Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ካስቴል የዘቢዳርን 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ያቀረበውን ዋጋ ባለአክሲዮኖች አልተስማሙበትም

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዥማር ኩባንያ ባለአክሲዮኖች በዘቢዳር ቢራ ያላቸውን የ40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለካስቴል ግሩፕ (ቢጂአይ ኢትዮጵያ) ለመሸጥ ወሰኑ፡፡ ካስቴል ግሩፕ አክሲዮኖቻቸውን ለመግዛት ያቀረበላቸውን ዋጋ ግን እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡

የዥማር ሁለገብ አክሲዮን ማኅበር አባላት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄዱት ስብሰባ ወቅት፣ በዘቢዳር ቢራ ውስጥ ለያዙት የአክሲዮን ድርሻ የቀረበላቸው ዋጋ ከሚጠብቁት በታች በመሆኑ፣ የሽያጭ ዋጋው እንዲሻሻልና ለዚህም ቦርዱ ከካስቴል ግሩፕ ጋር እንዲደራደር ውክልና ሰጥተዋል፡፡

የዘቢዳር ዋነኛ ባለድርሻ የነበረው ዩኒብራ ኩባንያ 60 በመቶ የአክሲዮን ድርሻውን ለካስቴል ግሩፕ ከሸጠ በኋላ፣ ቀሪውን 40 በመቶ የዥማር ኩባንያን ድርሻ ለመግዛት ካስቴል ያቀረበው ዋጋ 1.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የዥማር ባለአክሲዮኖች ካስቴል ያቀረበው ይህ የአክሲዮን መግዣ ዋጋ አነስተኛ በመሆኑ፣ የኩባንያቸው ድርሻ እንዲሸጥ የሚደረገው ስምምነት እንዲቋረጥ አቋም ይዘው ቆይተዋል፡፡ የቀረበው ዋጋ አነስተኛ ስለመሆኑ የሚከራከሩበት ነጥብ የብር የመግዛት አቅም መዳከም በግዥው ሒደት ውስጥ ታሳቢ መደረግ ሲገባው፣ ይህ ባለመደረጉ የዥማር የቦርድ አባላት ከቀረበው በላይ ዋጋ እንዲሰጣቸው መደራደር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ካስቴል ግሩፕ የዥማርን አክሲዮኖች ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ፣ ራያ ቢራን ለመግዛት ከሰጠው ዋጋ ያነሰ መሆኑ ተገቢ አይደለም የሚሉት የዥማር ባለአክሲዮኖች፣   የአክሲዮን ዝውውሩ እንዲካሄድ ከተፈለገና ከቀረበላቸው ዋጋ በላይ እንዲሻሻል የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርሱም፣ ምን ያህል ይሁን የሚለው ግን አልተገለጸም፡፡

ካስቴል ግሩፕ 40 በመቶን የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ በተናጠል ሲታይ፣ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለውን አንድ አክሲዮን በአራት ሺሕ ብር ለመግዛት ዋጋ እንዳቀረበ ያመላክታል፡፡ ይህ ዋጋ ግን በቂ ካለመሆኑም በላይ፣ ካስቴል ራያ ቢራን ከገዛበት ዋጋ አኳያ ዝቅተኛ መሆን አልነበረበትም የሚል ክርክር ቀርቧል፡፡ ካስቴል የራያ ቢራን አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን በሰባት ሺሕ ብር ለመግዛት ተስማምቶ የአክሲዮን ዝውውሩ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ካስቴል ግሩፕ በዥማር ባለአክሲዮኖች ፍላጎት መሠረት ለአክሲዮኖች ግዥ ያቀረበውን የገንዘብ መጠን በማሻሻል ዘቢዳር ቢራን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቅለል ቁርጠኛ ስለመሆኑ እስካሁን ለማወቅ ባይቻልም፣ የዥማር ቦርድ አመራር ግን ከካስቴል ጋር ድርድር ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች