Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አረፉ

​ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አረፉ

ቀን:

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አረፉ፡፡

አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከ30 ዓመታት በላይ በሊቀ ጳጳስነት ባገለገሉበት አርሲ ሀገረ ስብከት ያረፉት የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡

በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አማካይነት ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. በኤጲስ ቆጰስነት (ጳጳስነት) የተሾሙት አቡነ ናትናኤል፣ በመጀመርያ የትግራይ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ከመጰጰሳቸው በፊት አባ መዓዛ ቅዱሳን ገብረ ሕይወት በመባል ይታወቁ የነበሩት አቡነ ናትናኤል፣ በጎንደርና በስሜን እንዲሁም በአዲስ አበባ በጥንታዊው የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ጸዋትወ ዜማ፣ ቅኔ፣ መጻሕፍተ ብሉያት፣ ባሕረ ሐሳብ (አቡሻህር) ፍትሐ ነገሥት የተማሩ ሲሆን፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመረቁና በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ካገለገሉ በኋላ በ1955 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ኢየሩሳሌም በመሄድ በቲዎሎጂ ተመርቀዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከኢየሩሳሌም እንደተመለሱ ከ1957 እስከ 1960 ዓ.ም. ድረስ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪና በሐዋርያዊ ድርጅት የብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለብዙ ጊዜ አስተምረዋል፡፡ በ1961 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ አገር ሄደው በፍልስፍና ትምህርትና በሳይኮሎጂ በባችለር ዲግሪ (Bachelor of Divinity Basic Philosophy Super mental and Developmental Psychology) ተመርቀዋል፡፡

ከ1964 እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ቀደም ሲል በምክትልነት በኋላም በዋና አስተዳዳሪነት ሊቀ ሥልጣናት ተብለው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰፊ አገልግሎት ያበረከቱት አባ መዓዛ ቅዱሳን፣ ከ1968 እስከ 1971 ዓ.ም. በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መርሐ ልሳን በሚባለው ክፍል ተመድበው መሥራታቸው ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቅሱት ተግባራዊ አልሆነም እንጂ በታኅሳስ 1966 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆነው እንዲያገለግሉ በጽሕፈት ሚኒስቴር ተሹመው ነበር፡፡  

አባ መዓዛ ቅዱሳን የምንኩስና ማዕረግ የተቀበሉት በ1953 ዓ.ም. ነሐሴ 7 ቀን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲሆን፣ ከማዕረግ ቅስና እስከ ማዕረግ ምንኩስናና ቁምስና ድረስ ያለውን ማዕረግ የተቀበሉት ከመጀመርያው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ነበር፡፡

በቀድሞ አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት ክልተ አውላሎ አውራጃ ዐውዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀበሌ ከአባታቸው ከአቶ ገብረ ሕይወት ጻዕዱና ከእናታቸው ከወይዘሮ ወለተክርስቶስ ግብረቱ በ1923 ዓ.ም. ግንቦት 12 ቀን የተወለዱትና በ85 ዓመታቸው ያረፉት አባ መዓዛ ቅዱሳን (አቡነ ናትናኤል) ሥርዓተ ቀብር፣ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ባገለገሉበት ሀገረ ስብከትና ራሳቸው ባሳነፁት ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም እንደሚፈጸም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ሦስተኛ ዓመት በዓለ ሲመት የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚከበር፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በሚከበረው በዓለ ሲመት ከካህናትና ምዕመናን በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮችና የልዩ ልዩ ተቋማት ተወካዮች እንደሚገኙ መግለጫው አውስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...