Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜና​የዴቪድ ካሜሮን የኢትዮጵያ ጉብኝት በደኅንነት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተጠቆመ

  ​የዴቪድ ካሜሮን የኢትዮጵያ ጉብኝት በደኅንነት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ተጠቆመ

  ቀን:

  • የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የልዑኩ አባል ናቸው

  የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በመጋቢት ወር ሦስተኛ ሳምንት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ያደረጉት ፕሮግራም ዋነኛ ትኩረቱ፣ በሁለቱ አገሮች የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትብብር እንደሚሆን ዲፕሎማቲክ ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

  የዴቪድ ካሜሮን ጉብኝት ከደኅንነት ጉዳዮች በተጨማሪ፣ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ በምታቀርበው የልማት ፋይናንስ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ ውስጥ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የዓለም አቀፍ ልማትና ትብብር ሚኒስትር፣ እንዲሁም የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ እንደሚገኙበት ምንጮች ገልጸዋል፡፡

  ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለዓመታት የዘለቀ የፀጥታና የደኅንነት ጉዳዮች ትብብር እንዳላቸው ያስታወሱት ምንጮች፣ የኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች በእንግሊዝ መንግሥት ሙሉ ወጪ በደኅንነት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ ትምህርት በእንግሊዝ እንደሚከታተሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ከሚያገለግሉ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት የማስተርስ ዲግሪያቸውን በደኅንነት ዙሪያ በእንግሊዝ ተከታትለው ማጠናቀቃቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በዴቪድ ካሜሮን ጉብኝት ይኼው የደኅንነት የሰው ኃይል አቅም ግንባታን የማጠናከር ጉዳይ አንዱ የመወያያ አጀንዳ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትጫወተውን የፀጥታና የደኅንነት ሚና ማጠናከር፣ ከአፍሪካ ቀንድ ወደ አውሮፓ በሚደረግ ስደትና በደኅንነት ሥጋቶች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡

  ኢትዮጵያ ከውጭ መንግሥታት ከምታገኘው የልማት ፋይናንስ በመጠንም ሆነ በጥራት እንግሊዝ ቀዳሚዋ መሆኗን የሚናገሩት ምንጮች፣ በዓመት ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ እንደምታገኝ ገልጸዋል፡፡

  ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ በሚፈጥሩት ግፊት አንዳንድ አገሮች ቃል የገቡትን የልማት ፋይናንስ ሲያዘገዩ ወይም የፖለቲካ ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ፣ እንግሊዝ አቋሟን ቀይራ እንደማታውቅ ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዴቪድ ካሜሮን ጉብኝትን የግንቦት ሰባት አመራር ከነበሩትና በኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ከሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር አገናኝተው ዘግበዋል፡፡ ምንጮቹ ግን የጉብኝቱ ትኩረት ባይሆንም፣ በጎንዮሽ ውይይት ይነሳል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች አቶ አንዳርጋቸውን ከየመን ሰንዓ አውሮፕላን ማሪፊያ  ከየመን የፀጥታ ኃይሎች ተረክበው ወደ ኢትዮጵያ እንዳመጧቸው ይታወሳል፡፡

  አቶ አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በእሳቸው ላይ በወሰደችው ዕርምጃ የእንግሊዝ መንግሥት ዝምታን መምረጡ፣ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ትችት አስከትሎበታል፡፡ ይኼ ጫናም እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋማት የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቋርጥ የሚጠይቅ ሲሆን፣ የእንግሊዝ መንግሥትም ከስድስት ወራት በፊት ይህንን ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ገልጾ ነበር፡፡

  በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆነ አባል ሆና ለመመረጥ የምታደርገውን ጥረት ከደገፉ ምዕራባውያን አንዷ እንግሊዝ ስትሆን ሌላኛዋ ደግሞ አሜሪካ ነች፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያን በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አፍሪካን እንድትወከል በሴኔጋል ተቃውሞ ብቻ ከወር በፊት በአዲስ አበባ ባካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ወስኗል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዚህ ሳምንት ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡

  አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የዓለም ኃያላን የሆኑት የአሜሪካና የእንግሊዝ መሪዎች ኢትዮጵያን መጎብኘት፣ ኢትዮጵያ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆነ አባል ለመሆን ያደረባትን ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጉጉት እንዲሳካ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...