Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክእስላማዊ ባንክ በኢትዮጵያ የሕግ መነጽር

እስላማዊ ባንክ በኢትዮጵያ የሕግ መነጽር

ቀን:

በውብሸት ሙላት

አሁን ላይ በብዙ ደርዘን የሚቆጠሩ አገሮች ሸሪዓን አክብረውና በዚሁ መሠረት ብቻ ተወስነው የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ ባንኮች ደግሞ ከዓረቡ ዓለምና ከእስላማዊ አገሮች በተጨማሪም በምዕራቡ ዓለምም ዘንድ ከታወቁና ከተለመዱ ሰነባብተዋል፡፡

ባንኮቹም ኢስላማዊ ሕግጋትን አክብረው ከየአገሮቹ አሠራር ጋር ተጣጥመው መሥራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እነዚህ ባንኮችና መሰል የፋይናንስ ተቋማት ከተለመደው የባንክ አሠራር ጋር የሚለያቸው ዋናው ነጥብ ከወለድ ነፃ የሆነ አገልግሎቶችን ብቻ የሚሰጡ በመሆናቸው ነው፡፡ በቁርዓንም ይሁን በሐዲስ ለብድር ወለድ ማስከፈል ክልክል ነው፡፡ ኃጢያትም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኢስላማዊ ሕግጋት ሰው ጥሬ ገንዘብ በማበደሩ ብቻ ሳይለፋ፣ ሳይጥር በወለድ መልክ ገቢ ማገኘት የማይገባ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች የባንክ አገልግሎት ለመስጠት እንዲህ ዓይነት ተቋማት ማደረጃት ሊሆን የሚችለው ሃይማኖቱ በሚፈቅደው መሠረት ማከናወን ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን አክበረውና ጠብቀው በባንክ መገልገል በጣም የተለመደ ሆኗል፡፡ በሌሎች አገሮች የተለመደ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ራሱን ችሎ ይህን ዓይነቱን አገልግሎት መስጠት የሚችል ባንክ መመሥረትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አልፈቀደም፡፡

የእስልምና ሕግጋትን ጠብቆ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሰባት ሺሕ የሚጠጉ ባለአክሲዮኖች ወደ 350 ሚሊዮን ገደማ በሆነ ብር፣ በተፈረመ ካፒታል ከወለድ ነፃ አገልግሎት እንዲሰጥ በመቋቋም ላይ የነበረው ዘምዘም ባንክ በምሥረታ ላይ እያለ መፍረሱን ያስታውሷል፡፡ ለመፍረሱ ዋናው ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የሆነ አገልግሎት ብቻ መስጠት የሚያስችል ባንክ ማቋቋም የማይችል መሆኑን መመርያ በማውጣቱ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የሆነ አግልግሎት የሚሰጥ ራሱን የቻለ ባንክ መቋቋምን ከከለከለ በኋላ በተወሰነ መልኩ የዜጎችን መብት ለማክበር ከወለድ ነፃ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችም በሁሉም ባንኮች በተዘጋጁ መስኮቶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ፈቅዷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ባንኮች በተለየ መስኮት ያለወለድ ገንዘብ የማስቀመጥና ሌሎች ወለድ የሌለባቸው የፋይናንስ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው የሌሎች አገሮችን ልምድ በምናይበት ጊዜ የወለድ ነፃ ባንኮች የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ባልሆኑ አገሮች ውስጥም ይሠራባቸዋል፡፡ የሚሠሩትም የሸሪዓ ሕግጋትን አክብረው ነው፡፡ በሸሪዓ ሕግ መሠረት ወለድ በጥብቅ የተከለከለ ነው ብለናል፡፡ በመሆኑም የሚቋቋሙት ባንኮች ከወለድ ነፃ የሆነ አገልግሎትን ለመስጠት ነው ማለት ነው፡፡

 አብዛኛው ምሁራን እንደሚስማማው በወለድና በአራጣ መካከል ልዩነት የለም፡፡  ወለድ እንደ አራጣ ነው የሚቆጠረው፡፡ የወለድ ዓይነቶች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዓይነታቸው ምንም ይሁን ግን ክልክል ናቸው፡፡

እስላማዊ ባንኮችን እንዲቋቋሙ መፍቀድ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት መዘርዘር ይቻላል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሦስት ብቻ እንጥቀስ፡፡ የመጀመርያው በባንክ ሥርዓቱ ውስጥ ወለድን ማጥፋት ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ ወደዚህ ዓይነት የባንክ ሥርዓት እንዲሳብ ያደርጋል፡፡ በአንድ በኩል በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ መሳተፍንና ኢንቨስት ማድረግን ያበረታታል፡፡ በሌላ በኩል በባንክ ድጋፍ ነገር ግን ያለወለድ በሚደረግ ብድር ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የባንክ ዕገዛ በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች ላይ እንዲሳተፍም ይረዳል፡፡ አሁን ላይ ባንኮቻችን የሚያበድሩት በወለድ ስለሆነና ወለድ ደግሞ ስለማይፈቀድ ያለወለድ ኢንቨስት ለማድረግ ከባንክ ብድር ለማግኘት አዳጋች ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የእምነት ነፃነትን የሚጥስ መሆኑ ነው፡፡ ማንም ሰው የመሰለው እምነት የመከተል መብት አለው፡፡ ሃይማኖቱ የሚጠይቀውን ተግባርም የመፈጸም መብት አለው፡፡ በሃይማኖቱ መነሻነትም አድልኦ አይደረግበትም፡፡ ሕጎችም ሲወጡ እነዚህን መርሆች ታሳቢ አድርጎ ነው፡፡ ያለወልድ አግልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የአገራችንን የፋይናንስ ሥርዓት ላይ የሚያመጡት ጉዳት እስከለሌ ድረስ መከልከል ተጠያቂ አይሆንም፡፡ መከልከል የእምነቱን ተከታዮች በዚህ ዘርፍ እንዳይሳተፉ መከልከል ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም በቅርበት ላጤነው ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ አድልኦ አለመፈጸምን የሚለውን ድንጋጌ ይቃረናል፡፡

ሦስተኛ ደግሞ ማንም ሰው በመረጠው የኢኮኖሚ መስክ የመሠማራት መብት እንዳለው ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ የሙስሊሙ ማኅበረሰብም አንድም በፋይናንስ ተቋማት፣ ሌላም ደግሞ ከፋይናንስ ተቋማት እንደሌላው ሰው ነገር ግን ሃይማኖቱ በሚፈቅድለት መሠረት ብድር በመውሰድ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እንዳይሠማራ እንቅፋት ይሆናል፡፡ በተለይ የማኑፋክቸሪንግ፣ የአግሮ ኢንዱስትሪና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለመሰማራት እስላማዊ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት በአገራችን አገልግሎት መስጠት መቻል አለባቸው፡፡ እነዚህ ተቋማትን ከልክሎ ሁሉም ሰው በመረጠው የኢኮኖሚ ዘርፍ መሰማራት ይችላል የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እየሆነ ነው ማለት አይቻልም፡፡

እንግዲህ እስላማዊ ባንኮች ከወለድ ነፃ የሆነ የባንክ ሥርዓት ስለሚዘረጋ በባንክ ዘርፍ ውስጥ አማራጩን ለሚፈልጉት ደንበኞች ስለሚያቀርብ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ያለ ወለድ የሚሠሩ ባንኮችን እንዲመሠረቱ ማድረጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ባንኩ ዘርፍ ያልገባውን ካፒታል  እንዲገባ ስለሚረዳም ጭምር ነው፡፡

ይህንን ካፒታል መተው ወይም እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር ለልማት እንቅፋት ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ በተቻለ መጠን ማንኛውም የማኅበረሰብ አካል፣ በአገልግሎት ሰጪነትም ይሁን ተጠቃሚነት፣ ወደ ዘርፉ መግባት አለበት፡፡ ይህ  ደግሞ የሙስሊሙን ማኅበረሰብም ያጠቃልላል፡፡

ከሌሎች አገሮች ልምድ ማየት እንደሚቻለው እስላማዊ ባንኮች ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ ልዩነት ሳይፈጥር ለማንኛውም ሰው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በመሆኑም በአገልግሎት ደረጃ ከሌላ የሃይማኖት ተከታዮች ጋርም ሊሠራ ይችላል ማለት ነው፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ ሥርዓት ማለት ሌላ አማራጭ የባንክ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ደንበኛው አማራጭ የሆነ ባንክን በመፈለግ እንደዚህ ዓይነት ባንኮች ጋር  የሚመጣበት ሁኔታም ከፍ ይላል፡፡ እንደውም ያለወለድ ኢንቨስትመንት ውስጥ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎችንም ይስባል፡፡

 በእርግጥ እስላማዊ ባንክን እንዲቋቋሙ መፍቀድ የተወሰኑ ተግዳሮቶች አይኖሩትም ማለት አይደለም፡፡

የመጀመርያው የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ዝርዝር መመርያዎችን ማዘጋት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን በፍጥነት ማዘጋጀት ቢቻል ቀጥሎ ደግሞ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማሠልጠን ያስፈልጋል፡፡

 ቁም ነገሩ ያለው ጉዳይ ሕጉን ማውጣቱ ሳይሆን ይህ ሕግ ወደ ሥራ ሲገባ በዘርፉ የሚገቡ ባንኮችን እንዴት አድርጎ መቆጣጠር ይቻላል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የሚቋቋሙትም ባንኮች ቢሆኑ የሚወጡትን ሕጎች ተረድቶ በተገቢው መንገድ ለመተርጎም አገሪቷ ያላት የሰው ኃይል ብቃት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  በአገራችን የተለመደውና በአሁኑ ወቅት አብዛኛው በዘርፉ ያሉ ባንኮች የሚሠሩበት በወለድ ላይ የተመሠረተ የባንክ አገልግሎት ያለወለድ ከሚሠሩ እስላማዊ ባንኮች እጅግ የተለየ ነው፡፡ ስለሆነም ለዚህኛው ዓይነት የባንክ ሥርዓት ብቁ ባለሙያዎች ማፍራት ግድ ይላል፡፡

በወለድ ነፃ አሠራርን በሚጠቀሙ ባንኮች ውስጥ በገንዘብ አስቀማጩም (ደንበኛውም) ሆነ በባንኩ ግንኙነት መካከል ምንም ዓይነት ተከፋይ ወለድ ስለሌለ፣ ዋነኛው የሚያስተሳስራቸው ጉዳይ የትርፍ መካፈል ጉዳይ ነው፡፡ ደንበኛው ገንዘቡን ለባንክ ሲሰጥ ስምምነቱ ባንኩ በገንዘቡ ተጠቅሞ ትርፍ እንዲያስገኝና ከትርፉ ደግሞ ለደንበኛው እንዲያካፍል ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን አሠራር ተከትሎ ለመሥራት ባንኮች ከደንበኞች ጋር ዘርዘር ያሉ ውሎችን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም በዋናነት ግንኙነታቸው በውል የሚገዛ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የትርፍ መጋራቱም በሚቀመጠው ገንዘብና በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ የሚወሰን ጉዳይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ልብ ሊሉት የሚገባው ጉዳይ ባንኩ ትርፍ ሲያገኝ ማካፈሉን ብቻ ሳይሆን፣ ኪሳራ ሲኖርም ይህንኑ ኪሳራ ከደንበኛው ጋር የመካፈሉ ጉዳይ ሊኖር ይችላል፡፡ በመሆኑም የወለድ ነፃ የባንክ ሥርዓት ውስጥ አስቀማጩ ደንበኛ ለአደጋ ተጋላጭ ነው፡፡ በተለይ ሙዳረባህ በመባል የሚታወቀውን አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ ባለገንዘቡ ማለት ነው፡፡ ይህ ከዋናው የንግድ ባንኮች (ሥርዓት) ወለድ ላይ ደንበኛውን ለመጠበቅ የተለየ ሥርዓትና ዘዴ ሊኖር እንደሚገባ ግልጽ ነው፡፡ ባንኩ ለደንበኛው ሲያበድርም ቢሆን ወለድ ስለማያስከፍል ለዚህም ቢሆን የቁጥጥር ሥርዓቱ የተለየ ይሆናል፡፡  ባንኩ ለደንበኛው ብድር ለመስጠት ቢያስብ ገንዘቡ ምን ላይ እንደሚውል አጥንቶ አዋጪነቱን መርምሮ የትርፉ ተካፋይ ቢሆን ያዋጣኛል ብሎ አምኖ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን አሁን ትርፉ እንዳለ ሁሉ ኪሳራም ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚቀረፅ የቁጥጥር መንገድ በመሆኑ፣ ከሌላው የባንክ ሥርዓት ለየት የሚል ይሆናል፡፡ ይህም የራሱ የሆነ የሠለጠነ ባለሙያ ያስፈልገዋል፡፡

ወለድ ለባንክ ህልውና ወሳኝ ነው፡፡ ወለድ ከሌለ ሌሎች ገቢ የሚያስገኙ አማራጮችን ሥራ ላይ ማዋል ይጠይቃል ማለት ነው ባንኩ ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል፡፡ ከእነዚህ ከተለመዱት ወለድ የሌላቸው የባንክ አገልግሎቶች መከካል ሙዳረባህ፣ ሙራበሃ፣ ኢጃራ፣ አል አጅር፣ ሙሻረካ፣ እስትስናእን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለያዩ ማስታወቂያዎችም ላይ በየዕለቱ እንሰማቸዋለን፡፡ ስለምንነታቸው በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡ ኢድ ሙባረክ!

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...