Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ሊፍት››?

‹‹ሊፍት››?

ቀን:

እንደወትሮው ተማሪውም ሆነ ሠራተኛው ወደየመስመሩ ለመጓዝ ከቤቱ ወጥቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለዳ፡፡ ከተማው ግን ፀጥ እረጭ ያለ ነው፡፡ ፀጥታው በባዕላት ዕለት ወይም ቅዳሜና እሁድ ላይ ከሚስተዋለውም ለየት ያለ ይመስላል፡፡ በአስፋልት መንገድ ላይ የሚንቀሳቀስ ታክሲ አይታይም፡፡ ምክንያቱ ሁሌም በመንገድ ላይ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ታክሲዎች (ሚኒባስ) የትሪፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 208/2003 ተግባራዊ መሆንን ተከትሎ በዕለቱ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ነበር፡፡ በእግር መጓዝን፣ አልፎ አልፎ የሚመጡ ታክሲዎችን ተስፋ አድርገው የተሰለፉ ሰዎችን መቀላቀልን ምርጫቸው ያደረጉ ነበሩ፡፡ ያሰቡት ቦታ መድረስ የማይታሰብ እንደሆነ አምነው ከቤት እቤት የተመለሱም ነበሩ፡፡ የቤት መኪናዎችን ሊፍት በመጠየቅ እያቆራረጡ ካሰቡት የደረሱም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡

በእንደዚህ ዓይነት የታክሲ እጥረት በሚያጋጥምባቸው ጊዜያት ባለመኪኖች ሊፍት ለመስጠት ይበልጥ ፍቃደኛ፤ እግረኞችም ለመጠየቅ የሚደፍሩ ቢሆንም ሌላ ጊዜ አሽከርካሪውም በቀላሉ ሊፍት አይሰጥም፡፡ ተጠቃሚው እግረኛም በቀላሉ አይጠይቅም፡፡ ሊፍት ልስጥ የሚል ተሽከርካሪ ከፊቱ ገጭ ሲልም እንኳ ለመግባት የሚያቅማማ ጨርሶም ከቆመበት ንቅንቅ የማይል ብዙ ነው፡፡ ይህ በሁለቱም በኩል ያለው ነገር የተለያዩ ነገሮችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በጥቅሉ ግን ፍራቻና ጥርጣሬ የወለደው ነው ሊባል ይችላል፡፡ 

አንዳንዶች ሊፍት የሚሰጡት ለአቅመ ደካሞች ብቻ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ለነፍሰጡሮች ወይም ሕፃን ለያዙ እናቶች ብቻ ነው፡፡ ጊዜ መርጠው (ከጠዋትና ከማታ በስተቀር) ለማንም ለጠየቃቸው ሊፍት የሚሰጡ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ለዚህ ወይም ለዚያ ሳይሉ እንደስሜታቸው ለመሰላቸው መኪናቸውን የሚያቆሙ ያጋጥማሉ፡፡ አራስ ልጅ የያዘች ሴት በጭራሽ እንደማይጭኑ የነገሩንም አሉ፡፡

ለአራት ዓመታት አሽከርክሯል፡፡ ያለም ስንታየሁ በአንድ የማስታወቂያና ሕትመት ድርጅት በሾፌርነት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ አቅመ ደካሞችን ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሰዎች ተቸግረውም ቢሆን ሊፍት አይሰጥም፡፡ ሕፃን ልጅ ለያዙ እናቶች ግን መኪናውን ያቆማል፡፡ ቢሆንም በእግሩ መሔድ የጀመረ ሕፃን ለያዙት እንጂ ልጃቸውን በእቅፋቸው ላደረጉ በጭራሽ አያቆምም፡፡ ‹‹አሽከርካሪ ከመሆኔ በፊት ከሰዎችና ከሬዲዮ የሰማኋቸው ነገሮች እንድፈራ አድርገውኛል›› የሚለው ያለም ጨቅላ ሕፃን ለታቀፉ እናቶች እንዳያቆም ያደረገውንና ከዓመታት በፊት በሬዲዮ የሰማውን ታሪክ ያስታውሳል፡፡

ምንም እንኳ ያን ያህል በሚያዝናና ሁኔታ ውስጥ ያልነበረው አሽከርካሪ ሕፃን አቅፋ ታክሲ በብዛት በማይቆምበት ቦታ ላይ ለቆመችው እናት መኪናውን አቆመ፡፡ አመስግና ገባች፡፡ ጥቂት እንደሔዱ ፈራ ተባ እያለች ይቅርታ ጠይቃ ዳይፐር በመርሳቷ መግዛት እንዳለባት ለዚህም ሱፐር ማርኬት ደጃፍ እንዲያቆምላት ለመነችው፡፡ ምንም ሳያንገራግር ልክ ሱፐር ማርኬት እንዳገኙ አቆመላት፡፡ ደቂቃዎች ተቆጠሩ፡፡ ጨቅላውን መኪና ውስጥ ትታ የወረደችው እናት አልተመለሰችም፡፡ የደቂቃዎች ማለፍ ተመለሰች አልተመለሰች ስለሚለው ብቻ ሳይሆን ወደ አየር መንገድ እየተጓዘ የነበረውን አሽከርካሪ የበረራ ሰዓቴ ደረሰ አልደረሰ የሚል ጭንቀት ውስጥም ከትቶት ነበር፡፡ እናትየው አልተመለሰችም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሔድ ከቤት የወጣው አሽከርካሪ እንዳሰበው ሳይሆን ነገሮች ፈጽሞቀ ከሚያስበው ውጭ ሆነው ሕፃኑን ይዞ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አመራ፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ የሚሆንባቸው ጊዜአትም ጥቂት ላይባሉ ይችላሉ፡፡ በተቃራኒው ለ19 ዓመታት ያሽከረከረ የሁለት ልጆች አባት ደግሞ ሕፃን ልጅ ላቀፉና ለነፍሰ ጡሮች ሳይጠይቁት ሁሉ መኪናውን ያቆማል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ለማንም ሊፍት ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም፡፡

አቶ ያዕቆብ ወልደማርያም ይባላሉ፡፡ አዛውንት ናቸው፡፡ ለዓመታት መኪና አሽከርክረዋል፡፡ አንዳንዴ ትንንሽ ጉዳዮችን ለመከወን ለመንቀሳቀስም በማሰብ በእግራቸው ይሔዳሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ዓመት ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ እግረኛ ሆነው ሲንቀሳቀሱ ሊፍት በሰጣቸው አሽከርካሪ መዘረፋቸውን በእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ጽፈው ነበር፡፡ የሆነው እንደሚከተለው ነበር፡፡

ከቤታቸው አቅራቢያ ከሚገኝ ዳቦ መጋገሪያ (ሸዋ ዳቦ) ዳቦ ለመግዛት በእግራቸው ይሔዳሉ፡፡ ጊዜው በከተማዋ ዳቦ ቤቶች ዳቦ በቀላሉ የማይገኝበት ወቅት ነበር፡፡ ከዳቦ ቤቱ ዘልቀው ዳቦ አጥተው ተመልሰው ወጡ፡፡ ተመልሰው የሚሔዱትን መንገድ ቆም ብለው እየተመለከቱ ሳለ ወዲያው ከዚህ ነው ያላሉት አንድ ሰው መጥቶ መኪና መያዙንና በአቅራቢያው ካለ ሌላ ዳቦ ቤት እንደሚያደርሳቸው ገልፆላቸው፣ በር ከፍቶላቸው ከኋላ ተቀመጡ፡፡ ሀምሳ ሜትር እንደሔዱ አሽከርካሪው ለሌላ እግረኛ አቆመ፡፡ እግረኛው ገብቶ አጠገባቸው ተቀመጠ፡፡ ይህ ሰው እውነትም ሊፍት የተሰጠው ሳይሆን የአሽከርካሪው የተሽከርካሪ ላይ ስርቆት ባልደረባ ነበር፡፡ አቶ ያዕቆብ ይህን የተረዱት ኋላ ላይ ነበር፡፡ በመጨረሻ ሊፍት ልስጥዎት ብሎ በክብር የመኪና በር ከፍቶ ባስገባቸው አሽከርካሪ የወርቅ የጣት ቀለበታቸውን ተዘርፈው ከመኪናው ወረዱ፡፡  

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ሊፍት በመሰጠት የተለያዩ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ ይናገራሉ፡፡ ወንጀሉ የሚፈፀመው ደግሞ በአሽከርካሪዎችም በተሳፋሪዎችም ነው፡፡ ‹‹ሊፍት በሰጠን ወንድ ተደፈርን የሚሉ ያጋጥማሉ፡፡ የተጫኑት ሁለት ወንዶች እንደዚህ በሚሆኑበት ጊዜ ለመርዳት ብሎ የጫነን ሾፌር የማፈንና አስገድዶ ወደሌላ ቦታ በመውሰድ የመዝረፍ ነገር ያጋጥማል፡፡ ሊፍት ተሰጥቷቸው የአሽከርካሪውን ሞባይል ስልክና ገንዘብ ሁሉ ይዘው የሚወርዱ አሉ›› የሚሉት ኢንስፔክተሩ ብዙዎቹ ድርጊቶች የሚፈፀሙት ብዙ እንቅስቃሴ በማይኖርበት ምሽትና ማለዳ ላይ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

በምትኖርበት ሰሚት አካባቢ በማንኛውም ቀን ሊፍት መስጠት መጠየቅም የተለመደ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ሰኞ የከተማ ታክሲዎች ሥራ የማቆም አድማ መተው በነበረበት ዕለት ደግሞ ብዙ አሽከርካሪዎች ታክሲ ባለመኖሩ ተቸግሮ መንገድ ላይ የፈሰሰውን እግረኛ በደንብ ይረዱ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ነበር እሷም ከሰሚት ቦሌ ቢሮዋ የደረሰችው፡፡

ለእሷና ለአንዲት እናት ሊፍት የሰጧቸው ሴት አሽከርካሪ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ እግረኛን መርዳት እንደሚገባ ቢያምኑም አንዳንዱ ሰው አጋጣሚውን ተጠቅሞ ዕቃ ሠርቆ ስለሚወርድ፣ የሚሰማው ሌላ ሌላ ወንጀልም ስለሚያስፈራ ብዙ ጊዜ ዝም ብሎ መሔድን እንደሚመርጡ አሽከርካሪዋ ገለጹ፡፡ ከጐኗ የተቀመጡት እንደ እሷ ሊፍት የተሰጣቸው እናትም አደገኛ አሽከርካሪዎች መኖራቸውን፤ ከአንድ አጋጣሚያቸው ወዲህ በጣም አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልገቡ በስተቀር ሊፍት እንደማይጠይቁ፤ ሳይጠይቁ ሲያቆሙላቸውም ለመግባት ፍቃደኛ እንደማይሆኑ አወሩ፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው አጋጣሚ አዝኖልኝ አደረገው ያሉት አሽከርካሪ መኪናውን ያቆመላቸው ሁኔታቸውን ተመልክቶ ሊዘርፋቸው አስቦ እንደሆነ በማወቃቸው ነው፡፡ ከሾፌሩ አጠገብ የተቀመጠ ሌላ ሰው ነበር፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ ይህ ሰው ብር ጠፋኝ ብሎ መኪናውም ይፈተሽ እሳቸውም እንዲሁ አለ፡፡ በነገሩ ግራ ተጋቡ፡፡ ተፈተሹ ምንም የተገኘ ነገር የለም፡፡ በዚህ መካከል አሽከርካሪው ያልሆነ ዓይነት ነገር ሲያሳይ፣ ብር ጠፋኝ ባዩም እጅ እጃቸውን (ቀለበት) ሲያይ አስተዋሉ፡፡ ይህን ጊዜ ነገሩ ገባቸውና አቁሙልኝ ብለው ወረዱ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሊፍት ላለመጠየቅ የወሰኑት፡፡ ሰኞ ዕለትም ሁኔታው አስገዳጅ በመሆኑና አሽከርካሪዋም እንደሳቸው የተጫነችውም እግረኛ ሴት በመሆኗ ነበር ለመሳፈር የወሰኑት፡፡

ብዙዎች አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልገቡ በስተቀር በተለይም ምሽት ካልሆነ ሊፍት አይጠይቁም፡፡ አሽከርካሪዎች ሲያቆሙላቸውም አይገቡም፡፡ ብዙ መሆናቸው ምቾት ሰጥቷቸው ምሽትም ቢሆን ብዙ ሳያንገራግሩ ከቆመላቸው መኪና ውስጥ እንደሚገቡ የሚናገሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል እንደሁኔታው ሲጠይቁም፣ ለመግባት ፍቃደኛ ሲሆኑም የአሽከርካሪዎችን ሁኔታ በመመልከት ስሜታቸውን ተከትለው እንደሆነ የገለጹም አሉ፡፡ አቅመ ደካማ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ወንድ የማይጭኑ ሴት አሽከርካሪዎችም ያጋጥማሉ፡፡ ‹‹መዘረፍ በገንዘብ የሚያልፍ ነገር ነው መደፈር ግን በጣም ከባድ ነው›› የምትለው አንድ አሽከርካሪ ብዙ ጊዜ የሰዎችን ሁኔታ ዓይታና ስሜቷን ተከትላ መኪናዋን እንደምታቆም ትናገራለች፡፡ ምሽትና ማለዳ ግን በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መኪናዋን ማንንም ለመርዳት ልታቆም ፍቃደኛ አይደለችም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...