የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ባለአክሲዮን በመሆን ያቋቋሙት የኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ አቶ ብዙነህ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለኩባንያው ቦርድ ካቀረቡ በኋላ በብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጥሩነህ ሚጠፋ የሚመራው የኩባንያው ቦርድም ጥያቄያቸውን ተቀብሎታል፡፡
በአቶ ብዙነህና በቦርዱ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት፣ እንዲሁም ከአንዳንድ ባንኮች ኃላፊዎች ጋር ተግባብተው መሥራት ባለመቻላቸው ከኃላፊነታቸው ለመልቀቃቸው ምክንያት ስለመሆኑ ምንጮች ጠቅሰው፣ በሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ግን ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ስላበቃቸው ምክንያት የጠቀሱት ነገር ስለመኖሩ አልታወቀም፡፡ ሆኖም ቦርዱ ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱና እንዲሰናበቱ መወሰኑ፣ በመካከላቸው ተከስቷል ስለተባለው ችግር ማሳያ ነው የሚሉ አስያየቶች ተደምጠዋል፡፡
ኢትስዊች ዘመናዊ የባንክና የክፍያ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ታስቦ የተቋቋመው ሲሆን፣ ኩባንያው የሁሉንም ባንኮች የኤቲኤም ማሽኖች በማስተሳሰር የባንክ ደንበኞች በየትኛውም ባንክ የክፍያ ማሽኖች እንዲገለገሉ የሚያስችለውን አሠራር በመተግበርና በማዕከል መምራት ከሥራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ኢትስዊች ሥራ ከጀመረ ከሦስተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን፣ እስካሁን ወደ አትራፊነቱ አልተሸጋገርም፡፡
በ2009 ዓ.ም. የወጣው የኩባንያው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ 23.7 ሚሊዮን ብር መክሰሩን ነው፡፡ ኢትስዊች 18ቱንም የመንግሥትና የግል ባንኮች በአክሲዮን ባለድርሻነት በማካተት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ኩባንያ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ካፒታሉን 300 ሚሊዮን ብር ለማድረስ የቻለ የቴክኖሎጂ ፋይናንስ አገልግሎት አቅራቢ ተቋም ነው፡፡ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ለማስረጽ ተጨማሪ ዝግጅቶችን እያደረገ የሚገኘው ኩባንያው፣ አጠቃላይ የአገሪቱ ባንኮችና የደንበኞቻቸው የክፍያ ሥርዓት የሚንቀሳቀሰው በተቋሙ በኩል ነው፡፡