መተጫጨትን በተመለከተ በዚህ ጽሑፍ ለማየት የታሰበው ጸሐፊው በግል ሥራ በጎንደር በተገኘበት ጊዜ ባስተዋለው ጉዳይ ነው፡፡ የጎንደር ከተማን ለረገጠ ሰው ታሪካዊነቷን ለመመስከር የሚያስችሉ አሻራዎችን ያለአስጎብኝ አጋዥነት ሊረዳ ይችላል፡፡ የከተማዋ አቀማመጥ፣ የቤቶቿ አሠራር፣ በከተማዋ የሚገኙት የፋሲል ግንብና ደብረ ብርሃን ሥላሴን የመሰሉ ሕንፃዎች ጎንደር የቆየ ታሪክ ባለቤት ስለመሆኗ ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ስያሜዋም ታሪካዊነት አለው፡፡ አቶ ያሬድ ግርማ ‹‹የጎንደር ታሪክ›› በሚል የጻፉት መጽሐፍ ጎንደር ‹‹ወይኔና ሠይኔ›› የተባሉ ወንድማማቾች በመሬት ተጣልተው ሽማግሌዎች ሲያስታርቋቸው ‹‹ወይኔ በዚህ እደር (እረስ)፤ ሠይኔ ደግሞ በወይኔ ጎን እደር›› ብለው የስያሜውን አመጣጥ ይተነትናሉ፡፡ ተጨባጭነታቸው አከራካሪ ቢሆንም ሌሎችም አፈ ታሪኮች እንዳሉ ጸሐፊው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የቃሉ ምንጭ ‹‹ጉንደ-ሀገር›› የሚለው የግዕዝ ቃል የሀገር ግንድ፣ የሀገር መሠረት የሚል ትርጓሜ ያለው በመሆኑ ታሪካዊነቱን አይለቅም፡፡ ከቁሳዊው ቅርስ ባለፈ በገጠራማው የጎንደር አካባቢ በስፋት የሚተገበረው የመተጫጨት ሥርዓት ለዘመናት የቆየ በመሆኑ፣ የአማራን የቤተሰብ ሕግ ለመገምገም መነሻ ማድረጋችን ተገቢ ይመስላል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ መተጫጨትን የተመለከቱ የሕግ ሰነዶችን የክልሉን የቤተሰብ ሕግ በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ ውይይት ወቅት ከተነሱ ሐሳቦች ጭምር በማየት የጎንደርን ነባራዊ ሁኔታ ለመቃኘት ሙከራ ያደርጋል፡፡
መተጫጨት በፍትሐ ነገሥት
መተጫጨት እንደየባህሉ የተለያየ ቢሆንም ዘመናዊ ሕግ በአገራችን ከመወጣቱ በፊት በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተፈጻሚ የነበረው ፍትሐ ነገሥት ዓቢይ የሕግ ሰነድ እንደነበር የሕግ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ስለመተጫጨት በፍትሐ ነገሥት የሰፈሩት ድንጋጌ ቅድመ ፍትሐ ብሔር ሕግ የአማራው ክልል ልማድ ላይ ተፅዕኖ ስለማድረጉ መናገር ተአማኒነት ይኖረዋል፡፡ ፍትሐ ነገሥትን መነሻ ካላደረግን ባህሎች ተጽፈው ስለማይገኙ፣ እንደየአካባቢው ስለሚለያዩ ታሪካዊ ዳራውን ለመተንተን ያስቸግራል፡፡
በፍትሐ ነገሥት መተጫጨት ጋብቻን የሚቀድም የመፈቃቀድ ሥርዓት ነው፡፡ መተጫጨት የወደፊት ተጋቢዎቹ ጋብቻ ከመፈጸማቸው በፊት ጠባይ ለጠባይ የሚጠናኑበት፣ ፍቅራቸውን የሚያጠናክሩበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ማጨት በጽሑፍ ወይም በቃል ሊፈጸም እንደሚችል፤ ሥርዓቱም አስፈላጊ ስለመሆኑ በፍትሐ ነገሥት ተገልጿል፡፡ በዚሁ መሠረት ሁለቱ ጥንዶችና ወላጆቻቸው ሁለት ቀሳውስት በተገኙበት ፈቃዳቸውን መግለጽ የሚገባቸው ሲሆን፣ ቀሳውስቱ የወደፊት ተጋቢዎች ራስ ላይ እጃቸውን በመጫን እንዲፀልዩ በጣቶቻቸውም የቃል ኪዳን ቀለበት እንዲያደርጉላቸው ይደነግጋል፡፡ በመተጫጨት ወቅት ሁለቱ የወደፊት ተጋቢዎች ፈቃዳቸውን መግለጽ ያለባቸው ሲሆን፣ የምትታጨው ሴት ለማይመጥናትና ለማትፈልገው ወንድ ከታጨች ወላጆች ቢፈቅዱም እንቢታዋ የተከበረ ነው፡፡ ባሏ የሞተባት የተወሰኑ ዓመታት ካለፈ በኋላ ልትታጭ ትችላለች፡፡ የመተጫጨት ጊዜ ወንዱ አገር ውስጥ ካለ ሁለት ዓመት፣ ርቆ ከተጓዘ ደግሞ ሦስት ዓመታት ሊረዝም የሚችል ሲሆን፣ ከዚህ ዓመት በላይ ከቆየ ሴቷ ለሌላ ወንድ ልትሰጥ እንደምትችል በፍትሐ ነገሥቱ ተገልጿል፡፡ በመተጫጨት ወቅት ማጫ ገንዘብ ወይም ንብረት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሴቷ ማጫ ተቀብላ ጋብቻውን ለመፈጸም ፈቃደኛ ካልሆነች የማጫውን እጥፍ ለመመለስ ትገደዳለች፡፡ ማጫውን የሰጠው ቃሉን ካጠፈ ደግሞ የሰጠው አይመለስለትም፡፡ ይህ መርህ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከተደነገገው የቀብድ ደንብ ጋር ይመስላል፡፡ በፍትሐ ነገሥቱ ወንድ ልጅ አካለ መጠን የሚያደርሰው በሃያ ወይም በሃያ አምስት ዓመቱ ሲሆን፣ ሴት ደግሞ በአሥራ ሁለት ወይም አሥራ አምስት ዓመቷ ነው፡፡ የዓመታቱ ልዩነት ሴቶችና ወንዶች እኩል ሆነው የሚታዩ እንዳልነበሩ አመላካች ነው፡፡ ከዚህ በላይ የተገለጸው የፍትሐ ነገሥቱ ድንጋጌዎች በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያሉት አብዛኞቹ ባህሎች ላይ የራሱ ተፅዕኖ ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በፍትሐ ብሔር ሕጉና አሁንም በተወሰኑ የክልል የቤተሰብ ሕግጋት ውስጥ ለተደነገጉት የመተጫጨት መርሆዎች መሠረት መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ፍትሐ ነገሥት መተጫጨት በቤተ ዘመድ መከወኑ፣ ያስቀመጠው የተወሰነ የቆይታ ጊዜ መኖሩ የማጫ ሀብት አስፈላጊነት ሲፈርስ ማጫው የሚመለስበት ሁኔታ ለፍትሐ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች በተወሰነ ደረጃም መተጫጨት ላካተቱ የቤተሰብ ሕጎች መነሻ ሆኗል፡፡
መተጫጨት በፍትሐ ብሔር ሕጉ
የፍትሐ ብሔር ሕጉ መተጫጨትን በተመለከተ ሰፋ ያሉ ድንጋጌዎችን የያዘ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የቤተሰብ ሕጎቻቸውን ባወጡ ክልሎች የተሻረ በመሆኑ ተግባራዊ ጥቅም የለውም፡፡ ሆኖም የፍትሐ ነገሥቱን ተፅዕኖና የአዲሶቹን የቤተሰብ ሕግጋት ቅኝት የገራ በመሆኑ አጭር ምልከታ እናደርግበት፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ መተጫጨት በሁለት የተለያዩ ቤተሰብ አባላት መካከል እጮኛውና እጮኛይቱ ጋብቻ ለመመሥረት በመፈለግ የሚያደርጉት ውል ሲሆን፣ የሁለቱ ቤተሰቦች ፈቃድ ከሌለው በሕግ ፊት የፀና አይሆንም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መተጫጨት ወደፊት የሚጋቡት ጥንዶች ፈቅደው ካላደረጉት ዋጋ የለውም፡፡
ስለዚህ የወደፊት ተጋቢዎቹ ቢፈቃቀዱ እንኳን ቤተሰቦች ካልፈቀዱ፤ እንዲሁም ቤተሰብ ፈቅዶም የወደፊት ተጋቢዎች ካልተፈቃቀዱ መተጫጨቱ ሕጋዊ አይሆንም፡፡ ይህ ድንጋጌ ጋብቻ በተጋቢዎች ግልና ሙሉ ፈቃድ ሊመሠረት እንደሚገባ የሚገልጸውን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የሚጥስ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕጉ የወደፊት ተጋቢዎቹ በመተጫጨት ወቅት ፈቃዳቸውን እንደሚገልጽ ቢደነግግም፣ ከዚያ በላይ የቤተሰቦች ፈቃድ አስፈላጊነት ትልቅ ቦታ የተሰጠው በመሆኑ ነው፡፡ የሁለቱ ቤተሰቦች የተስማሙበትን መተጫጨት የወደፊቶቹ ተጋቢዎች ሊቃወሙ የሚችሉበትን ሁኔታ በባህል ተፅዕኖ ሥር ባሉ የገጠር አካባቢዎች ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል የወደፊት ተጋቢዎቹ ለጋብቻ የተፈቀደ ዕድሜ (በፍትሐ ብሔር ሕጉ ለወንድ 18 ለሴት 15) ካልደረሱ መተጫጨቱ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይህ ድንጋጌ መተጫጨት ከተጠቀሱት የዕድሜ ገደቦች በፊት መፈጸማቸውን የሚከለክል ባይመስልም፣ በሕጉ የተቀመጡት ውጤቶች ግን ተግባራዊ የሚሆኑት ተጫጭተው የጋብቻ አነስተኛ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ነው፡፡
ይህ አነስተኛ ዕድሜ ውል ለመዋዋል የሕግ ችሎታ ለሌላት ሴት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበትን ጋብቻ 18 ዓመት ሳይሞላት እንድትፈጽም የሚያደርጋት ከመሆኑ ሌላ፣ ከሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ጋር የሚጋጭ በመሆኑ መተጫጨትን አዳዲስ የቤተሰብ ሕግጋት እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ መተጫጨት በአካባቢው ልማድ ሥርዓት የሚፈጸም ሲሆን፣ በመዝገብ ሹም እንዲመዘገብ፣ በጽሑፍ እንዲደረግም ግዴታ አልተጣለም፡፡ ሆኖም በሁለት ምስክሮች ፊት ሊፈጸም የሚገባው ሲሆን፣ በመተጫጨት ወቅት የጋብቻው ጊዜ ካልተወሰነ ተጋቢዎቹ ወይም ቤተ ዘመዶቻቸው ፈቃዱን በሰጡ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጋብቻ ሊፈጸም እንደሚገባ በሕጉ ተገልጿል፡፡ መተጫጨት በተጋቢዎቹ ወይም በቤተ ዘመዶቻቸው ሊፈርስ የሚችል ሲሆን፣ ያፈረሰ ወገን ለወጣው ወጪና ኪሳራ እንዲሁም ለአንድ ሺሕ ብር የሞራል ካሳ ኃላፊ ይሆናል፡፡
መተጫጨት በአማራ የቤተሰብ ሕግ
በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተቀመጡትን የቤተሰብ ሕግጋት በማሻሻል ሒደት መተጫጨትን በተመለከተ የተለያዩ አቋሞች ተወስደዋል፡፡ የፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ ሲረቀቅ የተወሰኑ አካላት መተጫጨት የወደፊት ተጋቢዎች ለመጠናናት ሊጠቀሙበት የሚችሉበት መድረክ በመሆኑና የቆየ ባህል በመሆኑ ተገቢ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡ በወቅቱ የፍትሕ ሚኒስቴርም ባዘጋጀው ረቂቅ ተካትቶ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መተጫጨት በባህል የሴቶችን የበታችነት በሚያንፀባርቅ መልኩ የሚፈጸም በመሆኑና አተገባበሩም የተጋቢዎችን ነፃ ፈቃድ የሚጋፋ ለሕፃናት ጋብቻ (Child Marriage) በር የሚከፍት በመሆኑ እንዳይካተት የተከራከሩ ወገኖች ነበሩ፡፡ የፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ ሲፀድቅ ግን መተጫጨት በዝምታ እንዲታለፍ ተደርጓል፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት አቶ መሐሪ ረዳኢ ሲገልጹ ‹‹አንድ ወጥ የሆነ የመተጫጨት ሥርዓት በአገሪቱ ውስጥ ባለመኖሩ በአንድ ወጥ ሕግ ለመደንገግ መሞከር አስቸጋሪ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፤›› ይላሉ፡፡ አክለውም ‹‹የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በሕግ ዕውቅና አይሰጠውም ብሎ ከቤተሰብ ሕጉ ሰረዘው እንጂ ክልክል ነው ስላለው ሕገ መንግሥቱን እስካልተጻረረ ድረስ በመጠነኛ መድረክነቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡›› ሁለቱ ተጋቢዎች ከፈለጉ በየአካባቢያቸው ልማድ ሊተገብሩት እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልል መተጫጨትን በግልጽ ዕውቅና የሚሰጥ የቤተሰብ ሕግ አጽድቋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቤተሰብ ሕግጋትም እንዲሁ ለመተጫጨት የሕግ ዕውቅና ከሰጡት መሃል ናቸው፡፡ የአማራ የቤተሰብ ሕግ በምዕራፍ አንድ ‹‹ቅድመ ጋብቻ ትጭጭት›› በሚል በሕጉ የመጀመሪያ 10 ድንጋጌዎች ለመተጫጨት ሕጋዊ ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት ትጭጭት ‹‹ለአካለ መጠን የደረሱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለወደፊት ትዳር እንደሚመሠርቱ በይፋ ገልጸውና የጋብቻ መፈጸሚያ ቀን ቆርጠው በመስማማት የእጮኛውና የእጮኛይቱ ቤተ ዘመዶች ተወካዮችና ምስክሮቻቸው በታዛቢነት በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ፈቅደው የሚለዋወጡበት የእርስ በርስ ቃል ኪዳን ነው፤›› በሚል ትርጓሜ ተሰጥቷል፡፡ የመተጫጨት ውል በጽሑፍ የሚደረግ ሆኖ ዕጩ ተጋቢዎችና አራት የቤተ ዘመድ እማኞቻቸው /ሁለት ከወንድ ወገን፣ ሁለት ከሴት ወገን/ ሊፈርሙበት ይገባል፡፡ የጋብቻ መፈጸሚያ ቀን ካልተቆረጠ የጋብቻቸው ሥነ ሥርዓት ትጭጭቱ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚሆን ሕጉ ይደነግጋል፡፡ የፍትሐ ነገሥቱን ተፅዕኖ ልብ ይሏል፡፡ ከዕጩ ተጋቢዎች አንዱ የጊዜ ገደቡን ጋብቻ አልፈጽምም ሲል እምቢ ካለ ወይም ከዘገየ ውሉ የሚጣስ ሲሆን፣ ያፈረሰው ወገን የወጣውን ወጪ የመተካትና የተደረገ ስጦታም ካለ ለመመለስ ይገደዳል፡፡ የአማራው የቤተሰብ ሕግ የህሊና ጉዳትን በተመለከተ ያስቀመጠው የካሳ መጠን አለመኖሩ ከፍትሐ ብሔር ሕጉም ሆነ ከሌሎች ክልሎች የቤተሰብ ሕግጋት ያነሰ ቦታ ለመተጫጨት መስጠቱን ያሳያል፡፡ ሕጉ በመተጫጨት ወቅት የሚኖረው ነፍሳዊና ስሜታዊ ቅርርብ ግንኙነቱ በተቋረጠ ጊዜ የሚያመጣውን ጉዳት በአግባቡ ሊመለከት ይገባ ነበር፡፡ የህሊና ጉዳት ካሳ በፍትሐ ብሔር ሕጉ 1,000.00 ብር በደቡብ የቤተሰብ ሕግ እስከ 10,000.00 ብር ሊደርስ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በመተጫጨት ውል የሰፈሩ የመቀጫ የውል ቃል በአማራው የቤተሰብ ሕግ ውጤት የሌለው ሲሆን፣ በቤኒሻንጉል የቤተሰብ ሕግ ግን ፍትሐዊ እስከሆነ ድረስ ውሉን ያፈረሰው ወገን ያሰፈረውን መቀጮ የሚከፍል ይሆናል፡፡
ሕጉና አተገባበሩ
የአማራ የቤተሰብ ሕግ መተጫጨት በወደፊት ተጋቢዎች ፈቃድ ብቻ የሚመሠረት መሆኑን፣ ቤተ ዘመዶች የታዛቢነት ሚና ብቻ እንዳላቸው እንዲሁም መተጫጨቱ የሚፈጸመው የወደፊት ተጋቢዎቹ አካለ መጠን ሲያደርሱ መሆኑ መገለጹ በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና በፌዴራልና በክልሉ ሕገ መንግሥታት የተቀመጡትን የግለሰብ ሰብዓዊ መብት የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ሆኖም የድንጋጌው መኖር ብቻ በራሱ የተፈለገውን የሰብዓዊ መብት መከበር ግብ ለመምታቱ ዋስትና አይሆንም፡፡ ጸሐፊው በጎንደር ከተማ ያነጋገራቸው አንድ አዛውንት መተጫጨት በገጠራማው የዞኑ ክፍል አሁንም በቤተሰቦች መካከል እንደሚደረግ ነግረውታል፡፡ በሕግ ደረጃ የተቀመጠው የግለሰቦች የመፈቃቀድ መብት በተግባር መተጫጨቱ ፈቃድን የሚያረጋግጥ የመንግሥት አካል ፊት እስካልተደረገ ድረስ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ታጭተው የኮበለሉ በየከተማው የቤት ውስጥ ሠራተኛ ሆነው የሚያገለግሉ ሴቶች ለዚህ ጥሩ እማኝ ናቸው፡፡ የመተጫጫ ዕድሜንም በተመለከተ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ በገጠር አካባቢ መተጫጨት ከጋብቻ በፊት ሕፃናት አካለ መጠን ሳያደርሱ የሚከናወን በመሆኑ፣ በመተጫጨት ሰበብ የጋብቻን ሕይወት ቀደም ብለው የሚጀምሩበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ በገጠር የመታጫ ዕድሜ የሚወሰነው በቁጥር በሚገለጹ ዓመታት ሳይሆን ሴቷ በቤቷና በአካባቢዋ በተሰጣት ቦታ መጠን ነው፡፡ በሌላ በኩል መተጫጨቱ የተደረገው አካለ መጠን ባልደረሱ ሰዎች መሆኑን ለማረጋገጥ እንኳን የሚያስቸግርበት ሁኔታ አለ፡፡ የልደት ምዝገባ በሌለበት አገራችን የሕፃናትን ዕድሜ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ በዚህ ረገድ በቤተሰብ ሕጉ ዕድሜ በልደት ምዝገባ እንደሚረጋገጥ መደንገጉ ረጋ ሰራሽ ነው፡፡ የታጨይቲቱ ወይም የተገባችው ሴት አካለ መጠን ስለማድረሷ የምትናገረው ራሷ ናት፡፡ የሕጉ ጥበቃ ደግሞ አካለ መጠን ያላደረሱትን ከራሳቸው መጠበቅ ጭምር በመሆኑ፣ ዕድሜያቸውን ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ እንደተረዳሁት የሕፃናትን ዕድሜ በሐኪም የማስመርመር ልምድ አለ፡፡ ሐኪሞች በእርግጠኝነት የሕፃናትን ዕድሜ ለማወቅ ባይችሉም በኤክሲሬይ በመታገዝ ልጅቷ 18 ዓመት የሞላት ወይም ያልሞላት መሆኗን ገልጸው ማስረጃ ይሰጣሉ፡፡ ምዕራባውያኑ ግን ትክክለኛ ዕድሜ ለማወቅ የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ አላቸው፡፡
በመተጫጨት ሽፋን ሕፃናት ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው እንዲያገቡ የሚገደዱበትም አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ ያለዕድሜ ጋብቻ መነሻው ባህላዊ ቢሆንም ለመተጫጨት የተሰጠው የሕግ ከለላ ግን ሴቶችን ለጥቃት እንደሚያጋልጣቸው በዞኑ ያነጋገርኳቸው ፖሊሶች ገልጸውልኛል፡፡ አንዳንድ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች መተጫጨት ሴቶችን ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ከሚያነሳሱ ምክንያቶች አንዱ ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡ በአማራ ክልል በሚገኙ ብዙ ወረዳዎች ያለ ዕድሜ ጋብቻ ፈታኝ ያልተቀረፈ ችግር መሆኑን ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በተግባር ፖሊሲ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ያለዕድሜያቸው ሊያገቡ መሆኑ ተገልጾለት ጋብቻው እንዳይፈጸም አድርጓል፡፡ አብዛኛዎቹ ጉዳዮች በሕፃናቱ አቤቱታ አቅራቢነት ዕርምጃ የተወሰደባቸው መሆናቸውን ባለሙያዎች ገልጸውልኛል፡፡ ሕፃናቱ ጋብቻውን ባልተቃወሙበት ሁኔታ ወንጀሉ ሪፖርት እንደማይደረግ ማንም ሊረዳው የሚችል ሃቅ ነው፡፡ ሊፈጸሙ የነበሩት ጋብቻዎች የትጭጭት ጊዜ በአብዛኛው ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት የተደረጉ በመሆኑ፣ መተጫጨቱ በባህል መሠረት እንጂ በሕግ አግባብ ላለመከናወኑ በቂ አስረጂ ነው፡፡ መከላከልን አልፎ በሕፃናቱ ላይ የተፈጸሙ ያለ ዕድሜ ጋብቻዎች ስለመኖራቸው በልጅነታቸው ልጅ ይዘው በገጠርና በከተማ አደባባይ የሚሄዱ ሴቶች ምስክር ናቸው፡፡ በተወሰኑት ላይ ሕፃናት ያለዕድሜያቸው በመዳራቸው በቤተሰቦቻቸው ላይ የወንጀል ክሶች ተመሥርተው በክትትል ላይ እንደሆኑ፤ የተወሰኑትም ጥፋተኛ ተብለው ስለመቀጣታቸው ጸሐፊው በጎንደርና በባህር ዳር ከሚሠሩ የሕግ ባለሙያዎች ተረድቷል፡፡ ሪፖርት ያልተደረገው ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይደለም፡፡
ለማጠቃለል እንሞክር፡፡ መተጫጨት በአማራ የቤተሰብ ሕግ ዕውቅና ቢሰጠውም አፈጻጸሙ ሴቶች ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ሰበብ ይሆናል፡፡ መተጫጨትን በሕግ ማዕቀፍ ለማካተት ብቸኛ ምክንያት ባህልን መጠበቅ እንጂ ለዕጩ ተጋቢዎች የመጠነኛ መድረክ ለመፍጠር አይመስልም፡፡ የመተጫጨት ባህል ለወደፊት ተጋቢዎቹ በተለይ ለሴቷ የማይመች በሆነበት ሁኔታ የሕግ ዕውቅና መስጠት የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት ቸል ማለት ነው፡፡ በተግባር መተጫጨቱ በወደፊት ተጋቢዎቹ ፈቃድ መደረጉን፤ የሚተጫጩትም ዕድሜያቸው አካለ መጠን ያደረሰ መሆኑን ማረጋገጥ እንኳን በገጠር በከተማም አስቸጋሪ ነው፡፡ በጎንደርና በባህር ዳር ያስተዋልኩዋቸው የተወሰኑ ጉዳዮችና የግለሰቦች ተሞክሮ የአማራን ሙሉ ተሞክሮ ባይገልጽም፣ ከዚህ የራቀ እንዳልሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ መተጫጨት በሕጉ መቀጠሉ የቤተሰብ ሕጉ ለወጣበት የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ፤ እኩልነትን ለማረጋገጥ ዓላማ ማስፈጸም መጥቀሙ ከታመነበት፤ መዝጋቢ አካል፣ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ወይም ሌላ አካል አፈጻጸሙን ሊከታተለው ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡