ከጓደኛዬ ጋር በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደ ዓውደ ርዕይ ተሳትፈን ለእሱ ሥራ የሚስማማ የመሣሪያ አቅራቢ አግኝቶ ከድርጅቱም ጋር ለመነጋገር በማግሥቱ ቦሌ በሚገኝ አንድ ሆቴል ይቀጣጠራል፡፡ ጓደኛዬ በዕለቱ የሚገናኘው ከኩባንያው ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመሆኑ፣ ደረጃውን የጠበቀ ሙሉ ልብስና ከስድስት ወር በፊት ጓደኛው ከአሜሪካ ያመጣለትን ውድ የሙሉ ልብስ አላባሽ ጫማ ነበር ያደረገው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ይህን ጫማ ጓደኛው አድርጎት ሲመጣ ዓይቶ ስለወደደው በሌላ ጊዜ ሲመለስ ይዞለት እንዲመጣ በነገረው መሠረት ነበር ይዞለት የመጣው፡፡ ጫማውን ስለወደደው እንዲያመጣለት አዘዘው እንጂ፣ ዝርዝር ነገሮች ላይ አልተነጋገሩም ነበር፡፡ ጫማው ከመጣ ለመጀመርያ ጊዜ መድረጉ ነው፡፡ ከቤት ወጥቶ ወደ ቀጠሮው ቦታ መሄድ ጀምሯል፡፡ ቀጠሮ አካባቢ ሊደርስ ሲል ግን ጫማው ሊያራምደው አልቻለም፡፡ አቁስሎታል፡፡
ሌላ ጫማ እንዳይገዛ ተዘጋጅቶ አልወጣም፡፡ ከላይ የለበሰውም ልብስ ደረጃውን ያልጠበቀ ጫማ አይቀበልም፡፡ ቀጠሮ የሰጡን ሰዎችም በሰዓቱ አልደረሱም፡፡ አንደኛው ሌሎች ደንበኞችን ሊያነጋግሩ በሄዱበት መንገድ ተዘግቶባቸው መቆየታቸውን በጽሑፍ መልዕክት አሳወቁን፡፡ ይህን የሚታገስበት ጊዜ የለውም እግሩን አሞታል፡፡ ቀኑም እየመሸ ስለነበር ያለው አማራጭ አነስተኛ የአገር ውስጥ ሸራ ጫማ ገዝቶ ወደ ቤቱ መመለስና በማግሥቱ በጠዋት ለመነጋገር መወሰን ነበር፡፡
በማግሥቱ የሚስማሙትን ነገሮች አድርጎ ወደ ቀጠሮው ቦታ ሲሄድ በመጀመርያው ቀጠሮ ቀን ምሽቱን ወደ አገራቸው መብረራቸውን ይሰማል፡፡ በሆነውም ነገር ያዝናል፡፡ የማይሆን ጫማ ካሰበው ሥራ አስታጎለው፡፡ አትሌቶች ጥሩ ልምምድ አድርገው፣ ጥሩ አቋም ይዘው፣ ጥሩ የመሮጫ ጫማ ባለመምረጥ ብቻ ጥሩ ውጤት ሲያጡ ይታያሉ፡፡ በሚሊዮን ብር የሚገመት ሽልማት ያመልጣቸዋል፡፡ ስለዚህ በሩጫ ወቅት የማይሆን ጫማ አድርጎ ከመሮጥ በባዶ እግራቸው መሮጥን የሚመርጡ እንዳሉ ከጓደኛዬ ጋር አወጋን፡፡
በጫማ የጀመርኩት ሐሳብ የሚያጠነጥነው በአገራችን ሕጎች ዙሪያ የተወሰኑትን ለማነሳሳት ነው፡፡ አንድ አገር የምትራመደው በቀረፀቻቸው ሕጎች ነው፡፡ የአገራችን መሪዎች ከሌሎች ካደጉ አገሮች ዓይተዋቸው የሚወስዷቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለሥራ ጉብኝት ወደ ተለያዩ አገሮች ሲጓዙም ይሁን አስበውበት አገሬ እንዲህ ብትሆን፣ ይህ ቢኖራት፣ ያ ባይኖራት ማለታቸው አይቀርም፡፡ ይህንን ምኞት ለማሳካት ካደጉና በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ሕጎችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣቱ የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ገንቢ ሆነው ሲገኙ፣ ሌሎች ሕጎች ግን ለአገራችን ተስማሚነታቸው ያልተፈተሸ፣ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታዎች ያላገናዘቡ ከመሆን አልፈው፣ አብዛኞቹ በሚባል መልኩ ካደጉ አገሮች የተኮረጁ በመሆናቸው ምክንያት ውጤታማ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡
ውጤታማ አለመሆናቸውን እያየን እንኳ ማስተካከያ ባለማድረጋችን፣ የብዙዎችን ሕይወት ካጤንን፣ የአገር ሀብት ካወደመ፣ ብዙ ሥራ አጦች ከተፈጠሩ በኋላ ዘግይተን ከእንቅልፉ እንደነቃ ሕፃን መጮኽ እንጀምራለን፡፡ አንዳንዶቹ የአገራችን ሕጎች ደግሞ እንዲህ አድርገናል ለማለት ያህል ወይም የአፍሪካ ኅብረት ወይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል በመሆናችን ብቻ ተቀብለናቸው፣ በአዋጅ ፀድቀው ሥራ ላይ ሳይውሉ አስፈጻሚውም ሳይተገብራቸው የሚቀሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም የሚቀናባት በርካታ ጥሩ ጎኖች አላት፡፡ የሦስት ሺሕ ዓመታት አኩሪ ታሪክ ያላት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የራሷ ሀብት የሆኑ የኪነ ሕንፃ አሠራር ጥበብ የቀን አቆጣጠር፣ የገዳ ሥርዓት፣ እንዲሁም የራሷ ፊደሎችና የሃይማኖቶች ብዝኃነት የሚታይባት፣ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆና የኖረች አገር ነች፡፡
ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ የነበረንን የኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ ምን ወሰደው? ቴክኖሎጂንና ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ሕጎችን መኮረጅ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን የራሳችን የሆነውንና ለእኛ የሚስማማን፣ ለገጠሩም ለከተማውም የሚሆነውን፣ ሕግ፣ መመርያና ደንብ ለራሳችን እንደሚስማማን መቅረፅ አቅቶን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በጥናት ስም በማውጣት ከምዕራባውያን ገልብጠን እናመጣለን፡፡ ከእኛ ጋር ቅርርብ ከሌላቸው፣ ሰፊ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልዩነት ካለን አገሮች የምንገለብጠው፣ በአገራችን ምሁራንና ታላላቅ ሰዎች ጠፍተው ነው? ወይስ በእጅ የያዙት ወርቅ እንደሚባለው ሆኖብን ነው? በርካታ የኮረጅናቸው መመርያዎች የጥቂቶችን ኪስ ሲሞሉ፣ በተቃራኒው የብዙዎችን ሕይወት ካጠፉ ወይም ካስተጓጎሉ በኋላ ለአገራችን አይሆኑም ተብለው የሚለወጡ አሉ፡፡
ለዚህ ማሳያው ከዚህ በፊት ብዙ የተባለለት የትራንስፖርት የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሕግ፣ በአገራችን ለሰው ሕይወት ህልፈትና ለንብረት መውደም ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ ሕግ ቀድሞ በነበረው ፈቃድ አሰጣጥ ተተክቷል የሚለውን ስንሰማ፣ ትናንት ለአገራችን የማይስማማ ብሎም ብዙ ጉዳት ያደረሰን ሕግ ወደ ሥራ ያስገቡ አካላት ያጠኑት ምንድን ነበር ያሰኘናል፡፡ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳያስገባ የተተገበረ ሕግ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት አካሄድ አገርን የሚጎዱ አካላት የሚጠየቁበት ሥርዓት ሊዘረጋ ግድ ነው፡፡ ለጥፋታቸውም ተመጣጣኝ ቅጣት ሊያገኙና ሌሎችም ሊማሩባቸው የሚችሉባቸው ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው፡፡
የትምህርት ሥርዓቱም ተመሳሳይ ችግር አለበት፡፡ የትምህርትን ጥራት ከመግደል አልፎ በአገሪቱ የተማሩ ሥራ አጦች እንዲበራከቱ በማድረግ በአገር ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት መገመት ቀላል ነው፡፡ የትምህርት ዕድል መብዛቱ ጥሩ ነው፡፡ እነህንድ የተማረውን የሰው ኃይላቸውን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ ለአገራቸው የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ነው፡፡
እኛ ግን የውጭ ሐዋላ ገቢ ማግኘቱ ቀርቶ እንኳ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት አልቻልንም፡፡ ጥራት በሌለው የትምህርት ሥርዓት ያለፈ አስተማሪ ሲኖር ደግሞ ሁሉ ነገር የተበላሸ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መምህር ትውልድ ይቀርፃልና፡፡ የጤና ባለሙያ ሲሆን፣ ከሰው ሕይወት ጋር በተገናኘ የሚሰጠው አገልግሎት በተገቢው ደረጃ ካልተገራ ጉዳቱ ይከፋል፡፡ መሐንዲሱ ተገንብተው ከማለቃቸው በፊት የሚፈርሱ ሕንፃዎችን ይሠራል፡፡ አገር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአደጋው ግንባር ቀደም ተጎጂ ትሆናለች፡፡ የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ ሚዛኗን ታጣለች፡፡ ዜጎች ከአገራቸው ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅሞች በወቅቱና በተገቢው መጠን አያገኙም፡፡ በገዛ አገራቸው እኩል ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ በኑሯቸውም ደስተኛ ስለማይሆኑ ይሰደዳሉ፡፡ በስደትም ለሞትና ለከፋ ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ አገራቸው ለአንዱ እናት ለአንዱ የእንጀራ እናት ሆናባቸዋለች፡፡
የትምህርት ሕጉ በተለይ በግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታዩትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሊፈታ አልቻለም፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ዜጎች፣ ከመንግሥት ተቋማት በተመሳሳይ የሙያ መስኮች ተመርቀው ከሚወጡ ዜጎች እኩል የሙያ ምዘና በሚደረግላቸው ወቅት በግል ተቋማት ተምረው የሚወጡት በአመዛኙ ምዘናውን አያልፉም፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያትም ሕጉ በተቋማቱ ላይ ያለው ክፍተት ነው፡፡ አብዛኞቹ ገንዘብ ተኮር በመሆናቸው ደሃው ተማሪ በመከራ አምጥቶ ለሚከፍላቸው ክፍያ ተመጣጣኝ ብቃት ስላልሰጡት ይወድቃል፡፡ እነዚህ ተቋማት ያስተማሩት ተማሪ መውደቁ አይገዳቸውም፡፡ ሌላ ተረኛ ዜጋ ይቀበላሉ፡፡ ይህን እንዲያደርጉ የረዳቸው የምንከተለው ሕግና የሕግ አስፈጻሚዎች አገራዊና ሕዝባዊ አመለካከት ማጣት ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አንድን በጤና መስክ የሚያሠለጥነውን ተቋም ለመቆጣጠር፣ ተቋሙ በሚያስተምርበት የሙያ ዘርፍ ቢያንስ አንድ ባለሙያ ሊኖረው እንደሚገባ ኤጀንሲው ይጠይቃል፡፡ በሰመመን ሰጪነት ወይም በፋርማሲ ሙያ የሚያሠለጥንን ተቋም ለመቆጣጠር ኤጀንሲው የግድ በእነዚህ ዘርፎች የሠለጠነ ባለሙያ ከሌለው፣ በርካታ ሙያን የተመለከቱ ዝርዝር ሁኔታዎችን መቆጣጠር አይችልም፡፡
ይህን ክፍተት ለመሙላት ሙያው በሚመለከተው መሥሪያ ቤት ጭምር ዝርዝርና ተከታታይ ክትትል መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ በግልም ሆነ በመንግሥት የሚሰጡ የጤና ትምህርቶችን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ተገቢውን ባለሙያዎች መድቦ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ክትትል የሚያደርግ ክፍል ሊኖረው ግድ ነው፡፡ በሌሎችም ከጤና ውጪ ላሉ የሙያ ዘርፎች የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች እኩል የክትትልና የቁጥጥር ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሌላው የመሬት ሕጉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማ መሬት ግንባር ቀደም ተጠቃሚ የሆነው የመሬቱ ባለቤት መንግሥት ነው፡፡ ከመነሻው መሬት የመንግሥት ነው ብሎ በሕግ ወስኖ የያዘው ስለሆነ፣ መሬትን እንደፈለገ ሊያደርገው ችሏል፡፡ በፈለገው ዋጋና ሀብታም በሰጠው ገንዘብ አጫርቶ ይሸጠዋል፡፡ ስለዚህም በዓለም ታይቶ በማይታወቅ ዋጋ በኢትዮጵያ አንድ ሜትር ካሬ ሲሸጥ ታዝበናል፡፡ መሸጡ ባልከፋ ገንዘቡ ለአገር ልማት ውሎ መብራት፣ ውኃና የመሳሰሉትን በአግባቡ ለሁሉም ቢዳረስ መልካም ነበር፡፡
ሁለተኛው የመሬት ሽያጭ ተጠቃሚዎች ሕገወጥ ግለሰቦች ናቸው፡፡ መሬት በመነገድ የሚገኘው ገንዘብ ግለሰቦችን እንጂ አገርና ሕዝብን ስለማይለውጥ፣ በመሬት ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለአንድ ሥራ አጥ ዜጋ እንኳ ዕድል አይፈጥሩም፡፡ ታክስ አይከፍሉም፡፡ በጨረታው ከፍተኛ ዋጋ በመስጠት ከገዙ በኋላ፣ ቦታው ላይ እሴት ሳይጨምሩ አጥረው ያስቀምጡታል ወይም ጠቀም ያለ ትርፍ ሲያገኙ መልሰው በመሸጥ ያለ ምንም ሥራ የሚኖሩ ናቸው፡፡
ሦስተኛው ተጠቃሚ ደላላ ነው፡፡ በአገራችን ስለ ደላላ ብዙ ተብሏል፡፡ ሲባባስ እንጂ ሲሻሻል ግን አልታየም፡፡ ደላላ በመሬት ሕገወጥ ዝውውር ሥራ ላይ የማይገኝበት ቦታ የለም፡፡ በመንግሥት ሥራ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች ጀምሮ እስከ ሥራ አጥ ወጣቶች ድረስ የዚህ ሥራ ተጋሪ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን የከተሞች መሬት የአልማዝ ንግድ ያህል ውድ ያደረገውም የተቀረፀው ሕግ ነው፡፡ ብዙ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ሕጋችን አገራዊ መዓዛ ይኑረው፡፡ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኘው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በኪራይ እንዲሰቃይ፣ ተወልዶ ባደገበት አገር መቶ ሜትር ካሬ ተሰጥቶት እንደ አቅሙ ቤት ሠርቶ የሚኖርበት፣ ለልጆቹ የሚያወርሰው እንጂ የማይሸጠው መሆኑ በሕግ ተደንግጎ የሚኖርበት ቤት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቤት እገነባልሃለሁ በማለት እንደ 40/60 ያለው ላም አለኝ በሰማይ የሆነ ቤት፣ አሊያም፣ ለቤት ገንቢዎችና ለማኅበራት ሲሳይ የማይሆንበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ አስቦ መሥራት እንጂ ዜጎች ተማረው አደባባይ እስከሚወጡ መጠበቅ የለበትም፡፡
አገራችን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከገባችበት ቀውስ ወጥታ ልማቷን የማስቀጠል ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም አመራሮች እየተቀየሩ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲሶቹ አመራሮች ያሉትን ሕጎች ይፈትሹ፡፡ በነበረው ከቀጠሉ ግን የለውጡ ፍጥነት እንደሚፈለገው አይሆንም፡፡ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጥቂት የማይባሉ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ይኖራሉ የሚል ተስፋ ሰንቀናል፡፡ አሳሪና አፈናቃይ ሕግ መኖር የለበትም፡፡ በየቢሮው የማያሠራ መመርያ አለ፡፡ ሕጎች ለኅብረተሰቡ ሥጋ ሰጥተው ቢላዋ የሚነሱ መሆን የለባቸውም፡፡ ደንቦችና መመርያዎች ውስብስብ መሆን የለባቸውም፡፡ ውስብስብ ሲሆኑ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር መንገድ ይከፍታሉ፡፡
እንዲህ ባለው አካሄድ ዕድገታችን በታሰበው ፍጥነትና ጥራት ሊራመድ አይችልም፡፡ ስለዚህ የተላሸች ኢትዮጵያን ለማየት ተስማሚ ሕጎችን መቅረፅ የግድ ይለናል፡፡ የማይጠቅሙንን ሕጎች በፍጥነት እንከልስ፡፡ ኢትዮጵያ የኅብረ ብሔር አገር ነች፡፡ ሁሉም ተከባብሮና ሠርቶ በሰላም የምንኖርባት አገር እንድትሆን ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህም የተጀመሩት ሥራዎች ሁሉም ሰው በአገራዊ ስሜት በመሥራት ሕዝቡም ለስኬታማነቱ ቢረባረቡ መልካም ነው፡፡
(ወልዱ ሀብተሚኤል፤ ከአዲስ አበባ)