120ኛው የዓድዋ ድል በዓል፣ የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ በተገኙበት ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ አርበኞች፣ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ሹማምንትና የአዲስ አበባ ኅብረተሰብ ተገኝተዋል፡፡ ፎቶግራፎቹ ሥነ በዓሉን ያሳያሉ፡፡ (ፎቶ በመስፍን ሰሎሞን)
*****
እኔና ጨረቃ
እኔና ጨረቃ
ተጓድነን
ወጥተን፣
ልንደምቅበት አደባባዩን
ቀን በቀን
ሽተን፣
ተመለስን፤
እነፀሓይን አድንቀን
ባይሆንልን
ጨለማውን እየተመኘን፡፡
- ደበበ ሰይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ (የብርሃን ፍቅር ቅጽ ፪)›› (1992)
******
በርበሬና ጨው
አንድ ሰውና አንዲት ሴት አብረው ሲኖሩ “አንጢሹ” የሚባል ልጅ ነበራቸው፡፡ የስሙም ትርጉም ማስነጠስ ማለት ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ዘመድ ጥየቃ ለመሄድ ፈልገው ልጃቸው እቤት ተኝቶ እንዲቆይ ነገሩት፡፡
በሚቀጥለው ቀን ልጁ የቤቱን በር ሳይዘጋ ተኛ፡፡ ታዲያ አንድ ጅብ በቤቱ አጠገብ ያልፍ ነበርና የተከፈተውን በር አይቶ ወደ ቤቱ ውስጥ ሲገባ የተኛውን ልጅ ስላገኘው ወደ ጫካ ይዞት ሄዶ መሬት ላይ ሲያስቀምጠው ልጁ ነቃ፡፡
ልጁም ጅብ እንደወሰደው ባወቀ ጊዜ “ያለ በርበሬና ጨው ነው የምትበላኝ?” አለው፡፡
ጅቡም “በርበሬና ጨው የለኝም፡፡” አለ፡፡
አንጢሹም “እኔ ከቤቴ አመጣልሃለሁ፡፡” ሲለው ጅቡም በዚህ ስለተስማማ ልጁ ግን ወደቤቱ ተመልሶ ሄዶ በርበሬና ጨው ይዞ ከመመለስ ይልቅ በሩን ዘግቶ ተኛ፡፡
ጅቡም ልጁ እንደማይመለስ ሲያውቅ ወደ ልጁ ቤት መጥቶ “አንጢሹ፣አንጢሹ!” እያለ ሲጣራ አንጢሹም “አሁን መሽቷል፡፡ አትረብሽኝ፡፡” አለው፡፡
ጅቡም “በርበሬና ጨው አመጣለሁ ብለህ ለምን አታለልከኝ” ሲለው አንጢሹ “እግዜር መክሮኝ ነው፡፡” አለው ይባላል፡፡
- ተራኪው የማይታወቅ የትግራይ ተረት
****
የ114 ዓመት ደብዳቤ
ይድረስ ከቢትወደድ ኢልግ
የነገርከኝ የቁንጫ መድኃኒት በስሃን አድርገን ብንሞክረው የሚያልቀው ቁንጫ እጅግ በጣም ጉድ ነው፡፡ አንተው እንዳልከው እውነተኛ መድኃኒት ሆነ፡፡
መስከረም 7 ቀን አዲስ ዓለም ከተማ ተጻፈ 1894 ዓ.ም.
******
ይድረስ ከአባ እንድርያስ፡፡
እጅግ የሚጣፍጥ ኦራንጅ በዘውገ እጅ የላኩልኝ ሁለት አገልግል ደረሰልኝ፡፡ ለዓርብና ለሮብ በቃኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡
መስከረም 7 ቀን አዲስ ዓለም ከተማ ተጻፈ 1895 ዓ.ም.
(ሁለት አገልግል የተባለው ሁለት ካርቶን ነው፡፡ ልጅ ዘውገም በጂቡቲ የምኒልክ ጉዳይ ፈጻሚ ነበሩ)
- ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› (1984)
******
እንዲያው በንዲያው
- ጠያቂ፡- ባለበግ በዘንጉ እየነካ
- መላሽ፡- አይሸጥም ለዘንግ
- ጠያቂ፡-ምን ይላል
- መላሽ፡- ባ
- ጠያቂ፡- የት ያደገ ነው
- መላሽ፡- እጋጥ
- ጠያቂ፡- ምን ያራል
- መላሽ፡- በጠጥ
- ጠያቂ፡- ምነው ይኸ ጠማማ
- መላሽ፡- ቀንድ ነዋ አለና አበሸቀው ይባላል፡፡
- መሸሻ ግዛው ‹‹እርስ በርሳችን በወፎች ቋንቋ ንግግራችን›› (1949)
*****
የ19 ዓመቷ ቢልየነር
ለብዙዎች ቢልየነር መሆን ምኞት ሲሆን የሚሳካላቸው ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ በተለይ በወጣትነት ዕድሜ ቢልየነር መሆን የማይታሰብ ነው፡፡ ሆኖም የ19 ዓመቷ ኖርዌጅያዊት በዓለም የመጀመሪያዋ ወጣት ቢልየነር ተብላለች፡፡
አሌክሳንድራ አንደርሰን ቢልየነር ለመባል የበቃችው ከአባቷ ባገኘችው ውርስ ነው፡፡ ታላቋ የ20 ዓመቷ ካትሪናም የውርሱ ተጋሪ ናት፡፡
እ.ኤ.አ. በ2007 በኖርዌይ ኦስሎ ኢንቨስተር የሆነው አባታቸው ጆሃን አንደርሰን ከፈርድ ሆልዲንግ ካምፖኒው የ42.2 በመቶ ድርሻው ያወረሳቸው ሲሆን፣ እህትማማቾቹ በነፍስ ወከፍ የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ሆነዋል፡፡ ሆኖም አንደርሰን በዓለም የመጀመሪያዋ ወጣት ቢሊየነር በሚል የቢልየነሮች ዝርዝር የተካተተችው በ2016 ነው፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣ የ19 ዓመቷ አንደርሰን በፈረስ ግልቢያ ውድድር የታወቀች ናት፡፡ ብዙ ጊዜዋን የምታሳልፈውም ከፈረሷ ጋር ነው፡፡ ሦስት ጊዜም ተሸላሚ ሆናለች፡፡ አሁን ላይም የቤተቧን ካምፓኒ በቅልጥፍና ከመምራት ይልቅ፣ ትኩረቷ የፈረስ ግልቢያ ላይ ነው፡፡ በ2015 ለዩሮድሬሴጅ በሰጠችው ቃለምልልስ፣ ‹‹በሕይወት ዘመኔ በመሉ የምፈልገው ፈረስ ጋላቢ መሆን ነው፤›› ብላለች፡፡