Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

የሰሞኑ ገጠመኛችን እኔን ወደኋላ ሃያ ዓመታት መልሶኛል፡፡ ከዚያ ትውስታ ተነስቼ ወደ ሰሞኑ ጉዳይ እመለሳለሁ፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹ማርጀትህን የምታውቀው በተስፋ መኖር ትተህ በትዝታ መኖር ስትጀምር ነው፤›› የሚሉት ብሂል ለጊዜው ባይመለከተኝም፣ አንዳንድ ትዝታዎች ግን የግድ መነሳት አለባቸው እላለሁ፡፡ ለነገሩ አብዛኛዎቹ የትዝታ ዘፈኖቻችን የአድማጭን ቀልብ ይሰርቁ የለ? ስለዚህ ትዝታን ማንጎራጎር ባልችልም አንድ ሁላችንም የምናስታውሰውን ትዝታ ላካፍላችሁ፡፡

የኤርትራ መንግሥት በድንገት ባድመን መውረሩ የተነገረ ዕለት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ተነቃንቆ እንደተነሳ አይረሳንም፡፡ ምንም እንኳ ወረራው በምሽት ዜና ከመታወጁ ከሰዓታት በፊት ለፓርላማው በቀረበው ሪፖርት የአገሪቱ ወታደራዊ ቁመና አስተማማኝና ጠላትን በብቃት መመከት የሚያስችል ነው ቢባልም፣ ባድመ ላይ ወረራ ያካሄደውን የኤርትራ መንግሥት ጦር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ገትሮ የያዘው የአካባቢው ሕዝብና ሚሊሻ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ከዚያ በኋላ የዛጉ ታንኮችና መድፎች ዕድሳት እየተደረገላቸው ወደ ባድመ ሲንቀሳቀሱና ልምድ ያላቸው የቀድሞ ጦር አባላት ለዘመቻ ሲጠሩ ዓይተናል፡፡ ከዚያም የአገሪቱ ወጣቶች ከዳር እስከ ዳር ዘምተው የፈጸሙትን ገድልም እናስታውሳለን፡፡

በዚያን ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከነበሩት ተቋማት መካከል ከፍተኛ ክብርና ሞገስ የተጎናጸፈ አንድ መሥርያ ቤት ነበር፡፡ በአንዲት ታዋቂ ኢትዮጵያዊት ይመራ የነበረው ‹‹የመንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት›› ሁሌም የማልረሳው ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራን ጦርነት የየዕለቱን ሪፖርት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ሚዲያዎች በኩል ያሰራጭ የነበረው ይህ ተቋም፣ እስካሁን ድረስ መንግሥት አሉኝ ከሚላቸው እጅግ በጣም ጥቂት መንግሥታዊ ተቋማት በቁንጮነት ይጠቀሳል፡፡ እንዲህ እንደ ዛሬው ሁሉም ነገር ‹‹ሚስጥርና ድብቅ›› በሆነበት በዚያን ጊዜ፣ ይህ የመንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በኢትዮ ኤርትራ የጦርነት ዓውደ ግንባሮች የተከናወኑትን ድርጊቶች እግር በእግር እየተከታተለ ይነግረን ነበር፡፡ ከአንዳንድ ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ከሆኑ ጉዳዮች በቀር ብዙዎችን ክስተቶች በትኩሱ እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ ይኼንን ተቋም ይመሩ የነበሩት እመቤት በሠሩት ሥራ በበኩሌ ዛሬም ድረስ አመሠግናቸዋለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የላቀ ተግባር እያስታወስን የማመሥገን ባህል ቢኖረን ኖሮ እያልኩም እቆጫለሁ፡፡ ለማንኛውም በአጭሩ ትዝታዬ ይኼ ሆኖ ወደ ሰሞኑ ሁኔታ ልመለስ፡፡

ዘመኑ የመረጃ ነው፡፡ መረጃ በተቀላጠፈ መንገድ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው እንዲተላለፍ ደግሞ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ረቀቅ ያሉ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በየቀኑ እየተፈበረኩ ነው፡፡ የሞባይልና የኢንተርኔት የመገናኛ ዘዴዎች በተራቀቁ የቴክኖሎጂ ምርቶች እየተደገፉ ዘመናችን በኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ታላቅ ግስጋሴ እያደረገ ነው፡፡ ይኼንን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም መረጃን በአግባቡ መለዋወጥ ካልቻልን፣ ማዘን ያለብን በራሳችን እንጂ በማንም ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ ዘመን ለማመን እስከሚያዳግት ድረስ የተለመደውን የሚዲያ ተፅዕኖ የሚገዳደሩ ሶሻል ሚዲያዎችን እያስተዋወቀ ነው፡፡ ፌስቡክና ትዊተር የሚባሉት ሶሻል ሚዲያዎች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመረጃ ልውውጥ  እያሳተፉ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ የተካሄዱ  አብዮቶችም በቀዳሚነት መሠረት ያደረጉት እነዚህን ሶሻል ሚዲያዎች ነበር፡፡ በአገራችንም በተለይ የፌስቡክ ተገልጋዮች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው፡፡

መረጃዎች ከአንዱ ጫፍ ወደሌላኛው በፍጥነት በሚተላለፉበት በአሁኑ ዘመን፣ ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ኮሽ ሲል አዲስ አበባ በደቂቃዎች ውስጥ ይሰማል፡፡ በሶሻል ሚዲያዎቹ የሚተላለፉት መረጃዎች እንደወረዱ ስለሆኑና ብዙውን ጊዜ ግራና ቀኝ በማየት ሚዛናዊነት ስለማይታይባቸው፣ አንድ ጉዳይ አፈትልኮ ከወጣ በብዙዎቻችን ዘንድ እንደ እውነት ይቆጠራል፡፡ በብዙ አገሮች ከግላዊ ሚስጥሮች ማፈትለክ እስከ ብሔራዊ ደኅንነት አደጋዎች ድረስ የደረሱትን ችግሮች እናውቃለን፡፡ ይህ ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ ሳይቀር ሊያጋጥም የሚችል አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ ሶሻል ሚዲያ ያለውን ከፍተኛ  ጠቀሜታ ያህል አደጋውም የዚያን ያህል ነው፡፡

ከተነሳሁበት ትዝታ አንፃር ትዝብቴን ላቅርብ፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ተብሎ መረጃው ከዳር እስከ ዳር በሶሻል ሚዲያዎችና በአንዳንድ ድረ ገጾች ሲቀርብ፣ በሚመለከተው አካል ወቅታዊ የሆነ መረጃ ሲቀርብ አልተሰማም፡፡ ለአገሪቱ እንደ ‹‹ቃል አቀባይ›› የሚታየው መንግሥታዊ ተቋም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ወጣ ብሎ ያለውን እውነታ ማስረዳት ሲያቅተው ትርምስ ቢፈጠር ምን ይገርማል? በጣም ከዘገየ በኋላ በሬዲዮኖችና በቴሌቪዥን እያቃሰቱ ለማስተባበል ከመሞከር ይልቅ፣ ወጣ ብሎ ወዲያውኑ ያለውን ትክክለኛ መረጃ ለሚዲያዎች መንገር ለሕዝብ ግልጽ መሆንን ያሳያል፡፡ በበርካታ መስኮች የመንግሥት ግልጽነትና ተዓማኒነት እየወረደ በመምጣቱ የትናንት ናፋቂ ለምን እንደረጋለን?

በበኩሌ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር መራመድ ያቃተው ሥርዓት ከሚመራኝ ባልፈጠር ይሻለኝ ነበር፡፡ በዚህ ለውጥ በሚሸት ጊዜ እንኳን የተወሰኑ ሚዲያዎችን ብቻ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ማየት ያሳዝናል፡፡ እሳቸው ሚዲያው ጠንክሮ እንዲሠራ ደጋግመው ሲያሳስቡ ብሰማም፣ በተለየ ዕይታ ዘገባ የሚያቀርቡትን ግን የማግለል አባዜ በስፋት እየተስተዋለ ነው፡፡ ለውጥ እየሰበኩ የበፊቱን አሰልቺ አሠራር መድገም የመረጃ አማራጮችን መድፈን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሰሞነኛው ባድመን ለኤርትራ በሚሰጠው የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ በሙሉ መቀበል ውሳኔ ላይ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ አካል ቢኖር እኮ፣ የትኞቹ ሚዲያዎች አፋጠው እንደሚጠይቁ እናይም ነበር፡፡ እኔ በሥራ አጋጣሚ እንደታዘብኩት ከሆነ ሚዲያውን የማስተባበር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ሥራውን በመቀማቱ የሚዲያ አድልኦና መገለል በስፋት እየተደረገ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለአገር ኪሳራ ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም አጋፋሪዎችን ሳይሆን ጠንካራ ሚዲያዎች የት አሉ ብለው ይጠይቁ፡፡ እነሱንም ጠርተው ያነጋግሩ፡፡ ለውጥ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡

(ነቢያት ባዚን፣ ከአድዋ ድልድይ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ