Tuesday, January 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

​ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ሲዘከር የአገሪቱ አንድነትና ህልውናም ይታሰብበት!

ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ከ120 ዓመታት በኋላም የሚዘከረው፣ የዚህችን አገር ታላቅነት ከሚያደምቁ አንፀባራቂ ታሪኮች መካከል አንዱ ስለሆነ በኩራትና በታላቅ ሐሴት ነው፡፡ የዓድዋ ድል አንዲት አፍሪካዊት አገር በዘመኑ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የአውሮፓ ኮሎኒያሊስት በማንበርከክ፣ ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትንሳዔ ያበሰረችበት ነው፡፡ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ሕይወታቸውን የሰውበት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱበትና ደማቸውን ያፈሰሱበት ታላቁ የዓድዋ ድል፣ የታላቋ አገር ኢትዮጵያና የጀግናው ሕዝቧ የታሪክ አሻራ ነው፡፡ ይህንን በዘመኑ አቻና ወደር ያልተገኘለት አንፀባራቂ ድል እያሰብን፣ የእዚህን ዘመን የአገራችንን ጉዳይ እንቃኛለን፡፡

የዓድዋ ድል በአፄ ምኒሊክ መሪነት፣ በባለቤታቸው በእቴጌ ጣይቱ ዋና አስተባባሪነት፣ በየደረጃው ባሉ የዘመኑ አመራሮች አጋፋሪነትና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነት ተጋድሎ፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የተበረከተ የነፃነት ስጦታ ነው፡፡ ግማሽ ቀን ባልሞላው የዓውደ ግንባር ፍልሚያ አምስት ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት ተሰውተው፣ ስምንት ሺሕ ያህሉ ደግሞ የአካል መስዋዕትነት የከፈሉበት ነው፡፡ እናት አገርን በዘመኑ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ላለማስደፈር የተከፈለው ይህ ዓይነቱ አንፀባራቂ መስዋዕትነት፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጸሐፍት ትልቅ ሽፋን ያገኘ ነው፡፡ በዓድዋ ጦርነት ድሉ የኢትዮጵያዊያን መሆኑ ተረጋግጦ ሰባት ሺሕ የኢጣሊያ ወታደሮች ከሁለት ጄኔራሎቻቸው ጋር መሞታቸው፣ 1,500 ያህሉ ቆስለው ሦስት ሺሕ የሚሆኑት እጃቸውን መስጠታቸው፣ ለዘመቻው የተሠለፉት ሁሉም መድፎችና 11 ሺሕ ጠመንጃዎች መማረካቸው ሲታወቅ፣ በወቅቱ ታዋቂ በነበሩት የአሜሪካና የአውሮፓ ጋዜጦች የመጀመሪያ ገጽ ሰበር ዜና ሆነው ነበር፡፡ ኮሎኒያሊስቶች አንገታቸውን ሲደፉ፣ በቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ ግን በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገዋል፡፡

ይህንን ዓይነት ስመ ገናና ገድል የተፈጸመባት አገር ሕዝቧ መቼም ቢሆን እንዳትደፈር ሕይወቱን ሲገብርላት ኖሯል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድም ጊዜ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር አላረፈባትም፡፡ ይህ ለአገሩ ቀናዒ የሆነ ጀግና ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር እየተመመ እግሩን ለጠጠር፣ ግንባሩን ለጦር ያጋፍጥ የነበረው ደልቶትና ተመችቶት አልነበረም፡፡ በተለይ በዘመነ መሣፍንት አገዛዝ ወቅት በተደረጉ የእርስ በርስ ውጊያዎችና የግዛት ማስፋፋት ዘመቻዎች ከሚገብረው ሕይወቱ በተጨማሪ፣ የፊውዳሎች ሎሌና በገዛ አገሩ መሬት አልባ ገባር ሆኖ መከራውን በልቷል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የነበረው ሰቆቃ የኢትዮጵያዊያን የጋራ መገለጫ ነበር፡፡ ይህ መከራ በሁሉም ወገኖቻችን ላይ የደረሰ በመሆኑ በተናጠል የእነ እንትና ብቻ የሚባል አልነበረም፡፡ ነገር ግን ምን ግፉ ቢበረታ፣ ምን በደሉ ቢያስመርር፣ ምን መከራው ቢያንገፈግፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ አይደራደርም ነበር፡፡ ይህ ታላቅ የአገር ፍቅር ስሜት በዓለም ላይ ህያው ሆኖ የሚኖር ታላቅና አንፀባራቂ ድል እንዲጎናፀፍ አድርጎታል፡፡

በዓድዋ ድል ምክንያት የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሦስቱን ኅብረ ቀለማት (አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ)፣ ከአፍሪካ እስከ ላቲን አሜሪካ ድረስ በርካታ አገሮች ተጋርተዋል፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መፈጠርና ለፀረ ኮሎኒያሊስት ትግል ዘመቻዎች የልብ ልብ የሰጠው ታላቁ የዓድዋ ድል ነው፡፡ ለአሜሪካ ጥቁሮች የነፃነት ጥያቄ መነሻ ነው፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት ዋነኛው ፋና ወጊ ነው፡፡ በዚህ ድል ምክንያት ኢትዮጵያ ያገኘችው ከፍታ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ይህንን አንፀባራቂና ተምሳሌታዊ ድል በታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ስኬት ማስቀጠል ሲገባን ግን፣ ራሳችንን በራሳችን ጠልፈን እየጣልን የባዕዳን መዘባበቻ ሆነናል፡፡ የዓለም ጥቁሮችን በአንድነት ያሠለፈ ታሪክ ሠርተን፣ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል እያጠፋን እያነስን ነው፡፡ ከዚህ ታላቅ ድል ጋር የሚመጥን ሰብዕና መላበስ ካልተቻለ የታሪክ ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ የዚህች አገር አንድነትና ህልውና የሚታሰበውና ብዙ የሚባልለት ለዚህ ነው፡፡

በአሁኗ ኢትዮጵያ ሕዝቡን ለጋራ ዓላማ አስተሳስሮ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን እያሰፉ ከመገፋፋት ይልቅ እንደ ቀድሞዎቹ ጀግኖች አባቶችና እናቶች፣ የጋራ የሆነች አገርን ጥቅም የማስቀደም አስፈላጊነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለተወሰነ ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ብቻ በሚደረግ ሽኩቻ የአገርና የሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ ለዘመናት በመከባበርና በመፈቃቀድ ልዩነቶቹን አቻችሎ ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሲገብር ለኖረው ለዚህ አኩሪ ሕዝብ፣ ሰላሙንና አንድነቱን የሚገዘግዙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች መገታት አለባቸው፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን በተጋድሎው በአንድነት ያስተሳሰረ ይኼ ጀግና ሕዝብ፣ በስሜታዊነትና በደም ፍላት በሚቅበዘበዙ ወገኖች ምክንያት ሊፈታ አይገባውም፡፡ ከአገሩ አንድነትና ህልውና በላይ ምንም የሚበልጥበት ነገር እንደሌለ ዓድዋ ምስክር ነው፡፡

ባለፉት አራት አሥርቶች በፖለቲካ ልሂቃን መካከል በተካሄደው አላስፈላጊ ደም አፋሳሽ ትግል ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል፡፡ ብዙዎቹ በእስር ቤት ተንገላተዋል፡፡ የተረፉት ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ይኼ የዘመናችን የጥላቻ ፖለቲካ የፈጠረው በሽታ አሁንም ድረስ አለቅ ብሎ ወንድማማቾችን ወደ በለጠ ጥፋት እየነዳቸው ነው፡፡ በየቦታው በቅራኔ የተወጠሩ፣ ለቂምና ለበቀል የሚፈላለጉ በዝተዋል፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፣ የጠቡ ጎዳና የበለጠ እየሰፋ ነው፡፡ የአገር ብሔራዊ ጥቅምና የጋራ አጀንዳ ጠፍቶ ሥልጣኑን በማጠባበቅ ላይ የተወጠረውና ሥልጣን በተገኘው አጋጣሚ እንዴት ይነጠቃል የሚለው የሁለት ጎራዎች ፍጥጫ ሆኗል፡፡ ለዓለም በመቻቻልና በመከባበር ተምሳሌት ሆና የቆየች አገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብሔርና የሃይማኖት ጥበት የተጠናወታቸው ወገኖች ጭምር ይፋጠጡባታል፡፡ ዓለም ታላቁንና አንፀባራቂውን የዓድዋ ድል እያስታወሰ አሁንም ድረስ በሚደመምበት ጊዜ፣ እዚህ ድሉን የሚያንኳስሱና አገርን የሚያሳዝኑ ድርጊቶች በየቦታው ይታያሉ፡፡ እንዲህ እየተሆነ እስከ መቼ ይዘለቃል? መፍትሔ ካልተፈለገ የአገርና የሕዝብ አንድነትና ህልውና አደጋ ውስጥ ነው፡፡

ብዙዎቹ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት በዓድዋ የጣሊያን ወራሪዎች ላይ የተገኘው ድል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የመሠረታዊ ለውጥ ጅማሬ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ልዩ ትኩረትና ዕውቅና እንድታገኝ አስችሏታል፡፡ የአፍሪካውያን ብቻ ሳትሆን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ አድርጓታል፡፡ ለፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ ተምሳሌትና ነፀብራቅ ሆናለች፡፡ አፍሪካውያን በዚህ ታሪካዊ ተጋድሎ በተገኘ ድል ተነሳስተው ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ ሲወጡ፣ ኢትዮጵያ የጋራ መሰባሰቢያ ቤታቸው እንድትሆን መርጠዋታል፡፡ በሌላ በኩል የኢጣሊያ መንግሥትና ወታደራዊ ተቋም ብቻ ሳይሆን፣ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ኃፍረት ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጋቸው ይኼ ታላቅ የድል ገድል ነው፡፡ ይህንን የመሰለ የሚያኮራና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር አኩሪ ታሪክ ተይዞ፣ ለዚህች አገር ህልውና መቀጠል መታገል ሲገባ ያልተገባ ተግባር ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በመከባበርና በመነጋገር ችግራቸውን መፍታት እያቃታቸው ነው፡፡ እንኳን ወራሪን ለመመከት እርስ በርስ በሰላም ለመነጋገር ወኔ አጥተዋል፡፡ ይኼ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡ የታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ሲዘከር የአገር አንድነትን የሚያጠናክር ደማቅ ታሪክ መሠራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእርግማንና ከወቀሳ፣ ከብጥብጥና ከመደማማት ተወጥቶ ለአገርና ለሕዝብ የሚመች ተግባር ይከናወን፡፡ ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ሲዘከር የአገሪቱ አንድነትና ህልውና ይታሰብበት!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣...

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...