Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አድማጭነት የባለሥልጣኑ የለውጥ ጅምር

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎችና የንግዱ ኅብረተሰብ ለውይይት በተገናኙ ቁጥር ጭቅጭቅና ንትርክ መነሳቱ የተለመደ ክስተት ነው፡፡ በአግባቡ ለመደማመጥ የማይችሉባቸው አጋጣሚዎችም በርካታ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም እንደታየውም በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈጠረው አታካሮ ባለሥልጣኑና የንግዱ ኅብረተሰቡን ሆድና ጀርባ ያደረጉ መድረኮችም የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው፡፡ በተለይ ከጉምሩክ አሠራርና ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ችግሮችን ለመቅረፍ በንግዱ ተዋንያን የሚቀርቡለትን ሐሳቦች ባለሥልጣኑ ካለመቀበሉም በላይ ከኃላፊዎች አልፎ አልፎ የሚደመጠው ማስፈራሪያም ለመቃቃራቸው ምክንያት እንደነበር ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡

በጥቅሉ አንዱ ሌላውን በዓይነ ቁራኛ በጥርጣሬ የሚያይበት፣ ለዘመናት የቆየ የአዳኝና ታዳኝ ግንኙነት ውስጥ በመቆየታቸው፣ ከዚህ በኋላም ሁለቱ ወገኖች የሚገናኙበት አጋጣሚ ከተፈጠረ፣ የእሮሮና የእንኪያ ሰላንቲያው ልውውጥ እንደተመለደው ይቀጥላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ቢኖር አያስገርምም፡፡ ያሉትን ችግሮች በቀላሉ ተነጋግሮና ተግባብቶ ከመፍታት ይልቅ ይህንን ተቀበል፣ ይህንን ፈጽም የሚለው የአንድ ወገን አስገዳጅ አካሄድ መኖሩም ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ያለመተማመኑ ጉዳይ ዳርቻ የሌለው ነበር፡፡

ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከባለሥልጣኑ አሠራር ጋር በተገናኘ ችግር ገጥሞናል ያሉ የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ደጀን በማድረግ ከባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ በመድረኩ የታየው ድባብ ግን ከቀደመው ጊዜ የተለየ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የውይይት መድረኩ የተጠራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የንግዱ ኅብረተሰብ አሉብኝ ያላቸውን ችግሮች በተናጠል እንደመከረባቸው ባሳሰቡት  መሠረት ነበር፡፡ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከባለሥልጣኑ አሠራር ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሞናል ያሉ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ለንግድ ምክር ቤቱ በማቅረብ፣ ንግድ ምክር ቤቱም እነዚህን ጥያቄዎች አጠናክሮ ከባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ይሁን እንጂ ንግድ ምክር ቤቱ ችግራቸውን በመዘርዘር አቤቱታዎችን ያቀረቡ ነጋዴዎችን አደራጅቶ በውይይት አሳትፏል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች ባሻገር በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎችም ተጨማሪ ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ ዕድል ማግኘታቸው፣ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችም በርካታ ጥያቄዎች እንዲቀርቡ መጋበዛቸው፣ ከድቀድሞው ጊዜ ይልቅ ጆሮ መሰጠት እንደጀመሩ ያሳያል፡፡ ችግሬን አድምጡ ለሚለው የንግዱ ኅብረተሰብ ጥያቄና ውትወታ ምላሽ በመስጠት አለኝ የሚላቸውን ነጥቦች ሁሉ ማዳመጥ መቻል መልካም ጅምር ነው፡፡

በዚህ ውይይት ወቅት የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች እያንዳንዱን ጉዳይ ተመልክተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የባለሥልጣኑን ውሳኔ ባይገልጹም፣ የንግድ ኅብረተሰቡን ችግሮች በዝርዝር ለማወቅ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ በርካታ ጥያቄዎችን ያቀረቡት የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት በግማሽ ቀን ውስጥ በተደረገ ስብሰባ ወቅት ጉዳያቸው በሙሉ እንደሚገባው ይታይላቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የውይይት መድረኩ ድባብ ጤናማ መሆኑ በበጎ ሊታይ የሚገባው ጅምር ነበር፡፡ ሊለመድና ሊዘወተር የሚገባው የመደማምጥና የመግባባት መድረክ ነበር፡፡ የተጠበቀው ያህል ምላሽ ባይገኝበትም፣ በተናጠል ምላሽ ለሚገባቸው ጉዳዮች በአግባቡ መልስ እንሰጣለን የሚል ተስፋ መሰጠቱም ተግባብቶ ለመሥራት ያለውን የመንግሥት አካሄድ ያሳየ የለውጥ ጅምር ሊሆን ይችላል፡፡

በምክክሩ የቀረቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቃል መገባቱ መልካም ነው፡፡ የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ግን መረጃ ተመሳክሮ የቀረበባቸውን የግብር ከፋዩን ጉዳዮች እንደተባለው በተናጠል ዓይቶ ተገቢው ውሳኔ ሲሰጥ ነው፡፡ ከምክክር መድረኩ መንፈስ መረዳት እንደተቻለው፣ ከግብር አሰባሰብና ከጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር የአንድ ወገን ብቻ እንዳልሆነ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች በዚህ ተማምነዋል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድና ፈጣን ምላሽ መስጠት ውጥረቱን ያረግበዋል፡፡ በሌላ በኩል ግብር ከፋዩ የጥያቄው ትክክለኛነት አረጋግጦ መቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በተቀመጠው ሕግ መሠረት በአግባቡ ሊስተናገድ ካልቻለ ይህንን የሚያሳይና የሚያረጋግጥ መረጃ በመያዝ መብቱን ማስጠበቅ ይገባዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላም ቢሆን ባለሥልጣኑ ባዘጋጃቸው ረቂቅ መመርያዎች ዙሪያ ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር መምከሩም የበጎ ጅምር ምልክት ነው፡፡ 21 አዳዲስና ነባር ረቂቅ መመርያዎች ማሻሻዎችን አካተው የሚተገብሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ በውይይቱ የንግዱ ኅብረተሰብ እንዲመክርበት መደረጉ ባልከፋ ነበር፡፡ ችግሩ ግን ይኼንን ሁሉ ረቂቅ በአንድ ጊዜ በጥቂት ቀናት ውስጥ ዓይታችሁና መርምራችሁ እንምከርበት ማለቱ ሱሪ በአንገት ነው፡፡ ከልብ የንግድ ኅብረተሰብ እንዲመክርበትና ግብዓት ሊሆን የሚችል ሐሳብ እንዲያቀርብ  ከተፈለገ፣ ሁለቱንም የሚያግባባ የጊዜ ሰሌዳና ቀነ ቀጠሮ ይዞ መነጋገርና የቀረቡትን ረቂቆችም በሚገባ አሽቶና አዳብሮ ማቅረብ በተቻለ ነበር፡፡ ይህ አሠራር ባይለመድ ይመከራል፡፡ በአንድ ጊዜ እንደ ጎርፍ የቀረቡት ረቂቅ ሕጎች አሁንም ውይይት እንደሚያሻው እንዳለ ሆኖ፣ መመርያዎቹ ይፅደቁ ከተባለ ግን አጠቃላይ ይዘታቸውን በሚመለከት ግብር ከፋዩ በቂ መረጃዎች ሊያገኝባቸው ይገባል፡፡

ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም እንደማስፈጸሚያ የሚጠቀምባቸው መመርያዎች፣ ሰርኩላሮችና ሌሎች በርካታ አሠሮችን የሚከተል በርካታ ሕግጋትን የሚተገብር ከመሆኑ አንፃር፣ አዳዲሶቹ ድንጋጌዎች ሲተከሉ ሊፈጠር የሚችለው ብዥታ ቀላል አይሆንም፡፡ ሕጎቹን ከመተግበሩ በፊት፣ ግብር ከፋዩ ስለመመርያዎቹ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣ መመርያዎችን ለመተግበር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ እንቅፋት እንዳይገጥም ይረዳል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት