Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዩኒቨርሲቲዎቻችንና የተማሪዎች መመረቂያ ጽሑፍ

ታዋቂው ፈላስፋ አርስጣጣሊስ የትምህርትን ጠቀሜታ ሲገልጽ፣ “ትምህርት በፍሰሐ ዘመን ጌጥ፣ በመከራ ዘመን መጠለያ፣ በእርጅና ዘመን ደግሞ ምርኩዝ ናት፤” ሲል ነበር ያብራራው፡፡ ትምህርት ለአንድ ግለሰብ ያለውን ፋይዳ በጉልህ ሲያስረዳ የተጠቀመው አባባል ነው፡፡ ትምህርት ከግለሰባዊ ፋይዳው ባሻገር አገራዊ ሚናውም ጉልህ ነው፡፡ ትምህርት የዕድገት መሠረት ነው፡፡ አንድ አገር በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ አውዶች የተሻለ ባህሪ እንዲኖራት ትምህርት ዋነኛውን ሚና ይጫወታል፡፡ ለዚህ ነው ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ መንግሥታት ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ ይሰጡ እንደነበር የምንረዳው፡፡

ለምሳሌ በአገራችን ከአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው እንረዳለን፡፡ ከዓለማዊ ትምህርት ጀምሮ እስከ 1908 ዓ.ም. የመጀመሪያው የመንግሥት ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ላይ መከፈት፣ ከሚሲዮን ትምህርት ቤቶች እስከ 1925 ዓ.ም. ተፈሪ መኮንን ተብሎ እስከ ተሰየመው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ ያለውን ጊዜ ስናስብ፣ የቀደሙት መንግሥታት ለትምህርት ይሰጡት የነበረውን ትኩረት እንገነዘባለን፡፡

በእርግጥ በዚህ ወቅት ወጣቱን በጥናትና ምርምር ተሳታፊ በማድረግ የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱ ትኩረት ተደርጎ ሳይሆን፣ ገዥዎች በደንብ የሠለጠነ የሰው ኃይል ሳይኖር አጥጋቢ የሆነ የመንግሥት አስተዳደር ሊኖር እንደማይችል በመገንዘብ ነበር ትምህርት እንዲስፋፋ ያደርጉ የነበረው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከመንግሥት አስተዳደር ሥርዓታቸው ጎን ለጎን ዘመናዊ ኢትዮጵያን ለመገንባትም ትምህርት ሌላኛው ዓላማ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ለዚህም በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት የገቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዋናነት ግን በአፄ ምንሊክና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የትምህርት ዋና ዓላማ ከመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አክትሞ የአምባገነኑ የደርግ መንግሥት ሲተካ የተለየ የትምህርት ፖሊሲ ይከተል እንደነበር እንረዳለን፡፡ የመሠረተ ትምህርት ፖሊሲ አርሶ አደሩንና ያልተማረውን ማኅበረሰብ ማንበብና መጻፍ እንዲችል በር ከፍቶ ነበር፡፡ ይህ ፖሊሲ ደርግ ሥልጣን ከወጣ ለጥቂት ዓመታት ያህል የተተገበረ ቢሆንም፣ የማታ ማታ ግን ወደ ወታደራዊ ትምህርት ማዘንበሉ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ ደርግ ይገልጽ እንደነበረው አገሪቱ በወታደራዊ አቅሟ ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ልቃ እንድትገኝ እንጂ፣ መሠረተ ሰፊ የሆኑ የኅበረተሰቡን ችግሮች በትምህርት መፍታት እንዳልነበር እንገነዘባለን፡፡

የዚህ መንግሥት ከቀደሙት መንግሥታት ልዩ የሚያደርገው ለወታደራዊ ትምህርቶች ይሰጠው በነበረው ልዩ ትኩረት ነው፡፡ አገሪቱን የዘመናዊ ወታደር ባለቤት ማድረግና እንደሊቢያው ጋዳፊ ዝናውን በዓለም ማስነዛት ነበር፡፡

የደርግ መንግሥት መጨረሻ ላይ እንደ ሶቭየት ኅብረት ተንኮታኩቶ ሲፈርስ፣ በእግሩ የተተካው የኢሕአዴግ መንግሥትም የራሱን የትምህርት ፖሊሲ ይዞ ብቅ አለ፡፡ “ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” (Quality Education for All) በሚል መርህ የትምህርት ፖሊሲውን የነደፈው ኢሕአዴግ፣ ካለፉት መንግሥታት የተሻለ ዕመርታ አስመዝግቧል፡፡ ለምሳሌ ያህል በሁሉም አካባቢዎች የትምህርት ተቋማትን ከመገንባት ባሻገር ሁሉም ዜጋ በተለይ ወጣቱ የተማረ፣ ንቁና ተመራማሪ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል እየተጫወተም ነው፡፡

ለዚህም ማሳያ የሚሆኑትን ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት አንድ ወይም ሁለት ብቻ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎችን ዛሬ ከሰላሳ በላይ ከፍ ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ዋና ዓላማ ተማሪዎች ተመራማሪና አዲስ የፈጠራ ሥራ ባለቤት ሆነው አገሪቱ ያሉባትን ችግሮች እንዲፈቱ፣ ብሎም የአዳዲስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለቤት እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኢሕአዴግ በትምህርት ላይ ከቀደሙት መንግሥታት የተሻለ አቅጣጫና ትኩረት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ዋና ዓላማ ይህ ቢሆንም ቅሉ አሁን ላይ እየሄዱበት ያለው አሠራር ግን ከዓላማቸው ጋር የሚጣረዝ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች መገንዘብ እንችላለን፡፡ በአብዛኛው ነባር ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች አሠራራቸው ጊዜው ከሚጠይቀው መንገድ ያፈነገጠ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ እንገደዳለን፡፡ በዓመት የሚጠቀሙት በጀትና የሚያስገኙት ጥቅም (ጥቅሙ የጥናትና ምርምሩ ውጤት የአገሪቱን ችግር መፍታት ሲችል የሚገኘው ውጤት ነው) ሲመዘን የራሱ የሆነ ጉዳት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ለዚህ ማሳያ ሊሆነን የሚችለው አንዱ ጉዳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዙሪያ ያሉ “የመመረቂያ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንሠራለን” የሚሉ ድርጅቶችና ግለሰሶች መበራከት ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከበጀት ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በየጥጉ እየተፈለፈሉ ከዛሬ ዓመትና ከዚያ በፊት የተሠሩ የመመረቂያ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን በማባዛት ለአዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ጠቀም ባለ ገንዘብ የሚቸበችቡ ናቸው፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ከመመረቂያ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማባዛት ለአዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ጠቀም ባለ ገንዘብ የሚቸበችቡ ናቸው፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ከመመረቂያ ጹሑፋቸው ርዕስ ጀምሮ ሙሉ ጽሑፉን በአንዴ ይገዛሉ፡፡ በአማካሪያቸው ትዕዛዝ መሠረት ርዕስ፣ ፕሮፖዛል ከዚያም ረቂቅ የጥናት ጽሑፋቸውን በየተራ ያስገባሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተጠናቆ ለአገራችን አንድ አዲስና ልዩ ነገር እንደሠሩ ተቆጥሮ የምረቃ የምስክር ወረቀታቸውን ከዩኒቨርሲቲያቸው ያገኛሉ፡፡   

ሌላ ማሳያ ላንሳ፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓመት የተሠራ መመረቂያ ጽሑፍ በዚህ ዓመት ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ወይም ወለጋ ዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ሲሆን ማየቱ እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አሁን አንድ ድርጅት ከዛሬ ሦስት ዓመት ጀምሮ በአገራችን ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ተማሪዎችን የመመረቂያ ጽሑፍ ቢሰበሰብና ምን ያህሉ የመመረቂያ ጽሑፎች ተመሳሳይነት እንዳላቸው ቢያረጋግጥ፣ ይህ መኮራረጅ ሥር የሰደደ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ለማለት የተገደድሁት ባለፈው ጊዜ የአክስቴ ልጅ ለዕረፍት ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እኔ ዘንድ መጥቶ የነበረ ጊዜ የነገረኝን ጉዳይም አባሪ በማድረግ ነው፡፡

የ2008 ዓ.ም. የአንድ ዲፓርትመንት ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ በአንድ ወቅት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሠርተውት የነበረው የመመረቂያ ጽሑፍ እንደነበር ከእሱ ለመረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ በዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ምን ያህል ዓላማቸውን እንደሳቱ እንረዳለን፡፡ በዚህም የተነሳ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ከመታዘብ ባለፈ “ዓላማቸውን የሳቱና የአገራችን ንብረት የሚበዘብዙ ተቋማት” ብዬ ለመጥራት ተገድጃለሁ፡፡ በውስጣቸው በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ይዘውና በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በዓመት እየከሰከሱ፣ አንድ ወሳኝና ችግር ፈቺ የሆነ የመመረቂያ ጽሑፍ በአገር ደረጃ አለመገኘቱ የትምህርቱን ሥርዓትና ተቋማቱን እንድንኮንን እንገደዳለን፡፡

ማሳረጊያ

ዩኒቨርሲቲዎች በመቶና በሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በዓመት ወጪ እየተደረገባቸው የሚገኙ ተቋማት በመሆናቸው የቆሙሉትን ዓላማ ማሳካት አለባቸው፡፡ ዓለም የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስ ዋነኛ መሰላሎቻችን ሊሆኑ የሚችሉት ዩኒቨርሲቲዎቻችን በመሆናቸው፣ አገራዊ ግዴታቸውን በተገቢው ሁኔታ መወጣት አለባቸው፡፡ ወጪ ቆጣቢ አሠራሮችን በመከተልና ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን በመቅሰም የሚታይ ለውጥ ማሳየት አለባቸው፡፡ የተማሪዎቻቸውን የመመረቂያ ጽሑፍ አዲስ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ከሌላ ዩኒቨርሲቲ ያልተኮረጀ መሆኑን ሊያረጋግጥ የሚችል አሠራር መከተል አለባቸው፡፡

በአንድ ዓመት የሚመረቁ ተማሪዎች የመመረቂያ ርዕስና ረቂቅ የመመረቂያ ጽሑፋቸው በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ተመዝግቦ፣ ለመኮራረጅ በማያመች አሠራር ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተደራሽ የሚሆንበትን ዘዴ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችን ያሉ አንዳንድ ሕገወጥ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ አለባቸው፡፡

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡   

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles