Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአስደንጋጩ የአበረታች ንጥረ ነገር ውዝግብና ኢትዮጵያ

አስደንጋጩ የአበረታች ንጥረ ነገር ውዝግብና ኢትዮጵያ

ቀን:

‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› እንዲሉ የሰሞኑ የአትሌቲክስ ወሬ ሁሉ ከአበረታች ንጥረ ነገር ጋር ተገናኝቷል፡፡ አስደንጋጩ ወሬ በዓለም የመገናኛ ብዙኃን ከተሰማ ወዲህም ከጫፍ እስከ ጫፍ ባለው ስፖርት ወዳድ ሆነም ሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የተለያዩ ስሜቶችን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በአንድ በኩል እንደ ገዛ ልጆቹ የሚመለከታቸውን ብርቅዬና የኩራት ምንጭ የሆኑ አትሌቶቹን በጥርጣሬ ከመመልከት ባሻገር የአገሪቱን ስም ለማጉደፍና የአትሌቶቹን ክብር ለማጨቅየት ሴረኞች የሸረቡት ተንኮል ሊሆን ይችላል በሚል ጭምር ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከወራት በፊት በጎረቤት ኬንያውያን አትሌቶች ላይ የተወራውን ተመሳሳይ ወሬ በማስታወስ መዘዙና እውነትነቱ ለኢትዮጵያም እንደተረፈ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ ይኸኛው ከወሬም አልፎ አሁን አሁን በዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) መጠርጠራቸውና ጉዳያቸው እየተመረመረና እየተጣራ ይገኛል፡፡ ይህ ለብዙኃኑ ስፖርት ወዳድ ዜጋ ሁሉ አስደንጋጭ ወሬ ከተሰማበት ቀን አንስቶ ሕዝቡና አትሌቶቹ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም በተለየ ሁኔታ እንዲያተኩርበት በር የከፈተ ይመስላል፡፡ ይህም በመሆኑ ባለፈው ዓርብ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ‹‹አበረታች መድኃኒቶች ምንነትና አጠቃላይ ጉዳይ›› በሚል በኢትዮጵያ ሆቴል ባመቻቹት መድረክ ቀደምቱ በባዶ እግራቸው ያቆዩት የአትሌቲክሱ ተምሳሌታዊ ቅብብሎሽ አደጋ እያንዣበበበት ስለመሆኑ ወደ ድምዳሜ የደረሱ አስተያየቶች ተንፀባርቀዋል፡፡ መድረኩን የመሩት የብሔራዊ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው ንጉሤ ሲሆኑ፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አምበሳው እንየው በበኩላቸው በመክፈቻው ተገኝተው በዚህ ጉዳይ የመንግሥትን አቋም በግልፅ አንፀባርቀዋል፡፡ በሁለቱ መንግሥታዊ ተቋማት ትብብር በተዘጋጀው መድረክ የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አለባቸው በመድረኩ ለተገኙት አሠልጣኞች፣ የአገር ውስጥ የአትሌት ማናጀሮች? ተወካዮችና አትሌቶች ስለጉዳዩ ሲያስረዱ፣ በዚህ የሰሞኑ መነጋገሪያ በሆነውና አገሪቱ በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አለባቸው፣ በአገሪቱ መንግሥትም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አበረታች ዕፆችን በተመለከተ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በርካታ የዓለም አገሮች ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ ስማቸው እየተነሳ በችግሩ ሲብጠለጠሉ መቆየታቸው እንደተጠበቀ፣ በዚሁ ችግር ኢትዮጵያም አንዷ ተጠቃሽ መሆኗን ጭምር አንስተዋል፡፡ የዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) በአሁኑ ወቅትም ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን መጠራጠሩን በይፋ መግለፁን ሳይቀር አስረድተዋል፡፡ በሌሎች አገሮች ተከስቶ የቆየው ይኼው ችግር በኢትዮጵያ እንዳይከሰት መንግሥትም ሆነ ፌዴሬሽኑ ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ አሁን በተግባር እየሆነና እየተሰማ ያለው በተቃራኒው ሆኖ መገኘቱንም አውስተዋል፡፡ ክስተቱ ያለበትን ደረጃና ሁኔታ መመልከት የግድ እንደሚል ጭምር ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ አትሌቲክስ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ነገር ሳያካትት ተፈጥሮአዊ በሆነ አግባብ ለበርካታ ዓመታት በአመርቂ ውጤት መቀጠሉን የተናገሩት ኃላፊው፣ ወቅት እየተሰማና እየሆነ ያለውን ግን ለስፖርቱ አስፊሪ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ እንደሆነ፣ አትሌቲክሱ መመኪያና መኩሪያ መሆኑ ቀርቶ ወደ ማፈሪያነት እየተሸጋገረ ያለበት አጋጣሚ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ አስደንጋጭ ገጠመኝ የተጠረጠሩት ስድስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምርመራውንና የማጣራቱን ሒደት የተቀላጠፈ ማድረግ ይቻል ዘንድ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር በቅርበት መረጃዎችንና ቃለ መጠይቆችን እየሰጡ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በዚህ ሒደት ውስጥ አልፎ የጥርጣሬው ውጤት በማስረጃ ሲረጋገጥ የሚወሰደውን የዲሲፕሊን ዕርምጃና የአትሌቶቹን ማንነት ጭምር በይፋ የሚገለጽ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡ እያንዳንዱ አትሌት ከዕለት ጥቅምና ዝና ባለፈ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት እንዳለበት፣ በማወቅም ባለማወቅም ይሁን የአሠልጣኞችና የማናጀሮች ምክር በመስማት ተሳታፊ ሆኖ ከተገኘ በምንም ተአምር ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል ጭምር ነው ያስረዱት፡፡ ምክንያቱም ሲሉ ያከሉት ኃላፊው ‹‹የዕለት ነገር የዕለት ነው፡፡ የአገር የሕዝብና የማንነት ጉዳይ ግን ለድርድር የማይቀርብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ መነሻነት ማንኛውም አትሌት የችግሩ ገፈት ቀማሽ ራሱና ራሱ መሆኑን አምኖና ተገንዝቦ በዚህ ክብርንና ማንነትን በሚያሳጣ ተግባር ላለመሳተፍ በፅናት መታገል እንደሚኖርበትም ተናግረዋል፡፡

ሌላው በዚሁ መድረክ የመንግሥትን አቋም በግልፅ ያስቀመጡት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አምበሳው በበኩላቸው፣ ‹‹በምንገኝበት ዘመን የስፖርት ትልቁ ፈተና የስፖርቱ መርህ ከማይፈልጋቸው የፀዳ ስፖርት ማካሄድ ነው፤›› ካሉ በኋላ ለዚህ ሲባልም የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊቋቋም መቻሉን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2003 ፓሪስ ከተማ ላይ በተደረገው ውይይት የዚህ ተቋም አባል መሆን እንደቻለች፣ በዚህም ዋዳ በማናቸውም ሁኔታ የሚያራምዳቸውን ማናቸውንም ውሳኔዎች እንደምትቀበልና እንደምታስፈጽም፣ የአባልነት ክፍያም እንደምትከፍል ገልጸው በዚህ መሠረት በአገሪቱ ይህን ጥፋት ያጠፋ አመራር፣ አትሌት (በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ)፣ አሠልጣኝ፣ ማናጀርና የማናጀር ተወካይ ተመጣጣኝ የሆነ የዲሲፒሊን ዕርምጃ የምትወስድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ ይህንኑ ጉዳይ የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በቅርቡም አህጉራዊው የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ በአገሪቱ ተገኝቶ የተለያዩ ግምገማዎችን አድርጎ በተለይም በዚህ ረገድ ዘመናዊ አደረጃጀትና የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ ምክር አዘል አስተያየቶች ሰጥቶ ተመልሷልም ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ብሔራዊ ኮሚቴው በአገር ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውንም ውድድሮች ከውድድር በፊትና ከውድድር በኋላ አስፈላጊ ምርመራዎችን እንደሚያደርግ ጭምር ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ተገኘ ተብሎ በምርመራ ላይ ለሚገኘው ጉዳይ ተጠያቂዎቹ አትሌቶች ብቻ ተደርገው እንደማይወሰዱ ይልቁንም ለዚህ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮችና አመራሮች ሊኖሩበት እንደሚችል ግንዛቤ ተወስዶ ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 ምክንያቱም ይህ ድርጊት አትሌቶች ተገቢ ያልሆነ ውጤት እንዲያገኙ ከማስቻሉ በተጓዳኝ በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ እነዚህ ተዋንያን በወንጀልም ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀር ነው ያስረዱት፡፡ ሌላው ከዚህ ጎን ለጎን መታየት እንዳለበት ያስቀመጡት ደግሞ ዜግነትን የሚያስቀይሩ ጭምር መኖራቸውን ነው፡፡ በመጨረሻም ሚኒስትር ዴኤታው፣ ኢትዮጵያን በተቀረው ዓለም ተምሳሌታዊ ተደርጋ ከምትታወቅባቸው አትሌቲክሱ አንዱ መሆኑንና ይህንንም ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ከምንም በላይ የሚጠነቀቁለት ቅርስ እንጂ ማንኛውም ሰው በፈለገው መንገድ አላስፈላጊ ጥቅምና ወንጀል ሊፈጸምበት እንደማይቻል ጭምር አስገንዝበዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ቀደምቱ በባዶ እግራቸው ያቆዩት ተምሳሌታዊ ቅርስ እንደመሆኑና ይህም በአንዳንድ አጭበርካሪዎችና ተስፈኞች ልናጣው የሚገባ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡  የዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) የተጠቀሱትን አትሌቶች ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ስለመጠቀማቸው ጥርጣሬዉን ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አትሌቶችና የዘርፉ ሙያተኞች በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ኃይሌ ኢትዮጵያውያኑን አትሌቶች በሚመለከት በዋዳ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱበት አግባብ ጥርጣሬ ተብሎ መውሰድ እንደሌለበት ጭምር ይከራከራል፣ ሙሉ ቃለ መጠይቁን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገር ኤጀንሲ (ዋዳ) ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ይፋ ያደረገውን ጉዳይ እንዴት ትመለከተዋለህ?

ኃይሌ፡- በዋዳ ሕግ ጥርጣሬ ብሎ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ጥርጣሬ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ራሱ ኤጀንሲው አትሌቱ ባልጠበቀውና ባላሰበው ጊዜና ሰዓት ደምና ሽንት ናሙና መውሰድ እፈልጋለሁ የሚልበት ወቅት ነው ጥርጣሬ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው፡፡ አሠራሩም ዋዳ የሚከታተላቸውን አትሌቶች ዝርዝር ያውቃል፡፡ አትሌቶቹ በማራቶን ሊሆን ይችላል፣ በአምስትና አሥር ሺሕ ሜትሮች እንዲሁም በሌሎችም ውድድሮች ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህን ወቅት ጥርጣሬ ሲያድርበት ድንገተኛ የሆነ ናሙና ይወሰዳል፡፡ አትሌቱም ለዚሁ ሲባል በየሦስት ወር የሚሞሏቸው መጠይቆች አሉ፡፡ እኔን እንደ ምሳሌ ብወሰድ ብዙ ጊዜ ባልጠበቅኩትና ባላሰብኩበት ሰዓት ቢሮዬ በመምጣት ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ናሙና ወስደዋል፡፡ ሌላው የምርመራ ጊዜ ደግሞ በውድድር ጊዜ የሚደርገው ነው፡፡ ይኼ ከውድድር በፊትና በኋላ ሁለት ጊዜ የሚደረግ ምርመራ ነው፡፡ በአብዛኛው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የሚወጡ አትሌቶች በቋሚነት ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ከሦስተኛ በኋላ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች አለፍ አለፍ እያሉ ዕድል የገጠመው ነው ምርመራ የሚደረግበት፡፡ ለዚህ ነው በዋዳ ጥርጣሬ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም የምለው፡፡ ሌላውና ምናልባት የአትሌቱን ‹‹ኤ›› ናሙና መርምሮ ውጤቱ ፖዘቲቭ ከሆነ አትሌቱ በማመሳከሪያነት የ‹‹ቢ›› ናሙናው እንዲታይለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡ በዚህ ሒደት ሁሉ ነገር የሚከናወነው አትሌቱ ለምርመራ በሚሰጠው ናሙና በኮድ ይቀመጣል፡፡ ይኼው ኮድ ወደ ሰባት በሚደርስ ኮፒ ተባዝቶ ነው ለእያንዳንዱ አገር የሚላከው፡፡ ስም የሚኖርበት የመጀመሪያው ኮፒ ላይ በኤጀንሲው ቢሮ የሚቀመጠው ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሠረት አትሌቱ ኃይል ሰጪ ነገር መጠቀሙ ከተረጋገጠ ስሙና ማንነቱ ተገልጾ ለሚወክለው አገር ይላካል፡፡ የሚገርመው ምርመራውን የሚያደርገው ተቋምና ዋዳ የተለያዩ ናቸው፡፡ ሁሉን ነገር የሚያከናውኑት በኮድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአትሌቱ የምርመራ ውጤት የተከለከለ ንጥረ ነገር መጠቀሙ እውነት ከሆነ ዕርምጃውን የሚወስደው አካል ማነው?

ኃይሌ፡- የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤፍ) ሆነ ዋዳ የቅጣት ውሳኔ አያስተላልፍም፡፡ የተከለከለውን ንጥረ ነገር ተጠቅሞ የተገኘው አትሌት ለሰጠው ደምና ሽንት በተሰጠው ቁጥር (ኮድ) መሠረት ስሙና የየት አገር አትሌት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ስሙና ማንነቱ ተጠቅሶ ለሚወክለው አገር ፌዴሬሽን ተልኮ በፌዴሬሽኑ በኩል ቅጣቱ እንዲተላለፍበት ነው የሚደረገው፡፡ በእርግጥ ቅጣቱ ተፈጻሚ የሚሆንበት አግባብ ዋዳ በሚያስቀምጣቸው የቅጣት ዓይነት ደረጃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶች የ‹‹ቢ›› ናሙና ምርመራ እንዲደረግላቸው ለዋዳ ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፣ መፍትሔ ይኖረዋል?

ኃይሌ፡- ‹‹ቢ›› ናሙናን በሚመለከት ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ዋዳ በወሰደው ‹‹ኤ›› ናሙና አትሌቱ የእኔ ላይሆን ይችላል ብሎ የሚጠራጠር ከሆነ ለማመሳከሪያነት ካልሆነ በውጤቱ ላይ ያን ያህል ለውጥ አያመጣም፡፡ እስከዛሬ ባለው ተሞክሮም በ‹‹ቢ›› ናሙና ነፃ የወጣ አትሌት የለም፡፡ ዕድሉም 0.1 በመቶው ነው፡፡ ምክንያቱም ለ‹‹ኤ››ም ሆነ ለ‹‹ቢ›› ናሙና የሚወሰደው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ዕድሉ ጠባብ ነው የምለው፡፡

ሪፖርተር፡- በባዮሎጂካል መንገድ በደም የሚወሰድ አበረታች ንጥረ ነገር መኖሩም ተሰምቷል፡፡

ኃይሌ፡- አወሳሰዱ ረቀቅ ያለ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ዋዳም ሆነ አይኤኤኤፍ በምርመራ ያልደረሱበት ንጥረ ነገር (ሰብስታንስ) እንዳል ይታመናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ሁለቱ ተቋማት በእንደዚህ ዓይነት ነገር የሚጠረጥሩትን አትሌት የኋላ ታሪኩንና በአትሌቱ ደም ውስጥ ምን ምን ዓይነት ንጥረ ነገር እንዳለ ጊዜ ወስደው ያጠናሉ፡፡ በዚህ ሒደት የሚጠረጠሩ አትሌቶች የምርመራ ውጤታቸውን፣ አትሌቶቹም ወደየፌዴሬሽኖቻቸው አይላኩም፡፡ ሁሉ ነገር የሚጠናቀቀው በዚያው በዋዳ አካባቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዋዳ የሚጠረጥራቸውን አትሌቶች ዝርዝር የተረጋገጠ ካልሆነ ወደየፌዴሬሽኖች አይልክም፡፡ ያረጋገጠውን ብቻ ነው ለውሳኔ የሚልከው፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቶች ለኃይል ሰጪነት የሚጠቀሙባቸው ንጥረ ነገሮች ከ200 በላይ እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡  

ኃይሌ፡- ዋዳ በዚህ በኩል ምንም ችግር የለበትም፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂን ያሟላ መሣሪያ ባለቤት ነው፡፡ በአገራችን የደምና ሽንት ናሙና ወስደን እናስመርምር ብንል ከፍለን ካልሆነ አይሞከርም፡፡ ሁሉንም እንደ ባህሪው አንጥሮ የሚያወጣ መሣሪያ ባለቤት ስለሆነ በዚህ በኩል እስካሁን የገጠመው ችግር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደዚህ ከሆነ የተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ምንድነው?

ኃይሌ፡- ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገርን በሚመለከት ጠንካራ ሕግ አላት፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ተግባራዊ ማድረግ ካልሆነ ሌላ አማራጭ አይኖርም፡፡ አሁን መታሰብ ያለበት ተተኪ አትሌቶች ከዚህ አደገኛ መንገድና አካሄድ መትረፍ የሚችሉበት መሆን ይኖርበታል፡፡  

ሪፖርተር፡- አበረታች ንጥረ ነገር መጠቀም ሌላ ጉዳት አይኖረውም?

ኃይሌ፡- በሚገባ አለው፡፡ በአገራችን በተለይ በአሁኑ ወቅት ስለ ሙስና በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ ሙስና አንድ ሰው ከመንግሥት ካዝናም ይሁን ከግለሰብ ኪስ መውሰዱ አይደለም አደገኛ የሚያደርገው፡፡ ሌላው ኅብረተሰብ እኔም እንደ እከሌ ካልዘረፍኩ አያልፍልኝም ብሎ እንዲያስብ ማድረጉ ነው፡፡ በአትሌቲክሱም ጠዋትና ማታ ለፍቼ ካልተሳካልኝ እኔም በአንድ እንክብል አልጠቀምም የሚሉ ተተኪዎችን ማፍራቱ የማይቀር መሆኑ ሊታመን ይገባል፡፡ ይኼ ነው የጎንዮሽ ጉዳቱ፡፡

ሪፖርተር፡- ጥፋተኛ ተብለው ዕርምጃ የሚወሰድባቸው አትሌቶች በተለይ ካፈሩት ሀብት ጋር በተያያዘ የሚጠብቃቸው ምንድነው?

ኃይሌ፡- በግሌ የንብረቱ ጉዳይ የሚያሳስብ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ አትሌቶች ጥሪት ያፈሩት በዓለም ዋንጫና በኦሊምፒክ መድረኮች አይደለም፡፡ ከግል ውድድሮች ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አወዳዳሪ ድርጅቶች ገንዘቤን መልስ የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ በዓለም ዋንጫና ኦሊምፒክ ላይ የሚገኝ ከወርቅ እስከ ነሐስ ዋጋ የሚኖረው በወቅቱና በቦታው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ይልቅስ ለእኔ ትልቁ አደጋ ቀደምቱ ከእኔ ጀምሮ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረውን ቦታና ምልከታ ነው፡፡ ብዙዎች በእነ ኃይሌ ጊዜስ ላለመጠቀማቸው ማረጋገጫው ምንድነው የሚሉ እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለአገሪቱ አትሌቲክስ ሲባል ምርትና ግርዱ የሚለዩበት መሆኑ ጥሩ አጋጣሚ ስለመሆኑም መዘንጋት የለብንም፡፡ ምክንያቱም አሁን አሁን የተደበላለቀ ነገር ነው ያለው፤ ለስፖርቱ በቦታው የሚቀመጡ ሰዎች ሳይቀር መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ በአገሪቱ ለዚህ ቦታ እኔ አልመጥንም የሚል እየጠፋ ነው፡፡ እኔ አውቃለሁ እየበዛ ነው፡፡ በእግር ኳሱ እግር ኳሱን የሚያውቅ፣ በአትሌቲክሱም አትሌቲክሱን የሚያውቅ በሌላው ስፖርትም እንደዛው ካልሆነ አሁን እየሄድንበት ያለው ግምታዊና የደመ ነፍስ አሠራር አንድ ቦታ ላይ አቅጣጫ ሊበጅለት ይገባል፡፡ እዚህ አገር ሌላው በሽታ እኔ መስማት የምፈልገውን ካልሆነ ሌላውን በፍፁም፡፡ ወይም ደግሞ የተነገረበት አግባብ እንዴትና በምን አግባብ የሚለው ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው ሳይታይ ሰዎች ለሚፈልጉት አጀንዳ አንዱን ነገር ብቻ መዘው ማብጠልጠል መጥፎ በሽታ እየሆኑ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...