Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለንግዱ ኅብረተሰብ በአንዴ የቀረቡት 21 ረቂቅ የታክስ መመርያዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎች ጉምሩክ ባለሥልጣንና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ባልተለመደ አኳኋን 21 ረቂቅ መመርያዎችን በማሰናዳት ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

ሰኔ 5 እና 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ውይይት ከተደረገባቸው ረቂቅ መመርያዎች መከካል 11ዱ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል የቀረቡ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ረቂቅ መመርያዎችም በባለሥልጣኑ ለውይይት የቀረቡ ነበሩ፡፡ ከ21 መመርያዎች ውስጥ ስድስቱ አዳዲስ መመርያዎች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመመርያዎች ላይ የንግዱ ኅብረተሰብ እንዲወያይና ረቂቆቹን እንዲመለከታቸው የተሰጠው ጊዜ ከአንድ ሳምንት ያነሰ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም በቂ ዝግጅት ሳይደረግባቸው ለምክክር የቀረቡ የሕግ ሰነዶች እንደሆኑበት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ገልጿል፡፡ መመርያዎቹ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ‹‹የታክስ አስተዳደራዊ ቅጣት አነሳስ መመርያ›› በሚል ርዕስ የቀረበው ረቂቅ አንዱና በነጋዴው በኩልም ትኩረትን ካገኙት ውስጥ ተጠቃሹ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ የታክስና የግብር መቀጫ ይነሳልኝ አቤቱታ ሲቀርብለት ወይም በራሱ አነሳሽነት በታክስ ከፋዩ ላይ የተጣለውን አስተዳደራዊ ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ሊያነሳ እንደሚችል በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ውስጥ ስለመደንገጉ የረቂቁ መግቢያ ያወሳል፡፡ ታክስ ከፋዮች በተለያዩ ምክንያቶች ግዴታቸውን በሕግ በተቀመጠው አግባብ መወጣት ባለመቻላቸው ሳቢያ የሚጣልባቸው አስተዳደራዊ ቅጣት፣ ታክሱን ለመክፈል ፈቃደኛ ሆነው ሲገኙ ቅጣቱ ካልተቃለለ በስተቀር የመክፈል አቅማቸው እንደሚዳከም ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አስተዳደራዊ ቅጣቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማንሳት ታክስ ከፋዮች ወደፊትም ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ በታክስ ከፋይነት እንዲጓዙ ለማገዝ እንደሚረዳቸው ታምኖ የተሰናዳ ረቂቅ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር የረቂቅ ሕጉ መዘጋጀት ውዝፍ የፍሬ ግብር እንዲከማች ከመተው ይልቅ በወቅቱ ለመሰብሰብ አጋዥነቱ ስለታመነበት፣ አስተዳደራዊ ቅጣቶች የሚነሱበትን መሥፈርት በማውጣት ፍትሐዊ አሠራር ማስፈን አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ለረቂቅ ሕጉ መዘጋጀት እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ውስጥ ይመደባሉ፡፡   

በታክስ አስተዳደር አዋጁ መሠረት ግብር ከፋዩ ላይ የተጣለ አስተዳደራዊ ቅጣት፣ የድርጊቱ መፈጸምአለመፈጸም በታክስ አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ መሠረት በማድረግና የተለያዩ የሥጋት ደረጃዎችን መነሻ በማደርግ ቅጣቱ በከፊል የሚነሳበትን አሠራር እንደሚያሰፍን ታምኖበታል፡፡ የቅጣት አነሳሱ የሚወሰነው ግን እንደ ቅጣት ዓይነቱ በደረጃ ተከፋፍሎ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ የቅጣት ዓይነት መሥፈርቶችም በመመርያው ተመልክተዋል፡፡  

የተጣለባቸው መቀጫ በከፊል ይነሳላቸዋል ተብለው በየደረጃው በዝርዝር ከቀረቡት የግብር ከፋዩ ችግሮች ውስጥ፣ ከምዝገባና ስረዛ ጋር የተያያዘ ቅጣት፣ ከታክስ ከፋይነት  መለያ ቁጥር ጋር የተገናኘ ቅጣት፣ የታክስ ማስታወቂያ ዘግይቶ ማቅረብ፣ ታክስን ዘግይቶ መክፈል፣ ለተጨማሪ እሴት ታክስ አለመመዝገብና ላልተመዘገበበት ጊዜ ታክስ ከመከፈል ጋር የተያያዙ ቅጣቶችና የመሳሰሉት በከፊል የሚነሱበትን ዝርዝር ጉዳይ መመርያው ይዟል፡፡ ታክስን አሳንሶ ማሳወቅ፣ የኤሌክትሮኒክስ የታክስ ሥርዓትን አለመከተል፣ በታክስ ወኪል ላይ የሚጣል ቅጣት፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከመጠቀም ግዴታ ጋር የተያያዙ ቅጣቶች፣ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የአገልግሎት ማዕከል ጋር የተያያዙ ቅጣቶች፣ ለባለሥልጣኑ መረጃ ባለመስጠት የሚጣሉ ቅጣቶች፣ በዝቅተኛ ሥጋት ደረጃ የሚታዩ ሆነው የታክስ ዕዳቸው የተከፈሉበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ቅጣታቸው በከፊል የሚነሳላቸው ጥፋቶች ስለመሆናቸው ተዘርዝሯል፡፡

 ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ተቀንሶ ከሚከፈል ታክስ ጋር የተያያዘ ቅጣት፣ የታክስ ደረሰኝ አለመስጠት፣ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ወይም ሶፍትዌር አቅራቢ ድርጅት ጋር የተያያዙት ቅጣቶች ደግሞ በመካከለኛ ሥጋት ደረጃ እንደሚመደቡ የሚጠቅሰው መመርያው፣ የእነዚህ ቅጣቶች መነሻ የታክስ ዕዳው የተከፈለበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ ከፊል ቅጣቱ ሊነሳላቸው እንደሚችል በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

ተገቢ የሒሳብ ሰነዶችን አለመያዝ፣ ትክክለኛ ያልሆነ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መስጠት፣ ታክስ በመሸሽ የሚጣል ቅጣት በከፍተኛ ሥጋት ደረጃ የሚመደቡ ጥፋቶች ሲሆኑ፣ የታክስ ዕዳው የተከፈለበትን ጊዜ መሠረት በማድረግ፣ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የነበረውን የግብር ግዴታ ባለመወጣት የሚጣል ቅጣትም በረቂቁ በዝርዝር በቀረቡት የሥጋት መሥፈቶች መሠረት ሊነሱ ስለሚችሉባቸው ጉዳዮች አካቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር ረቂቅ ሕጉ አስተዳደራዊ ቅጣትን በልዩ ሁኔታ ማለትም ‹‹በኢኮኖሚያዊ፣ በአስተዳደራዊ ወይም በማኅበራዊ ምክንያቶች የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይም በሚወክለው ኃላፊ በልዩ ሁኔታ በታክስ ከፋዩ ጥያቄ ወይም ባለሥልጣኑ በራሱ አነሳሽነት አስተዳደራዊ ቅጣት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲነሳ ሊደረግ ይችላል፤›› በማለት ጠቅሷል፡፡

ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይም ለሚወክለው ኃላፊ የቅጣት ውሳኔው በሙሉ ወይም በከፊል እንዲነሳ የሚቀርብ አቤቱታ ላይ የውሳኔ ሐሳብ በአገር ውስጥ ታክስ አሠራርና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት በኩል እንዲቀርብበት ከተደረገ በኋላ፣ የቀረበው ምክንያት አሳማኝ ሆኖ ሲገኝ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይም የሚወክለው ኃላፊ የተጣለው አስተዳደራዊ ቅጣት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲነሳ ውሳኔ የማስተላለፍ ሥልጣን እንደሚኖረው ረቂቅ ሕጉ ይጠቅሳል፡፡

በመመርያው መሠረት የማይነሳ አስተዳደራዊ ቅጣት ስለመሆኑ የተመለከተው፣ የታክስ ባለሥልጣኑ በሕግና በውክልና በሚሰበስባቸው የከፍተኛ ትምህርት የወጪ መጋራትና የጡረታ መዋጮ ክፍያ ግዴታዎችን ባለመወጣት የሚጣሉ መቀጫዎች ግን በአዲሱ መመርያ አግባብነት ሊነሱ ወይም ቀሪ ሊደረጉ አይችሉም፡፡

ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሶ እንዲያደርግ ግዴታ የተጣለበት ሰው ይህን ግዴታ ባለመፈጸሙ የተጣለበት ቅጣት፣ ታክስ ከፋዩ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብር ቀንሶ ለሚያስቀረው ሰው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩን ባለማቅረቡ የተጣለ ቅጣት፣ በመመርያው የማይነሱ ቅጣቶች ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ረቂቅ መመርያው ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ተቀባይነት አግኝቶ የታክስ ክፍያ የጊዜ ማራዘሚያ ስምምነት ውስጥ ገብቶ የታክስ ዕዳውን በመክፈል ላይ የሚገኝ ግብር ከፋይ ላይ የተጣለ አስተዳደራዊ ቅጣት ስለሚነሳበት ጉዳይ በነባሩና ሥራ ባለው መመርያ መሠረት ፍጻሜ እንደሚያገኝ ረቂቁ ያመለክታል፡፡

እንዲህ ካሉት ረቂቅ መመርያ በተጨማሪ 20 ረቂቅ መመርያዎችና አዳዲስ መመርያዎች ውይይት እንዲደረግባቸው ተደርጓል፡፡ ሆኖም በአንድ ጊዜ ከቀረቡት የረቂቅ ሕጎች ብዛት አኳያ፣ መመርያዎቹን በቅጡ ተረድቶና ተመልክቶ አስተያየት ለመስጠት ያልተቻለበት መድረክ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ መመርያዎቹ በአንድ ጊዜ ለውይይት እንዲቀርቡ መደረጋቸውም በነጋዴው በኩል የሚነሱ ሥጋቶችን ማዕከል በማድረግ በቂ ጊዜ ወስዶና አብላልቶ ሐሳብ ለመስጠት እንዳላስቻለም ተገልጿል፡፡ ከዚያ በላይ መመርያዎቹ በሰፈሯቸው አንቀጾች ላይ ሐሳብ ለመስጠት፣ የሚሻሻሉና የሚለወጡ ቢኖሩ በእነሱ ላይ ለመወያየት የተሰጠው ጊዜ ከአንድ ሳምንት ያነሰ መሆኑ ቅሬታ አስነስቷል፡፡

በሁለት ቀኑ የውይይት መድረክ ላይ ከቀረቡት ረቂቅ መመርያዎች ውስጥ የታክስ ከፋይነት ምዝገባና የአፈጻጸም መመርያ፣ የታክስ ወኪልነት ፈቃድ አሰጣጥ መመርያና የታክስ ግዴታን በመወጣት ስለሚሰጥ የምስክር ወረቀት መመርያ፣ የራስ ታክስ ስሌት አፈጻጸም መመርያ፣ ያልተከፋፈለ ትርፍ ላይ የሚጣል ግብርን ለማስፈጸም የወጣ መመርያ፣ የደረሰኝ አስተዳደር መመርያ፣ የቅድመ ግብር ክፍያ ሥርዓት አፈጻጸም መመርያ፣ የታክስ ክፍያ ማራዘሚያ መመርያና ከገቢ ግብር ነፃ የተደረጉ ገቢዎች አፈጻጸም መመርያ ከዋና ዋናዎቹ መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች