በአንድነት ኃይሉ
መንግሥት ምንድነው? ባለ ሀብት ግለሰብስ? የሚለያያቸውንና የሚያመሳስላቸው የሚጠበቅባቸውንና የማይጠበቅባቸውን ብቻ ካየን ምን የማን ኃላፊነት እንደሆነ እንግባባለን፡፡ በአንድ አገር ውስጥ መንግሥት ብቻ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸው መንግሥትን መንግሥት ከሚያስብሉት ነገሮች መሀል አንዱ ነው፡፡ በማንም ሊተካ የማይችል ኃላፊነት ከማንም የማይጠበቅ ግዴታ በማንም ሊነፈግ የማይቻል መብት ባለቤት ሕዝብ ስለሚያደርገው ነው፡፡ ሕዝብ መንግሥት የሚያቋቁመው እነዚህን መብትና ግዴታ የሚያከናውንለት የግለሰብ ስብስብን ይሠራል፡፡
መንግሥት ለገንዘብ ትርፍ አይቋቋምም፣ መንግሥት ገንዘብን አያተርፍም፣ ገንዘብም አይከስርም፣ ግለሰብ ገንዘብን ከገበያ ያሰባስባል ትርፍና ኪሳራውን በገንዘብ ሊተምነው ይችላል፡፡ ስለዚህ ገንዘብን ያተርፋል ይከስራል፡፡ ዓላማውም ግዴታውም ነው፡፡ መንግሥት ግን ሕዝብ የሰጠውን መብትና ግዴታ ተጠቅሞ ገንዘብ ያዘጋጃል፡፡ መንግሥት በምንም ምክንያት ወደ ገበያ ውስጥ ቢያሠራጨው ብር ከሰርኩ አይልም፡፡ በምንም ምክንያት ወደ ገበያ የገባ ብር ለሌሎች ዘርፎች ሥራ ነውና ግለሰብ ግን ገንዘብን ይከስራል ገንዘብ ለማትረፍ ነው የተቋቋመው፡፡ ግለሰቡ መሠረቱ አገር ብትሆንም ዓላማው ግን ገንዘብን ማትረፍ ነው፡፡ መንግሥት ብሎ ደሃ ግለሰብ ብሎ ሀብታም ግራ የሚያጋባ ፍልስፍና ነው፡፡ ያውም በገንዘብ ሲወዳደሩ ስህተቱን ያብሰዋል፡፡ መንግሥት ሥራን አቅቶኛል ብሎ ሲተውና የሚተካኝ አግኝቻለሁ ሠርቻለሁ ብሎ ሲወጣ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ማንም ሕፃን አባቱ የሚሳነው ነገር እንደሌለ እንደሚያምን ሁሉ ሕዝብም መንግሥት የሚሳነው ነገር እንደሌለ እንደሚያምነው አይደለም፡፡ በውስጡ ምንም ስህተት የለውም፡፡ መንግሥት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የሚሳነው ነገር የለም፡፡ ለአንድ ሕዝብ ማንም ያላየውን የሚያሳየው፣ ማንም ያላሰበውን የሚያስበው፣ ማንም ያልሞከረውን የሚሞክርለት ነው፡፡ መንግሥት ለሕዝብ በማንም የማይተካ ኃላፊነትና ሚናውን ለግለሰብ አሳልፎ መስጠት አይችልም፡፡ መንግሥት ለሕዝብ የማይተካ ሚና ድምር ውጤት ነውና፡፡ መንግሥትን የሚተካ ግለሰብ ሕዝብ መሥራት ግዴታው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ትልልቅ ተቋሞች ለገበያ የቀረቡበት ምክንያት የሚተካ ተገኝቶ ሳይሆን የበርካታ ስህተት ድምር ውጤት መሆኑ ስህተቱ የበለጠ ያከፋዋል፡፡ ጠንካራ ተቋማትን ገንብቶ ለጠንካራ ግለሰብና ሕዝብ መስጠት ድል ነው፡፡ ስህተትን ማረምና ውድቀትን ማቃናት ኃላፊነቱ የሆነ መንግሥት ሥራውን ለማን ሊሰጥ ነው? መንግሥት አቅቶኛል ደክሞኛል ልወጣው አልችልም ብሎ ማለት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይፈታው ችግር የለምና፡፡ መንግሥት የማይሞክረውን ቢሞክረው ኪሳራ የለውም፡፡ ትርፉ ቀጥተኛ ባይሆንም በተዘዋዋሪ ያገኘዋል፡፡ ግለሰብ ቢከስር ትርፉን በምን ሊያካክሰው ነው? እንደ መሪና እንደ አገር እንደ ሕዝብ በርካታ ችግሮች ገጥመውን ሊሆን ይችላል፡፡ የምንወስዳቸው መፍትሔዎች ነገ ልናርማቸው የማንችለው መሆን የለበትም፡፡ የትኛውንም ያክል በርካታ ችግሮች ያሉብን ሕዝቦች ብንሆንም ከችግሮቻችን መውጣት እንደምንችል ተስፋ ከሚጭሩብን መሠረቶቻችን መካከል አሁንም ድረስ በመንግሥት ወይም በኢትዮጵያውያን የሚመሩና የሚተዳደሩ ተቋሞች መኖራቸው ነው፡፡ እነዚህ ተቋሞች ሰው በመሆን ከሰው እንደማናንስ ማድረግ መሥራት የምንችል መሆናችንን በዘመኑ ቢመሰክሩም ዛሬ ላይ ተጨማሪ የኬሚካል፣ የመድኃኒትና የምሕንድስና ወዘተ. የበለጡና የተጠናከሩ ተቋማት ተጨምረው ማየትን ስንጠብቅ ያሉትም ለገንዘብ ተብሎ ሊሸጡ መሆኑን ስሰማ የሌሎች ሰዎች ስሜት ምን እንደሆነ ለማወቅ ነበር የጓጓሁት፤ አብዛኛው ሰው ደንግጧል፡፡ አገር ችግር አትሸሽም ሸሽታ የት ልትደርስ ነው መፍትሔው ወደፊት መሄድ እስከሆነ ችግሩን መፍታት እንጂ ሌላ ምርጫ የለም፡፡ የበለጠ የሚያስደነግጠው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ስህተቱን የበለጠ ያከብደዋል፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፣ ኢትዮጵያውያን ስንሆን ይኼንን ያክል የሰው ገንዘብ በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊና መሠረታዊ የሆነበት ታሪካዊ ስህተትን ማረም እንጂ ሌላ ታሪካዊ ስህተት መሥራት ችግርን እንደመሸሽ ነው የሚቆጠረው፡፡ በምንም ዓይነት አስተሳሰብ የሌላ አገር ገንዘብ ለሌላ አገር መሠረታዊ ፍላጎት መሆን አይችልምም ሊሆንም አይገባም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፣ የኛ መሠረት የገዛ ገንዘባችን እንጂ የሰው ገንዘብ አይደለም፡፡ ያኔ በምን ስህተት እንደሆነ ባላውቅም የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና ብለን የተዘፈቅንበትን ስህተት ዛሬ ድረስ ባለማስተካከላችን ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡
ስላሉን ብቻ ተስፋ የምናደርጋቸውን ተቋሞች ሊያሳጣን ደርሷል፡፡ በእኛ ሥር መኖራቸው የጥንካሬያችን፣ የተስፋችን ሰፊ ህልም ዓርማችን ብለን ያልነውን ተቋም የመጣንበት መንገድ ሊያሳጣን ከግቡ ደርሷል፡፡ ይኼ ዜና ለማንም ኢትዮጵያዊ የምስራች ሊሆን አይችልም፡፡ ለመንግሥታችንም መፍትሔ ሊሆን አይችልም፤ በሰው ገንዘብ ቢተካቸውም የሰው ገንዘብ ነውና ገንዘቡ ተመልሶ ወደ አገሩ ይገባል፡፡ የሚገርመው በሰው ገንዘብ የሚሠራ የትኛውም ልማት ነገም የሰው ገንዘብ ፈላጊ ነውና የተሟላ ልማት ነው ልንለው አንችልም፡፡ ፋብሪካ ብናቆም ፋብሪካውን ገዝተን፣ ግብዓት ገዝተን ሲበላሽ መለዋወጫ ገዝተን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ የሰው ገንዘብ የበለጠ ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ ማስገባት የበለጠ የሰው ገንዘብ ፈላጊዎች እንደሚያደርገን የመጣንበት መንገድ በደንብ ያሳየናል፡፡ ዛሬ ላይ ቆም ብለን በችግር ውስጥ ለማለፍ ካልወሰንን ነገ ልንጋፈጠው የማንችለው ችግር እንደሚገጥመን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ዛሬ ላይ የገጠመን የሰው ገንዘብ እጥረት ምክንያቱ የሰው ገንዘብ ይኼንን ያክል በኢኮኖሚ ውስጥ አስፈላጊ መሆኑ ሲሆን መፍትሔውም የሆነበትን ምክንያት በመቀነስና በማስተካከል ኢኮኖሚያችንን በገዛ ገንዘባችን የምንመራበት መንገድ መሥራት ነው፡፡
ትናንት የነበሩ የገንዘብ ዕውቀቶች ዛሬን ተሻግረው አይተውት ነበር ለማለት ባልችልም ዛሬ በዓለም ላይ በርካታ የሆነ የገንዘብ ዕውቀት በሥራ ላይ መዋል እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ አገሮች የተፈጠረውን የገንዘብ የግብይት የልማት ችግር ማየት በቂ ነው፡፡ አገሮች በአገሮች፣ አህጉሮች በአህጉሮች መካከል ሁሉንም ተጠቃሚና ማዕከል ያደረገ ባለን ሀብት ላይ፣ ባለን ዕውቀት ላይ በምንፈልገው ፍላጎት ላይ መሥራት የሚያስችለን አዲስ የገንዘብ መግባቢያ ዘዴን በሥራ ላይ ማዋል ካልቻልን በተለይ የዶላር ባለቤት የሆነችው አሜሪካ አንዳንድ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች ዓለማት ላይ የሚገኘውን ገንዘብ መሰብሰቡ አያሳስባትም ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በፊት ለፊት ባይሆንም ውሰጥ ውስጡን የምትወስደው ዕርምጃ እኛ ከመጣንበት የተሳሳተ መንገድ ጋር ተደማምሮ ችግራችን እንደከበደ ግልጽ ነው፡፡
ግብይት የልማት ምክንያትና ውጤት ብቻ አይደለም፡፡ ልዩነት የፈጠረው ምክንያትና መፍትሔም ነው፡፡ እኛ የተለየ ያለንን የምናበረክትበት እኛ የሌለንን ከሌሎች የምናገኝበት መፍትሔ እንጂ የአንድ የውዴታ ግዴታ ከሆነ ግብይት ሳይሆን ባርነት ይሆናል፡፡ እኛ ምንም ስለጎደለን ሳይሆን ሌሎች የሌላቸውን ብናካፍል የሌለንን ብንቀበል የምንከፈለው ዋጋ መሆኑ በሁሉም ካልታመነ ለብቻችን ልንወስደው የምንችለው ለራሳችን ችግር ራሳችን ኃላፊነት በመውሰድ የመፍትሔው አካል መሆን ብቻ ነው፡፡ እንኳን አገር ግለሰብ ገንዘብ ጠባቂ ሲሆን ስህተት ነው፡፡ ያለንን በማብቃት አንድ ኢትዮጵያዊ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ግብዓት እንዲሆን በማስቻል የሚጎለንንም ያለንንም በአግባቡ ተጠቅመን ቆመን መታየት ካልቻልን በዓለም ፊት ቆመን መፍትሔ ማቅረብ እንደማንችል ግልጽ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ምርትን ከነድክመቱ በመቀበል ለማሳደግ መጣር የግለሰብ ጥረትና ውጤት ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ የግለሰብ ጥረትና ውጤትን በማብቃት ነው አገራችንን ዓለም አቀፋዊ መልክ እንዲኖራት ማስቻል የምንችለው፡፡ መሪ እንደመሪነቱ፣ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ግለሰብ እንደ ግለሰብ ያለብን ችግርና መፍትሔ ልናምንበትና ሊገባን ይገባል፡፡ ያኔ ነው ምንም ችግር ቢገጥመን የምንፀናው የምንፈልገው ላይ ለመድረስ ጠንክረን የምንለፋው ተስፋ የማንቆርጠው ራሳችንን ከማንም ጋር እያወዳደርን ሳይሆን የገባንበትን ችግር ከመፍትሔው ጋር እያወዳደርን ስንጓዝ ነው በችግር ውስጥ ማለፍ የምንችለው ያኔ ባለድል ለመሆን መንገድ ሩቅ አይሆንምብንም፡፡
ድሮም ዛሬም አስተምረንም ተምረንም የዶላር ጥገኞች ከሆንን የተሳሳትነው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ አገር እንኳን የሰው ገንዘብ የራሷ ገንዘብ የተራራን ያክል ቢቆለል መፍትሔ መሆን የሚችለው በዕውቀት ነው፡፡ ገንዘብ የተለያየ ዕውቀትን ለማስተሳሰር በሥራ ላይ ይውላል እንጂ ገንዘብ በራሱ ተራ ነገር ነው፡፡ እኛ እኮ ችግራችን የሰው ገንዘብ ሳይሆን የገዛ ገንዘባችንን መጠቀም አለመቻላችን ነው፡፡ በምንም ሁኔታ የተለያዩ ሰዎች አንዱ ችግር ይዞ ሌላው መፍትሔ ይዞ የተቸገረውም ከነችግሩ ባለመፍትሔው ከነ መፍትሔው በገንዘብ ዕጦት ሳይገናኙ የሚቀርበት መንገድ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ምክንያቱም በኢኮኖሚያችን ውስጥ የሰው ዕውቀት፣ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ ገበያውን ስለተቆጣጠረው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ጭራሽ በጣም ከፍ ብለው የሚታዩንን ሀብቶች ሊያሳጣን ነው፡፡ የትኛዋም ሉዓላዊት አገር የራሷ ገንዘብ አይቸግራትም፡፡ ለየትኛውም አገርና ሕዝብ ዕድገት ገንዘብ ምንም ቦታ የለውም፡፡ ትልቁ መፍትሔ ዕውቀት ነው፣ ዕውቀት በብር አይገዛም ዕውቀት በብር አይሠራም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ ሀብት ግን በገንዘብ ይበዛል ይዳረሳል እኛ የሰው ገንዘብ የፈለግነው የሰው ዕውቀት ስለፈለግን ነው፡፡ ዛሬ ላይ ተምረንም አስተምረንም በራሳችን ዕውቀትና ገንዘብ ላይ ጥገኛ መሆን ያልቻልንበት ትልቁ ምክንያት በርካታ ነገሮችን ስለለመድን ልማዳችንን ላለማጣት በችግር ውስጥ ከማለፍ ይልቅ ችግርን እየሸሸን መኖር ስለመረጥን ነው፡፡ እኛ በችግር ውስጥ ለማለፍ የምንችለው ሁላችንም ስለችግራችን ሲገባንና ኃላፊነት ስንወስድ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ቆም ብለን የሰው ገንዘብ የሰው ዕውቀት የለመድንበትን ምክንያት በመፈተሽ ካላስተካከልን ገና ገና ብዙ እናያለን፡፡ የትኛውም መንግሥትና ሕዝብ ገንዘብ አይከስርም አያተርፍምም፡፡ ሕዝብ ከሰረ የሚባለው ሥራ መፍጠር፣ ሀብቱን መጠቀም ሲያቅተው ነው፡፡ አተረፈ የሚባለው ሥራ መፍጠር ዕውቀቱን ማደራጀት፣ ሀብቱን መጠቀም ሲችል ነው፡፡ በምንም መሥፈርት ለግለሰብ እንጂ ለአገር ገንዘብ ሀብት አይደለም የአገር ሀብት በፋብሪካ የምታመርተውን ብር በሥራ ላይ ማዋል መቻል የተለያየ ዘርፍ በመፍጠር እርስ በርሱ እንዲመጋገብ ማስቻል እንጂ ለአገር ገንዘብ የፋብሪካ ውጤት ነው፡፡ እንዳሻት ልታመርተው ትችላለች፡፡ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ካላወቀች በትክክለኛው መንገድ በሥራ ላይ ማዋል ካልቻለች ነው ችግሩ የከፋ የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ በርካታ የትምህርት ተቋማት እንዳሉን በርካታ የተማሩ ሰዎች እንዳሉን ግልጽ ነው፡፡ ዕውቀቱን ወደ ሥራነት ወደ ሀብትነት ለመቀየር የሚያስፈልገው ግብዓት የሰው ገንዘብ ከሆነ ትምህርቱ፣ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ነው ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ መሆን ያለበት ጉዳይ ላይ፣ መሆን የሌለበት ጉዳይ ላይ በትክክል ገብቶን ኃላፊነታችንን መወጣት ካልቻልን ማድረግ የሚገባንን ተግባር ባለማድረጋችን እያደረሰብን ያለውን ጉዳት መረዳት አልቻልንም፤ ወይም ድህነት ተስማምቶናል ማለት ነው፡፡ ከድሮው የባሰ ዛሬ ላይ እየሠራን ያለነው ስህተት የውጭ ምንዛሪ ላለመፈለግ ከመሥራት ይልቅ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ጠንክረን መሥራታችን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከትክክለኛው መፍትሔ እጅግ በጣም የራቅን መሆኑን ነው፡፡ ዛሬ ላይ ያሉንን ተቋማት በየትኛውም ብር ብንሸጣቸው ትልቁን ምስል ከውስጣችን ከማውጣት ውጪ የሰው ገንዘብ አጠቃቀምና ፍላጎት አጠቃቀማችን ካላስተካከልን ብሩ ማለቁ ብቻ ሳይሆን ነገ የማይተካና ሌላ ፍላጎት እንደሚያደርገን የሚታይ ነው፡፡ የተፈጠረውን ችግር በዓለም አቀፋም ይሁን በሕዝብ ተቀባይነት ያለው መንግሥት መጋፈጥ ካልቻለ ነገ ግለሰብ ቢገጥመው ምን ሊያደርግ ነው፡፡ መንግሥት መወጣት ያቃተውን ግለሰብ ምን ሊያደርገው ይችላል፡፡ እውነት ከመንግሥት ይልቅ ግለሰብ የውጭ ምንዛሪ የማግኘት አቅሙ የተሻለ ሆኖ ነው፣ ነገ ላይ ምንድነው ዋስትናችን? እነኚህን ተቋማት ዛሬ ላይ ማጣት ትልቁን አገራዊ ስሜት ቢያሳንስብንም ነገ ላይ ሰው የሚለውን ግላዊ ሞራልና ሰብዕናም ለመፈታተን ዳር ዳር እንደሚል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ትልቁን አገራዊ ስሜት ሰዋዊ ሰብዕና መሸራረፍ የሚጀመረው እንደዚህ አገራዊ ራዕይ ያላቸውን ተቋም በመናድ ነው፡፡ ሰዋዊ አገራዊ ስሜት የሚገነባው አገራዊ ተቋማትንና ውጤትን በማብቃት ብቻና ብቻ ነው፡፡ አገራዊ ተቋም በነጠፈ ቁጥር የኔ የሚል ስሜት በጠፋ ቁጥር አገራዊ ስሜትንና ኃላፊነትን የምንፈጥርበትና የምናደራጅበት ግብዓት እንዳያሳጣን ቆም ብለን ልናስብበት ይገባል፡፡
መሠረታዊ ችግራችንን ሳናስተካክል አገራዊ ተቋማትን እንኳን መሥራት መምራት እንደማንችል በግልጽ ታይቷል፡፡ መሠረታዊ ችግራችን በርካታ ቢሆንም የሁሉም መሠረት ግን ከድህነታችን ለመውጣት በገዛ ዕውቀታችን ሳይሆን በሰው ዕውቀት ስለምንታገል ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡