ድንገት ሰማይ ተከፍቶ አለቀሰ
ደመና ቋጥሮ ምድርን አራሰ
ፀሐይም ብርሃን ጮራ ነፍጋ
ወራት ተቀየሩ ክረምት ሆነ በጋ
ወንዝና ተራራ ጋራው ሳር ቅጠሉ
በሐዘን ተኮራምተው ቀና ደፋ እያሉ
ካካላቸው ቁራጭ ቅጠል እየጣሉ
‹‹ፍቅር ተገነዘ ሊቀበር ነው›› አሉ
ውበት ፈገግታዋን ከላይዋ አውልቃ
ጠላሸት ተቀባች አዘነች ጨረቃ
በመረረ ስሜት እጅግ ስለባቡ
ምድር ማየት ጠሉ ክዋክብት አነቡ
የአዕዋፋት ዝማሬ ተረሳቸው ወጉ
የንጋትን ብስራት ዶሮዎች ዘነጉ
ኩርፊያና ፍቅራችን የእኔና የእሷ ሳለ
በፍጡራን ሁሉ ድብርት ተጣለ
ታሪኩ ከበደ ‹‹ምክረ ሰይጣን›› (2008 ዓ.ም.)