Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብሔራዊ ባንክ ገዥና የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች በአዳዲስ አመራሮች ሊተኩ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትን ሪፎርም ለማድረግ እየተደረጉ ባሉ እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊዎች በአዳዲስ አመራሮች ሊተኩ ነው፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ አሁን ባለው መረጃ እሳቸውን ለመተካት የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በዕጩነት ቀርበዋል፡፡

ይናገር (ዶ/ር) የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከሆኑ የአሁኑን ኃላፊነታቸውንና የንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢነታቸውን ይለቃሉ፡፡

ከሳምንታት በፊት ከብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥነት በተነሱት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ምትክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ምክትል ገዥ እንዲሆኑ መታጨታቸው ተሰምቷል፡፡ አቶ በቃሉ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትነት ቢታጩም፣ ባለመፈለጋቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ ይዛወራሉ ተብሏል፡፡

ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትነት በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ አንዱ የቀድሞው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት አሁን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ናቸው፡፡ አቶ ወንድማገኝ በተጨማሪም ለልማት ባንክ ፕሬዚዳንትነት መታጨታቸው ተሰምቷል፡፡

መንግሥት ዋና ዋና የፋይናንስ ተቋማትን በኃላፊነት እንዲመሩለት አገር ውስጥና ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን ሲያፈላልግ ቆይቷል፡፡ አሁን በዕጩነት ቀርበዋል ከተባሉት ኃላፊዎች በተጨማሪ፣ ለሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነቶች ባለሙያዎች የማፈላለጉ ሥራ መቀጠሉን ሪፖርተር ማወቅ ችሏል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንዳረጋገጡት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ላለፉት 13 ዓመታት ሲመሩ የቆዩት አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉና የእሳቸው ማኔጅመንት በአዲስ ይተካል፡፡

በአሁኑ ወቅትም እሳቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለአዳዲስ ተሿሚዎች ኃላፊነታቸውን ለማስረከብ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች