Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ክሳቸው ያልተቋረጠላቸው ተከሳሾች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ክሳቸው ያልተቋረጠላቸው ተከሳሾች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተለያዩ ክፍሎች ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩና በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ተካተው ክስ የተመሠረተባቸው ስምንት ግለሰቦች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አቤቱታ አቀረቡ፡፡

አቤቱታ ያቀረቡት ተከሳሾች የባለሥልጣኑ የኦዲት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በላቸው በየነ፣ የታክስ አማካሪ፣ የቴክኒክ ኮሚቴ አባልና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ማሞ አብዲ፣ ምክትል ዋና ዓቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ መርክነህ ዓለማየሁ፣ ጠበቃው አቶ አውግቸው ክብረት፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም የሥራ ሒደት መሪ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ማርያም፣ አቶ ያለው ቡላና አቶ ተመስገን ጉላል ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጻፉት አቤቱታ እንደገለጹት፣ ክሳቸው በቅርቡ ከተቋረጠላቸው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ የተካተቱ ሲሆን፣ አለቆቻቸውና አብረዋቸው የነበሩ ጓደኞቻቸው ክሳቸው ተቋርጦ ሲለቀቁ እነሱ አልተለቀቁም፡፡ የተመሠረተባቸው ክስም ሆነ ይቀርብባቸው የነበረው የሰውና የሰነድ ማስረጃም ተመሳሳይና አሳማኝ ያልነበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲከራከሩ ቆይተው ጥፋተኛ በመባላቸው ለግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ለቅጣት ተቀጥረው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ 31 ታሳሪዎች ክስ ተቋርጦ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር ሲለቀቁ፣ እነሱ ግን መንግሥት በሰጠው ይቅርታ ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተው ወይም ተረስተው ይሁን ባልታወቀ ምክንያት ተነጥለው መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለአምስት ዓመታት በእስር ላይ ሲቆዩ ከምርመራ ጀምሮ እስከ ፍርድ ባለው የክርክር ሒደት የተከሰሱበት ጉዳይ፣ መደበኛ የመንግሥት ሥራቸውን በሕጉ መሠረት የታክስ ፍትሐዊነትን ለማስፈን በሚያስችል ሁኔታ ሲሠሩ ያከናወኗቸው ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለራሳቸውም ሆነ ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ የፈጸሟቸው ተግባራት አለመሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ክርክሩን ያየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ፍርድ፣ የክስ ምክንያት ሆነው የተገለጹት ተግባራት ለታክስ ተደራሽነትና ፍትሐዊነት የተሠሩ መሆናቸውን በግልጽ ማስፈሩንም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሁኔታዎችን ብቻ መነሻ በማድረግ ‹‹የመንግሥትን ሥራ በማያመች ሁኔታ መምራት›› በሚል አንቀጽ የጥፋተኛነት ውሳኔ እንደሰጠም አስታውሰዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ የፍርድ ሀተታ የሚያመለክተው፣ ሥልጣናቸውን በመጠቀም የታክስ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን የሚያዛባ ተግባር አለመፈጸማቸውን እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ዋስትና ተከልክለው ከፍተኛ ጉዳትና እንግልት እንዲደርስባቸው የተደረገው፣ ታክስ ከፋዩ ኅብረተሰብ ብቃት በሌላቸውና ሥነ ምግባር በጎደላቸው ኦዲተሮች ያለግባብ እንዲከፍሉ የተጠየቀውን ግብርና ታክስ፣ ፍትሐዊና ሕጋዊ እንዲሆን በማድረጋቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ምሥጋና ሊቸራቸው ሲገባ በግልባጩ እነሱን ለእስርና ቤተሰቦቻቸውንም ለእንግልትና ለችግር እንዲጋለጡ መደረጋቸው አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስረዱት፣ ሰዎች የፍትሕ አካላትን በመሣሪያነት በመጠቀም ሕገወጥ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር የሚሠሩ ከሆነና ሕገወጥ ፍላጎታቸው በፍትሕ አካላቱ ላይ የሕግ ሥርዓት ሽፋን ተሰጥቶ ዜጎች ለእስርና እንግልት የሚዳረጉ ከሆነ፣ በደሉ የደረሰባቸው ሰዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚኖራቸው እምነት ከባድ ነው ብለዋል፡፡ በመንግሥታዊ ሥርዓቱም ላይ የሚፈጥረው ቅሬታ በቀላሉ የማይፈታ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በፍትሕ መድረክ እውነቱ ነጥሮና ወጥቶ ነፃነታቸውን እንደሚያገኙ በማመን፣ እስካሁን ክርክራቸውን በማቅረብ የፍርድ ሒደቱንም እየተከታተሉ እንደሚገኙም በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እየወሰደው ያለው ዕርምጃ አበረታችና እነሱም የሚደግፉት መሆኑን ጠቁመው፣ የቀረቡባቸውን ክሶች በማቋረጥ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ እንዲሰጡላቸው፣ ቤተሰቦቻቸውንም ከችግርና እንግልት እንዲታደጉላቸው ጠይቀዋል፡፡ በተለይ በተመሳሳይ ጉዳይና በአንድ መዝገብ አብረዋቸው ተከሰው የነበሩ አለቆቻቸውና ጓደኞቻቸው ክስ ተቋርጦ የእነሱ ተለይቶ መቅረቱ፣ እስካሁን በደረሰባቸው በደልና እንግልት ላይ ተጨምሮ ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውም በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እነሱ ላይ ብቻ የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ቀጠሮ እንደሰጣቸው ጠቁመው፣ ከዚያ በፊት ግን እንዲታደጓቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ተማፅነዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...