Wednesday, April 17, 2024

የሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጀቶች የተናጠል ስብሰባና ውሳኔዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስና በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ያሳለፋቸውን ሁለት መሠረታዊ ውሳኔዎች ተከትሎ፣ የግንባሩ ሦስት ፓርቲዎች በተናጠል በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች ተሰብስበው የሚመሩትን ክልልና አገራዊ ሁኔታዎች በመገምገም ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡

የተናጠል ስብሰባቸውን ያካሄዱት ደኢሕዴን፣ ኦሕዴድና ሕወሓት ሲሆኑ፣ ደኢሕዴንና ኦሕዴድ ያካሄዱት ድርጀታዊ ጉባዔ ነው፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ባካሄዱት ድርጅታዊ ጉባዔ የየፓርቲያቸው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ሕወሓት ያካሄደው ስብሰባ ግን የፓርቲው ሁለተኛ የሥልጣን አካል በሆነው በሕወሓት ምክር ቤት ደረጃ ነው፡፡

ሦስቱ ፖርቲዎች ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት የፈጀ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን፣ በቀዳሚነት ድርጅታዊ ስብሰባውን አጠናቆ ይፋዊ መግለጫ ያወጣው የደቡብ ክልል ብሔራዊ ድርጅት ደሕዴን ነው፡፡

የደኢሕዴን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጉባዔ የተካሄደው ከግንቦት 29 ቀን እስከ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ ‹‹መደባዊ ትግሉን በማጠናከር ክልላዊ እንድነታችንን ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግራለን›› በሚል ርዕስ ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው በክልሉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የፓርቲውን ውስጠ ዴሞክራሲ በተመለከተና በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በተወሰኑት ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንደነበር መግለጫው ያመለክታል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ባካሄደው ስብሰባ የአገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት ይቻል ዘንድ የአገሪቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ተቋማት የሆኑትን ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በሙሉና በከፊል ለመሸጥ መወሰኑ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እልባት ሳያገኝ የቆየውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ሲባል የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቀበሉን፣ ለተግባራዊነቱም ለኤርትራ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡ የበርካታ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ትኩረት በአግራሞት የሳበ ነበር፡፡

በዚህ ውሳኔ ላይ በተናጠል የተወያየው የደኢሕዴን መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ድርጅታዊ ጉባዔ፣ ‹‹የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ማነቃቂያ የፖሊሲ ማሻሻያ ሐሳቦች አገራችን አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተግባብተንበታል፤›› በማለት በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በማስከተልም በኢሕአዴግ ደረጃ የተወሰኑትን የፖሊሲ ማሻሻያ ውሳኔዎችንና በአገሪቱ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን ተከትሎ እየመጣ የሚገኘውን ሰፊ የሕዝብ መነቃቃት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ ለላቀ ክልላዊና አገራዊ አንድነት እንዲሁም የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራትን ለመፈጸም እንዳሚተጋ አስታውቋል፡፡

‹‹በመሪ ድርጅታችን ኢሕአዴግ የሚመራው ልማታዊ መንግሥታችን በአገራችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጋር ተያይዞ ባለው ጉዳይ፣ በቅርቡ የወሰነውን ውሳኔ እኛም የደኢሕዴን አመራሮች ተቀብለን ከድርጅቶቻችንና (ኢሕአዴግ) ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚጠበቅብንን ሁለ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን፤›› ሲል አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ደኢሕዴን ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውን የአቋም መግለጫ ተከትሎ፣ ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል ብሔራዊ ድርጅት የሆነው ኦሕዴድ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ድርጅታዊ ጉባዔ የውይይት አጀንዳዎችንና በኮንፍረንሱ የተወሰኑ ውሳኔዎችን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የኦሕዴድ የከፍተኛና የመካከለኛ አመራሮች ድርጅታዊ ጉባዔ በመሠረታዊነት በክልሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ እንደነበርና የፓርቲው የታችኛው መዋቅር አመራር ከጎጠኝነት አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ አለመላቀቁን፣ ይህም በክልሉ በሚኖሩ ሕዝቦች አብሮነት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን በመገምገም ችግር የታየባቸው አመራሮች ላይ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን፣ ይህ ተግባርም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመግባባት ላይ መድረሱን የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

የኦሕዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያላት ሕገ መንግሥታዊ ጥቅም እንዲከበር የተጀመረው ሥራ እንዲጠናከር፣ እንዲሁም የኦሮሚኛ ቋንቋ ከአማርኛ ጎን ለጎን የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ቀደም ብሎ የተላለፈው ውሳኔ ትኩረት ተሰጥቶበት እንዲሠራም መግባባቱ ተገልጿል፡፡

በኦሕዴድ የአመራሮች ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩ የሪፖርተር ምንጮች በበኩላቸው፣ በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፋቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች የውይይት አጀንዳ እንደነበሩና ተሳታፊዎችም በሙሉ ድምፅ ለውሳኔዎቹ ድጋፋቸውን በመስጠት ምላሻቸውን እንዳሳወቁ ተናግረዋል፡፡

የደኢሕዴንና የኦሕዴድ ድርጅታዊ ኮንፈረንሶች ከተጠናቀቀ በኋላ ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ የተደረገው ደግሞ፣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች የያዘ መግለጫ ነው፡፡

የሕወሓት መግለጫ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ያለው መሆኑን፣ እንዲሁም በኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራርና በአጠቃላይ በግንባሩ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ የማፈንገጥ አዝማሚያ እየታየ እንደሚገኝ፣ ይኼንንም ለመቀልበስ እንደሚታገል የሚገልጽ ነው፡፡

ይህ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫው በኦሕዴድና በደኢሕዴን ከተሰጡት መግለጫዎች በይዘቱ በእጅጉ የተለየና በገዥው ፓርቲ ውስጥ ፖለቲካዊ አለመግባባት ስለመኖሩ የሚጠቁም ሲሆን፣ የበርካታ የፖለቲካ ልሂቃንን ቀልብም በአትኩሮት ስቧል፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎች ይዘት

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰኔ 3 ቀን እስከ ሰኔ 5 ቀን 2010 ባካሄደው ስብሰባው ትኩረት አድርጎ የተወያየው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፋቸውን ሁለት ውሳኔዎች አስመልክቶ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀረበለት ሪፖርት ላይና በክልላዊና በአገራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎችን በሚመለከት እንደሆነ መግለጫው ያመለክታል፡፡

በሁለቱም የመወያያ አጀንዳዎች ላይ በዝርዝር እንደተወያዩ የሚገልጸው መግለጫው፣ በሁለቱም የውይይት አጀንዎች የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራርና ራሱ ግንባሩ ከመሠረታዊ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር እየሸሸ በመሆኑ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መውጣት አለመቻሉን ይገልጻል፡፡

‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን አገራችንን ከጥፋት የታደገ፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠበት፣ አዲሲቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ያደረገና ለወደፊትም የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ መሆኑ የእስካሁኑ ትግላችን ያረጋገጠው እውነት ነው፤›› የሚለው መግለጫው፣ ‹‹ይህ ተዓምር የፈጠረ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤› ይላል፡፡

ይኼንን አሳሳቢ ችግር መነሻ በማድረግ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች መገምገሙን የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ በቅድሚያ ለውይይት ይገባ የነበረው የኢሕአዴግ ምክር ቤት በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በኢሕአዴግ ውስጥ በግልጽ እየታየ የመጣውን መሠረታዊ የአመራር ብልሽት ያስከተለውን ጉዳት፣ እንዲሁም የተጀመረው በጥልቀት መታደስ የደረሰበት ደረጃን በመገምገም በአገሪቱ ዋነኛ ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ ማየት አለመቻሉ አንድ መሠረታዊ ጉድለት መሆኑን በዋናነት ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል የኢሕኣዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአገሪቱን ግዙፍ ተቋማት ሙሉ በሙሉና በከፊል ለመሸጥ ከመወሰኑ በፊት ማየት የነበረበት አሁን አገሪቱን ለገጠማት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ መሆን ሲገባው፣ ችግሩ ባስከተላቸው ውጤቶችና ለጊዜያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ መስጠቱ ተጨማሪ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የፈጸመው ሌላ ጉድለት መሆኑን ያትታል።

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን በግልጽ የለያቸውን የልማት አቅሞቻችን ማለትም መላው ሕዝባችን፣ መንግሥትና የግል ባለሀብቱን በማደራጀት ርብርብ እንዲያደርጉ ያለመቻላችን ችግር ላይ ትኩረት ስጥቶ መውያየት አልቻለም፤ሲል ይወቅሳል። የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያና የኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ የወሰነው ውሳኔ በመሠረቱ ሕወሓት ቀድሞም ቢሆን የሚያምንበትና ለአካባቢው ሰላም ወቅታዊ ውሳኔ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ግን ጥንቃቄን የሚጠይቅ መሆኑን አመልክቷል።

 “አፈጻጸሙን በሚመለከት ግን አገራችን ከሌሎች ጎረቤት አገሮች የገጠሟትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲቻል ዘለቄታዊ መፍትሔ ከማበጀት አንፃር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ጉድለት ነበረበት፤›› ብሏል፡፡ ‹‹የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሆኑት መካከል ቴሌ፣ኤሌክትሪክ ማመንጨዎች፣ ሎጂስቲክስና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛው ድርሻ በመያዝ የግል ባለሀብቶችን ለማሳተፍ፣ እንዲሁም የቀሩትን የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ የወሰነው ውሳኔ ከግንባሩ ፕሮግራማችንና ፖሊሲዎቻችን ጋር የማይጋጭ፣ ባለፉት ጉባዔዎቻችን እየተወሰነ የመጣና ወቅታዊ ነው፤›› በማለት እንደሚቀበለው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ገልጿል።

በኢትዮ ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ጉዳይም ሆነ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያየዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢሕአዴግ ምክርቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበትና የሚመለከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያዩበት እንደ መጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለሕዝብ ይፋ መደረጉን፣ ሌላው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ጉድለት እንደሆነም ወቅሷል።

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተወያየበት ሁለተኛ አጀንዳ ወቅታዊ ክልላዊና አገራዊ ሁኔታዎችን የተመለከተ መሆኑን መግለጫው ያስረዳል። በኢሕአዴግ ደረጃም ሆነ በሕወሓት ደረጃ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በልማታዊ መስመሩና በሕገ መንግሥቱ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ሲገምግም ቢቆይም፣ ችግሮቹ በመቀጠላቸው የችግሮቹ ስፋትና ትርጉም በኢሕአዴግ ደረጃ በጥልቀት መገምገም እንዳለበት ወስኗል። ችግሩን ለመታገል መወሰኑንም በመግለጫው ይፋ አድርጓል።

በዴሞክራሲ ኃይሎችና በጥገኝነት መካከል የሚደረገው ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ በዋናነት በዴሞክራሲና በልማት ዙሪያ በሚለኮስ ንቅናቄ ማኅበራዊ መሠረታችንና ከልማታችን ተጠቃሚ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት የተደራጀ ትግል ነው። ይህን ለማድረግ እንዲቻል መላው ሕዝባችንና አባላችን የምንገኝበትን መድረክ ባህሪ መነሻ በማድረግ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በአገር ደረጃ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ትግል በቁርጠኝነት እንዲረባረብ፤ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

በአሁኑ ወቅት በኢሕአዴግ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የኢሕአዴግን ሕገ ደንብና ተቋማዊ አሠራር ያልተከተሉ የአመራር ምዳባዎች እንዲታረሙ፣ ለሕወሓት ነባር አመራሮች ዕውቅና እንዲሰጥም የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥያቄውን በይፋ አቅርቧል። የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚገባ መልስ የሰጠባቸው የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን ፈዴራላዊ ሥርዓቱን በመፃረርና የሕዝብን ክብር በሚነካ መልኩ በኃይልና በተፅዕኖ የትግራይን ሕዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ እየተደረጉ ያሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ከሕዝቡ ጋር በመሆን በፅናት እንደሚታገልም አስታውቋል። ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ በፍጥነት ለማየትና ለመገምገም እንዲቻልም፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጠይቋል፡፡

ብአዴን እስካሁን ስብሰባም ሆነ ድርጅታዊ ጉባዔ አላካሄደም፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ብአዴንም በቅርቡ ስብሰባ እንደሚቀመጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -