አውራሪስ ከዝሆን ቀጥሎ ከየብስ እንስሳት ሁለተኛው ግዙፍ እንስሳ ነው፡፡ አምስት ዓይነት ዝርያዎች ሲኖሩት ሁለቱ በአፍሪካ፣ ሦስቱ በእስያ ይገኛሉ፡፡
ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› በሚለው ድርሳናቸው እንደገለጹት፣ አውራሪስ 1.5 ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ክብደቱ ከአንድ እስከ ሁለት ቶን ይመዝናል፡፡ ነጩ አውራሪስ ሁለት ቶን ያህል ሲመዝን፣ ጥቁሩ ደግሞ ከአንድ እስከ 1.5 ቶን ይሆናል፡፡
አውራሪሶች ጥሩ የማሽተትና የመስማት ችሎታ ቢኖራቸውም የማየት ችሎታቸው ግን ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የቅርቡን ብቻ ተመልካች አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ወዳጅና ጠላት ለመለየት የሚጠቀሙት ዘዴ የትኛውንም የሚረብሽ በአካባቢያቸው ያለን ነገር እንደጠላት በመቁጠር ነው፡፡ ነጮቹ ዝርያዎች የጥቁሮቹን ያህል ባይሆኑም ትንኮሳ ከተካሄደባቸው ግን እነሱም አደገኛ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
አውራሪሶች ብዙውን ጊዜ ትግል የሚያካሂዱት በቀንዳቸው ነው፡፡ የቀንዳቸው ርዝመት አንድ ሜትር አካባቢ የሚደርስ ሲሆን፣ የዙሪያቸውን መጠን ግማሽ ሜትር ይገመታል፡፡ ይሄ እንስሳም ከዝሆን ቀጥሎ በትልቅነቱ የሚታወቅ የየብስ ላይ እንስሳ ነው፡፡