሪዎች የአልምበረከክም ባይነት የትግል ወኔና ቁርጠኝነት፣ ዛሬም ድህነትን በመዋጋት የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ የሚፋጠንበትና ስኬት የሚመዘግብበት ሊሆን ይገባል ሲል አክሏል።
ኢትዮጵያ በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት ወራሪውን የኢጣሊያ ሠራዊት ዓድዋ ላይ ድል ያደረገችው የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. እንደነበረ ይታወሳል፡፡