Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዳያስፖራው በባህልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት

ዳያስፖራው በባህልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት

ቀን:

ኢትዮጵያውያንና የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው መጥተው በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግሥት እያበረታታ ነው፡፡ ለዳያስፖራዎች ትኩረት በመስጠት ለኢንቨስትመንት የተመቻቸ መንገድ እንደተፈጠረም ይነገራል፡፡ የዳያስፖራዎች ቀን በማክበር፣ በየክልል ከተሞች የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ቢሮ በማቋቋም፣ ዳያስፖራዎችን ለመሳብ ጥረት ይደረጋል፡፡ በተለያየ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ላይ ለተሰማሩ ዳያስፖራዎች የሚደረግ የመንግሥት ማበረታቻ እንዳለ ሆኖ ባለሀብቶቹ ውጣ ውረዶች እንደሚገጥሟቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከዘርፎቹ አንዱ ባህልና ቱሪዝም ነው፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ዳያስፖራ ኢንቨስተሮች መንግሥት ወደ አገራቸው ተመልሰው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያቀርብ የገባላቸውን ቃል ሙሉ በሙሉ አልጠበቀም ሲሉ ይተቻሉ፡፡ በተለይም ሆቴልና አስጐብኚ ድርጅት በመክፈት አገሪቱ ውስጥ እየሠሩ ያሉ ዳያስፖራዎች በርካታ እንቅፋቶች እየገጠሟቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በሳሬም ሆቴል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይም ቅሬታዎቹ ተቀንፀባርቀዋል፡፡

መድረኩ የተዘጋጀው በአገሪቱ በባህልና ቱሪዝም ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማመላከትና የዳያስፖራዎችን ምልከታ ለመቃኘት ነው፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ዳያስፖራዎችም የሚገጥሟቸውን ችግሮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ አብርሃም ሥዩምና አቶ የተማረ አወቀ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር አባላት ናቸው፡፡ ዳያስፖራዎች አገር ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርጉ የሚገጥሟቸውን ውጣ ውረዶች ይናገራሉ፡፡ አቶ አብርሃም እንደሚሉት፣ ዳያስፖራዎች በማንኛውም ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ ሲደረግ የሚነገራቸውና መሬት ላይ ያለው ይለያያል፡፡ በዋነኛነት የሚጠቅሱት ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በጉምሩክ የሚገጥማቸውን ውጣ ውረድ ነው፡፡ ለአስጐብኚ ድርጅት መኪና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞክሩ ጉምሩክ ላይ በተፈጠረ ውጣ ውረድ መኪናቸው ከጥቅም ውጪ የሆነባቸው ኢንቨስተሮችን እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡

ብዙ ዳያስፖራዎች ሌሎች ቅሬታዎቻቸውንም ይዘው ቢሯቸውን እንደሚያንኳኩም ገልጸው፣ ለዳያስፖራዎች ማበረታቻ ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡ አቶ አብርሃም ‹‹መንግሥት ለዳያስፖራው የሚሰጠው ተስፋና ነባራዊ ሁኔታው መናበብ አለበት፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ዳያስፖራዎችን ለኢንቨስትመንት ሲቀሰቅስ ቢያበረታታቸውም ገንዘባቸውን አውጥተው ሥራ ከጀመሩ በኋላ መጓተት ይገጥማቸዋል፡፡ ይህም ሌሎች ዳያስፖራዎችን ተስፋ እንዳያስቆርጥ ይሰጋሉ፡፡

ዳያስፖራዎች በክልል ከተሞች ኢንቨስት ሲያደርጉ የበለጠ ችግር እንደሚገጥማቸው በደብረ ማርቆስ ከተማ በሆቴል ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ሰለሞን ሽፈራው ይናገራሉ፡፡ እሳቸውና ሌሎችም በክልሎች ሆቴል ያላቸው ዳያስፖራዎች በዋነኛነት የሚጠቅሱት የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላትን ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይልና የኢንተርኔት ሽፋን ውስንነት በሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውና አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ የእነዚህ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለመሆን ንድፈ ሐሳብ ሲያቀርቡ ቶሎ ምላሽ እንደማይሰጥም ያክላሉ፡፡ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ ቦታዎች በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የመሠረተ ልማት አለመሟላት በቱሪዝሙ ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖም ይጠቀሳሉ፡፡

የሶማሌ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልናስር መሐመድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የዳያስፖራዎች ማኅበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽንና ኢሚግሬሽን መካከል ቅንጅት ቢኖር ለችግሮቹ መፍትሔ ለማግኘት እንደሚቀል ያምናሉ፡፡

ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ ሀብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ኢንቨስትመንት ያለው ጠቀሜታ ግልጽ ነው፡፡ ለኢንቨስትመንት የተመቻቸ ሁኔታ አልተፈጠረም ሲባል ግን የዳያስፖራዎችን ውጣ ውረድ ከሌላው ባለሀብት በተለየ የሚያዩት አሉ፡፡ አቶ ከበደ ሌሌማ አስጐብኚ ድርጅት አላቸው፡፡ ከገንዘብ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኢንቨስተሮች የተመቻቸ አካሄድ እንዲፈጠርላቸው መጠየቅ ተገቢ ቢሆንም፣ ከሌላው ባለሀብት የተለየ አሠራር ይፈጠር ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዳያስፖራ በመሆናችን የተለየ ነገር ይደረግልን አይባልም፡፡ ሁሉም እኩል እየሠራ ችግሮቹ ይፈቱለት፤›› ይላሉ፡፡

ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መቀስቀስ ብቻ ሳይሆን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ቢሮክራሲ መቀረፍ እንዳለበት፣ ዳያስፖራዎች ስለሚገጥሟቸው እንቅፋቶች ቅሬታ ለማቅረብ ወደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ወይም የመሥሪያ ቤቱ የክልል ቢሮዎች ሲሄዱ በአግባቡ እንዲስተናገዱም ያሳስባሉ፡፡

በተያያዥም በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በሆቴልና በአስጐብኚ ድርጅት ብቻ መገደብ እንደሌለባቸው ዳያስፖራዎቹ ይናገራሉ፡፡ ለግዠሪ ፈርኒቸር አፓርትመንትና ቡቲክ ሆቴልን የመሰሉ በሌላው ዓለም የተለመዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች በኢትዮጵያም እንዲስፋፉ ይጠይቃሉ፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ የኢንቨስትመንት ማነቆ የሆነው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ውስንነት የአገሪቱ አጠቃላይ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየመጣ መሆኑንም ያክላሉ፡፡ የአገሪቱ ቅርሶች ብዙ መሆንና በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የባህልና ትምህርት ማዕከል መዝገብ መስፈር ብቻ የቱሪስቶችን ቁጥር እንደማይጨምር ሚኒስትር ዲኤታዋ ይናገራሉ፡፡ የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጪዎች መጠናከር ቱሪስቶችን እንደሚስብና የቆይታ ጊዜያቸውን እንደሚያረዝም ይገልጻሉ፡፡

ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት ረገድ በቂ ማበረታቻ እንደማይደረግላቸው ያቀረቡትን ቅሬታ በተመለከተ፣ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ከቀረጥ ነፃ ቁሳቁሶችን እንዲያስገቡ በመፍቀድና በሌላም መንገድ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ማበረታቻዎች ሲደረጉ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል፡፡ ከቀረጥ ነፃ አገልግሎትን ከቱሪዝም ጋር ግንኙነት ለሌላቸው ነገሮች የሚጠቀሙ እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ የገቡ ቁሳቁሶችን ከገቡበት ዓላማ ውጪ የሚያውሉ መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ጄኔራል አቶ ሚካኤል ጦቢያስ፣ ኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጭ ውጭ አገር ለሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሰጠው መረጃ የተሟላ ነው ለማለት እንደማይደፍሩ ይናገራሉ፡፡ የመረጃውን ክፍተት ለመሙላት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ወቅት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

የዳያስፖራውን ችግር ለመፍታት በየአካባቢው ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙበት አጋጣሚ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ መሰል የመልካም አስተዳደር ችግሮች የአገሪቱ አጠቃላይ ተግዳሮት እንደሆኑና ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከወ/ሮ ታደለች ጋር ይስማሙበታል፡፡

በባህልና ቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን መስመር ለማስያዝ የዳያስፖራ ፖሊሲ ተረቋል፡፡ ፖሊሲው የዳያስፖራዎችን መብትና ጥቅም የማስከበርና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት አገሪቱን ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ እንዳለው አቶ ሚካኤል ይናገራሉ፡፡ ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ለማበረታታት ከምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ አሠራሩን የሚያቀሉ መንገዶች እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ ዳያስፖራዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ፖሊሲው ያለውን ሚናም ያብራራሉ፡፡ ዳያስፖራዎች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲናገሩ፣ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳያስፖራዎች የተሰበሰበውን ገንዘብ እንደ ምሳሌ በመውሰድ ነው፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህልና ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ካሳ በዘርፉ ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭ በስፋት እንዳልተሠራበት ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶች ያለገበያ ፉክክር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉን ገበያ፣ የገበያ ትስስር፣ የገዢዎችን ፍላጎትና ገበያ ላይ የሚቀርቡ ምርቶችን የጥራት ደረጃ የሚያውቁት ዳያስፖራዎች በዘርፉ ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚነቱ ይሰፋል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ችግሮች ሲቀረፉ ከቱሪስት መዳረሻዎች፣ የእደ ጥበብ ውጤቶችና የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚገኘው ጥቅምም ያድጋል፡፡ አገሮች በባህልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...