ለሦስት ዓመታት ያህል የዘለቀው ደም አፋሳሽ ግጭት በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ረገብ ቢልም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀሰቀስ ግጭት ግን ገጽታውንና አድማሱን እያሰፋ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ከተሰየሙበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ቢታይም፣ ከእግር ኳስ ሜዳዎች እስከ ክብረ በዓላት ሥነ ሥርዓቶች ድረስ ምክንያታቸው በውል ያልታወቀ ግጭቶች በብዙ ሥፍራዎች አጋጥመዋል፡፡ በጉጂና በጌዴኦ መካከል ከፍተኛ ዕልቂትና መፈናቀል ደርሷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች አቤቱታ በስፋት እየተደመጠ ሳለ በሐረር፣ በሐዋሳ፣ በወላይታ፣ በወልቂጤ ከተሞች ደግሞ ግጭቶች ተከስተው በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በሐረር ከተማ ባጋጠመ ግጭት በሰው አካልና በንብረት ላይ ጉዳት ሲያጋጥም፣ በሐዋሳ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጨምበላላ ሲከበር ሁከት ተቀስቅሶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በወላይታም እንዲሁ፡፡ የወልቂጤው ደግሞ በእግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል የተነሳው ግጭት አልበቃ ብሎ ወደ ከተማ ተዛምቶ የአንድ ሰው ሕይወት ሲጠፋ፣ በርካታ ቤቶችና መደብሮች ሲቃጠሉ ንብረትም ወድሟል፡፡ በስፋት የሚታዩት ግጭቶች በቶሎ ካልተገቱ ጥፋቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭቶቹ ያጋጠሙባቸው ሥፍራዎች በመገኘት ከኅብረተሰቡ ጋር እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል፡፡ እስከዚያው ድረስ አንፃራዊው ሰላም እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡ ፍጥነት ያስፈልጋል፡፡
አገር ሰላም ከሌላት ዴሞክራሲ አይኖርም፡፡ ልማት አይታሰብም፡፡ የግለሰቦችን ድንገተኛ ጠብ ወደ ብሔር መግፋትና በቂም በቀል ተነሳስቶ የገዛ ወገን ላይ መዝመት ለዚህ ዘመን አስተሳሰብ የሚመጥን አይደለም፡፡ ይህ ያለንበት ዘመን ልዩነትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያቀራርቡበት ወይም ላለመስማማትም ቢሆን የሚግባቡት ነው፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን፣ መዝናኛዎችን፣ የሥራ አካባቢዎችንና መኖሪያዎችን እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች የጠብ አውድማ ማድረግ ሰላምን ያደፈርሳል እንጂ ጥቅም የለውም፡፡ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ የሚደረግ ትግልና ጠባብ የቡድን ፍላጎትን ለማንገሥ የሚደረግ ሁከት የተለያዩ ናቸው፡፡ በኳስ ሜዳ የዳኛን ውሳኔ በፀጋ ያለመቀበል ግንፍልተኛ ባህሪ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሌላ ትርምስ ሲፈጥር የንፁኃን ሕይወት ይቀጠፋል፣ አካል ይጎድላል፣ የአገር ሀብት ይወድማል፡፡ ስሜታቸውን መቆጣጠር ባቃታቸው ነውጠኞች ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች ወደ ብሔር ሲገፉ ደግሞ ጥፋቱ ከሚቆጣጠሩት በላይ ይሆናል፡፡
አንፃራዊው የአገር ሰላምና መረጋጋት ተመልሷል እየተባለ ባለበት በዚህ ወቅትና አገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ የአገርን ተስፋና ራዕይ የሚያጨናግፍ ድርጊት ውስጥ መገኘት ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚዎችን ስታገኝ እንደ ወረርሽኝ እያሰለሰ የሚመጣባት ክፉ ደዌ ፈውስ ካልተገኘለት፣ ታሪክ ራሱን እየደገመ ክፋት የበላይነቱን ይይዛል፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ ቂመኝነት፣ ሴረኝነት፣ አሻጥረኝነትና መሰሪነት መላ ካልተፈለገላቸው የሚከፈለው መስዋዕትነት የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው ለአገሩ አንድነትና ክብር አንድ ላይ ሲቆም እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው እርስ በርሱ ሲናደፍ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የእባብ ባህሪይ የተከበረውን ሕዝብ ሲወክልም አይታወቅም፡፡ ሕዝቡ ውስጥ እየተሹለከለኩ ጥላቻ የሚዘሩ፣ ወገንን ከወገን የሚያባሉ፣ ለሥልጣንና ለንዋይ ሲሉ አገርን የማትወጣው አደጋ ውስጥ የሚከቱና ለነገው ትውልድ የማያስቡ ኃይሎች የዚህ ዘመን ውጤት ናቸው፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚባለው ደካማ አስተሳሰብ የሚመሩ ራስ ወዳዶች የአገርን ዕጣ ፈንታ ሊያበላሹ አይገባም፡፡
ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ጎትቶ ለማውጣት የጋራ ዓላማና ግብ ሊኖር ይገባል፡፡ የፖሊሲና የስትራቴጂ ልዩነት ቢኖርም እንኳ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሠለጠነ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ በወገናዊነትና በቡድንተኝነት ላይ የተንጠለጠሉ ኋላ ቀር እሰጥ አገባዎች ውስጥ በመዘፈቅ የአገርን ህልውና መፈታተን መቆሚያና መቀመጫ ያሳጣል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ቢሆንም በምኞት አይገኝም፡፡ በመጀመርያ ለብሔር ብቻ ሳይሆን ለሐሳብ ብዝኃነትም ነፃነት እንደሚያስፈልግ መታወቅ አለበት፡፡ በሰከነ መንገድ በመነጋገር በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደር መቻል የሥልጡን ማኅበረሰቦች የተለመደ ባህል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ግለሰብ ድረስ በጉልበት እኔ ያልኩት ካልሆነ እያሉ መደንፋትም ሆነ ጥቃት መፈጸም ሕገወጥነት ነው፡፡ ለሐሳብ ነፃነት እታገላለሁ የሚለው ሌላውን ወገኑን የሚያጠቃ ከሆነ፣ በምክንያታዊነት መመራት ያለበት በግብታዊነትና በስሜታዊነት እየተነሳሳ ሕይወት የሚያጠፋና ንብረት የሚያወድም ከሆነ፣ እንዴት ነው ስለመብትና ነፃነት መነጋገር የሚቻለው? በጣም ያሳስባል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሉት አኩሪ ፀጋዎች መካከል ዋናው አስተዋይነቱ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን እናውቃለን በሚሉት ዘንድ ከሚያስተውሉት ይልቅ በደመነፍስ የሚመሩት እየበዙ ጭፍንነት በማየሉ፣ አገርን ከባድ ችግር ውስጥ የሚከቱ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ለእነዚህ ምልክቶች ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረቶች እየተደረጉ አይደሉም፡፡ ግጭቶች በተቀሰቀሱባቸው አካባቢዎች ሰዎች እየሞቱ፣ እየተፈናቀሉ፣ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸውና ንብረት እየወደመ ለዘብ ያሉ ድምፆች ናቸው የሚሰሙት፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ ኃይሎች ማንነት እየታወቀ ማድበስበስ የተለመደ ነው፡፡ በአንዳንድ ሥፍራዎች ግጭቶች ሲቀሰቀሱ የፀጥታ ኃይሎች ቸልተኝነት ይታያል፡፡ እንደ ወትሮው የፀጥታ ማስከበር ኃላፊነት ላይ የሚታዩ ቸልተኝነቶች ደግሞ አንድም የግጭት ተሳትፎን ሌላም ምን አገባኝ ባይነትን ስለሚያመላክቱ፣ ለአገር ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ናቸው፡፡ መንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነቱ የሕዝቡን ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ለብሔራዊ ደኅንነት ጭምር አደጋ የሚጋብዙ ሕገወጥ ተግባራትን ማስወገድ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማይቻል ከሆነ የአገር ህልውና አደጋ ይገጥመዋል፡፡ በአገር ህልውና መደራደር ስለማይቻል የግጭት መንስዔዎችን በፍጥነት መላ ማለት ይገባል፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በውስጡ አምቆ የያዛቸው ልዩነቶች በራሳቸው ሌላ ጠንቅ ናቸው፡፡ ልዩነቶች መኖራቸው ጤናማ ነው፡፡ ነገር ግን ጤናማነትን ጠብቆ መጓዝ የሚቻለው ልዩነቶችን ማስተናገድ በሚቻልበት ሥልት ነው፡፡ ፉክክርና እልህ የመጋባት አባዜ ውስጥ ሲገባ፣ በየጎራው የሚነካኩ የጥፋት ቁልፎች ለግጭት መንስዔ ይሆናሉ፡፡ ውስጠ ዴሞክራሲ ተቃውሶ ከሆነ ለዘመኑ ትውልድ የሚመጥን አደረጃጀትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ የድርጅት ህልውና ሊቀጥል የሚችለው በመግባባትና በሰጥቶ መቀበል መርህ መመራት ሲቻል ነው፡፡ አንዱ ወደፊት እያለ ሌላው ወደ ኋላ ልጎትት ካለ ትርፉ ተጠላልፎ መውደቅ ነው፡፡ የአሁኖቹ ምልክቶች ሁሉ የዚህ የመጠላለፍ ምክንያት ናቸው ባይባልም፣ ሌላ ፍላጎትና ዓላማ ያላቸው ወገኖች አሉታዊ ተሳትፎ ውጤት ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዚህ ዓይነት መንገድ እንደማይገነባ መገንዘብ ነው፡፡ በየቦታው ግጭት በመቀስቀስ ዓላማን ማሳካት እንደ ፋሽን ተኮርጆ ከሆነም ፋይዳ የለውም፡፡ ይልቁንም የአገሪቱን ፖለቲካ ከመሰሪነትና ከአሻጥረኝነት በማላቀቅ ቀናውን ጎዳና መያዝ ይሻላል፡፡ አገር የምታድገው፣ የምትበለፅገውና ዴሞክራሲያዊት የምትሆነው በሠለጠነ መንገድ ስትመራ ብቻ ነው፡፡ እያገረሸባቸው ያሉትን ግጭቶች መግታት ካልተቻለ ግን ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው!