Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ግብር የሚፈለግበት ኪንግናም ንብረቱ ታገደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ዘርፍ ለ20 ዓመታት ያህል ሲሳተፍ የቆየው ኪንግናም የተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ፣ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መክፈል የነበረበትን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ግብር ባለመክፈሉ፣ የኩባንያው የተለያዩ ንብረቶች ታገዱ፡፡ ኮሪያዊው ሥራ አስኪያጅም ከአገር እንዳይወጡ ታዘዘ፡፡

ኪንግናም የተለያዩ መንገዶችን ቢገነባም በ2007 ዓ.ም. ደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ በመክሰሩ የምዝበራና የሙስና ክስ ከተመሠረተበት በኋላ፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ የነበረው የሥራ እንቅስቃሴ ተዳክሞ የመንገድ ፕሮጀክት እስከመነጠቅ ደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ አገር ያስገባቸውን ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ሕጋዊ ውክልና ያለው የአገር ውስጥ ወኪል በመቅጠር ቀረጥ እየከፈለ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ኪንግናም ኢንተርፕራይዝስ ኤስኤም ግሩፕ የተባለ ኩባንያ ከገዛው በኋላና አዲስ አስተዳዳሪ ከተሾመ በኋላ፣ በኩባንያው አካሄድና የታክስ አከፋፈል ላይ በመንግሥት ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡ ኩባንያው በተሸጠበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት 14 ሚሊዮን ዶላር (600 ሚሊዮን ብር) ዕዳ እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ማስከበር የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ገላን ሰቦቃ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኪንግናም ለመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ከ1,000 በላይ ተሽከርካሪዎችንና ማሽኖችን ቀረጥና ግብር ሳይከፍል በጊዜያዊ የጉምሩክ ቦንድ አስገብቷል፡፡ ኩባንያው ሕጉ በሚፈቅድለት መንገድ ማሽኖቹንና ተሽከርካሪዎቹን ከቀረጥ ነፃ ማስገባቱን የገለጹት አቶ ገላን፣ የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ያጠናቀቀ በመሆኑ ሦስት አማራጮች እንደነበሩት ተናግረዋል፡፡

ቀረጥና ግብር በመክፈል ተሽከርካሪዎቹንና ማሽኖቹን በአገር ውስጥ መሸጥ፣ ወደ ደቡብ ኮሪያ መላክ ወይም ተገቢውን ቀረጥና ግብር ከፍሎ እንደ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ላሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መለገስ ይችል እንደነበር ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ኪንግናም የሚጠበቅበትን ቀረጥና ግብር ሳይከፍል ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች እየሸጠ እንደሆነ በደረሰው ጥቆማ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በኩባንያው ላይ ምርመራ አካሂዷል፡፡

በተደረገው ምርመራ በርካታ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች እንደተሰወሩ ተረጋግጧል፡፡ ‹‹በተሠራው የምርመራ ኦዲት ያልተገኙ ዕቃዎች አሉ፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ከአገር ለመውጣታቸው መረጃ ያልቀረበ በመሆኑ፣ ለሌላ ወገን እንደተላለፉ ለማወቅ ተችሏል፤›› ያሉት አቶ ገላን፣ ለተሰወሩት ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ቀረጥና ግብር ኪንግናም ከእነ ቅጣቱ 171 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል እንደተወሰነበት ገልጸዋል፡፡

የኦዲት ሪፖርቱ ተሽከርካሪዎቹና ማሽኖቹን በሁለት ከፍሏቸዋል፡፡ የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቃ በጊዜያዊ የጉምሩክ ቦንድ ገብተው ከአገር መውጫ ጊዜ ያለፈባቸው በሚል የተለዩት ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች፣ ተገቢው ቀረጥና ግብር ሳይከፈልባቸው ከአገር መውጫ ጊዜያቸው እንዳለፈባቸው ታውቋል፡፡

ኪንግናም ከቀረጥ ነፃ ካስገባቸው አንድ ሺሕ በላይ ማሽኖች በቆጠራ የተገኙት 625 ብቻ ያህሉ እንደሆነ አቶ ገላን ገልጸዋል፡፡ በጊዜያዊ ቦንድ ገብተው ከአገር የመውጫ ጊዜ ላለፈባቸው ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ቀረጥና ግብር 91 ሚሊዮን ብር ኪንግናም እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡ በአጠቃላይ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ ጽሕፈት ቤት ኪንግናም 263 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ወስኗል፡፡

እንደ አቶ ገላን ገለጻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኩባንያው የተወሰነበትን ቀረጥና ግብር እንዲከፍል በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ጽፈናል፡፡ በአካልም ጭምር ሄደን ኃላፊዎቹን ብናነጋግርም ክፍያውን ሊፈጽሙ አልቻሉም፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም የታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 በሚፈቅደው መሠረት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የኪንግናም ኩባንያ ንብረትን እያደነ መያዝ ጀምሯል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በወሰደው ዕርምጃ በቅርቡ ንብረትነታቸው የኪንግናም ኩባንያ የሆኑ ስምንት ተሽከርካሪዎች (ሁለት ቪኤይት፣ ሁለት ላንድ ክሩዘር፣ ሁለት ፒክአፕና ሁለት ዶልፊን ሚኒባስ) ይዞ ወደ ጉምሩክ መጋዘን አስገብቷል፡፡ የኪንግናምን የባንክ ሒሳቦችን ለማሰስ ለ17 የአገር ውስጥ የመንግሥትና የግል ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ 13 ሚሊዮን ብር ብቻ ማግኘት ችሏል፡፡

በተጨማሪም በዱከም ከተማ ገላን ኢንዱስትሪ ዞን አቅራቢያ የሚገኘውን የኩባንያው ወርክሾፕ አሽጓል፡፡ በወርክሾፑ ውስጥ በርካታ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ገላን፣ ከቅጥር ግቢው እንዳይወጡ መደረጉንና ለጥበቃዎቹም ጥብቅ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ በወርክሾፕ ውስጥ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ እንደ ግሬደርና ሎደር የመሳሰሉ ማሽኖች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ንብረቶቹ እንዳይዘዋወሩና ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፉ ተደርጓል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኤጀንሲ በጻፈው ደብዳቤ የኪንግናም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሊ ጁን ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ አስተላልፏል፡፡ ሪፖርተር ሚስተር ሊ ጁን ሞባይል ስልካቸው ላይ በመደወል፣ በኢሜይል አድራሻቸው ጥያቄዎችን በመላክ አስተያየታቸውን ለማግኘት የሞከረ ቢሆንም፣ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ኩባንያው የአዲስ አበባ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ እንደተደረገባቸው ታውቋል፡፡ ሚስተር ሊ ጁን ኩባንያው ያለበትን ግብር ከመክፈል ይልቅ፣ በየመሥሪያ ቤቱ እየሄዱ አቤቱታ በማቅረብ መጠመዳቸውን አቶ ገላን ገልጸዋል፡፡ ግለሰቡ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቅሬታ እንዳቀረቡ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በጻፈው ደብዳቤ፣ ለኪንግናም የሚከፈል ቀሪ ክፍያ ካለ እንዲያዝበት ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበኩሉ ለኩባንያው የሚፈጸም ምንም ዓይነት ክፍያ እንደሌለ፣ ኩባንያው በእጁ ምንም ዓይነት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እንደማይገኝ ገልጿል፡፡ ኩባንያው ቀደም ሲል ባሳየው ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸም በጥቁር መዝገብ ውስጥ የሰፈረ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ባለሥልጣኑ ለኩባንያው ሌላ ፕሮጀክት ለመስጠት እንደማይችል አስታውቋል፡፡

ኪንግናም የአዲስ አበባ ቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ካቀረበበት የቀረጥ ክፍያ ጥያቄ በተጨማሪ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት 290 ሚሊዮን ብር የግብር ክፍያ እንደሚጠበቅበት ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ኩባንያው ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ዕዳ እንዳለበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኪንግናም የሚገኙ የሪፖርተር ምንጮች ኤስኤም ግሩፕ ኪንግናም ሲገዛ በፊሊፒንስ፣ በስሪላንካ፣ በቬትናምና በኢትዮጵያ ያሉት የኩባንያው ሒሳቦች ኦዲት ያስደረገ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ 14 ሚሊዮን ዶላር የመንግሥት ዕዳ እንዳለበት አውቆ ከእነ ዕዳው እንደተረከበው ገልጸዋል፡፡

የኩባንያው ስም ወደ ኤስኤም ኪንግናም ከተቀየረ በኋላ ተሹመው የመጡት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሚስተር ሊ ጁንና የቅርብ ረዳታቸው የመንግሥት ዕዳ እንዳይከፈል እያከላከሉ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዋና ሥራ አስኪያጁ ግብሩ እንዲነሳ የመንግሥት ባለሥልጣናትን አሳምናለሁ በማለት ከኩባንያው ዳረጎት ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

የኪንግናም ኢትዮጵያ የማቴሪያል ክፍል ኃላፊ የነበሩት ሚስተር ሊ ሚንዩንግ ቹል ኩባንያው ከመሸጡ በፊት ተገቢውን ቀረጥና ግብር በመክፈል፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች በሕጋዊ ወኪሉ አማካይነት ሲሸጡ እንደነበር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች