Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹ካፒታል ድንበር ስለሌለው የባንኮች ውህደት የማይቀር ነው››

አቶ አዲሱ ሃባ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት

አቶ አዲሱ ሃባ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ባንኮች በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ከጣሊያን ሚላኖ ከሚገኘው ፊን አፍሪካ ፋውንዴሽን በባንክና ፋይናንስ ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ላለፉት 38 ዓመታት በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሳለፉት አቶ አዲሱ፣ 15 ዓመታቱን በባንክ ፕሬዚዳንትነት ሠርተዋል፡፡ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ከስምንት ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ካፈው አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ ደግሞ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪውና እሳቸው እየመሩ ባሉት የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር እንቅስቃሴ ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ 38 ዓመታት ቆይተዋልና ኢንዱስትሪውን እንዴት ይገልጹታል? ዕድገት እየታየበት ነው?

አቶ አዲሱ፡- ኢንዱስትሪው ደርግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የሶሻሊዝም ሥርዓትን ያራምድ ስለነበር ስፔሻላይዝድ ባንኮች ነበሩ፡፡ በወቅቱ ብዙ የውድድር መንፈስ የሌለበትና በአገልግሎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ ሦስት የመንግሥት ባንኮች ብቻ ሲንቀሳቀሱ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ስንገባ የግል ባንኮች መቋቋም እንደሚችሉ ተፈቀደ፡፡ የፋይናንስ ዘርፉም ሪብላራይዝድ ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት 16 የግል ባንኮች ተፈጠሩ፡፡ የመንግሥት ባንኮች ደግሞ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አሁን ከሦስት ወደ ሁለት ወረዱ፡፡ በአጠቃላይ አሁን የውድድር መንፈስ መኖሩ ባንኮች ወደ ደንበኞች እየቀረቡ እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደ ደንበኞች እየሄዱ ነው ሲባል እንዴት?

አቶ አዲሱ፡- ምክንያቱም ቅርንጫፎችን በብዛት እንዲከፍቱ አስችሏል፡፡ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተሠራባቸው ነው፡፡ በተለይ የካርድ ባንኪንግ፣ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓትን መጠቀሙ በጣም ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ ወደፊትም ኅብረተሰቡ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎትን በስፋት ይጠቀማል፡፡ እንዲህ ካሉ ሁኔታዎች አንፃር ባንኮች እያደጉና እየሰፉ መምጣታቸውን ያሳያል፡፡ ካፒታላቸው ከቀድሞው እየጨመረ ነው፡፡ ይኼ የባንኮችን ጥንካሬና ኃላፊነት የመውሰድ አቅማቸውን እንዲያጐለብቱ እያደረጋቸውም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዕድገታቸውን ይገልጻል? በሌላ በኩል ደግሞ የባንኮች ማቋቋሚያ ካፒታል መጠን እያደገ መምጣት አማራጭ ባንኮች እንዳይፈጠሩ እያደረገም ነው ይባላል፡፡  

አቶ አዲሱ፡- ዋናው ነገር ተደራሽነቱ ነው፡፡ የባንክ ቁጥሩ መብዛቱ አይደለም፡፡ አሁን እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ጥቂት ትልልቅ ባንኮች ነው ያሉዋቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥቂት ባንኮች እጅግ ብዙ ቅርንጫፎች አሉዋቸው፡፡ ተደራሽ ናቸው፡፡ ስለዚህ የባንኮች ቁጥር መብዛት ሳይሆን ተደራሽ መሆናቸው ነው መታየት ያለበት፡፡ ማዕከላዊ ባንኩም ሱፐርቫይዝ ለማድረግ ትልልቅ መሆናቸው ይመቸኛል የሚል እምነት አለው፡፡ በየቦታው ተበታትነው በሚገኙበት ጊዜ ለመቆጣጠር ያስቸግራል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የኢትዮጵያ የባንኮች ካፒታል ሲታይ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ አሁን ያላቸውን ካፒታል ወደ ዶላር ብትቀይረውና ከሌሎች አገሮች ባንኮች ጋር ብታወዳድረው፣ ባንኮቹ አላቸው የሚባለው ካፒታል ትንሽ ነው፣ ገና በማደግ ላይ ያለ ነው፡፡ ለእኛ አገር ብዙ ሊመስል ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኬንያ ባንኮች ያላቸውን ካፒታል እንኳን ወስደህ ከእኛ ጋር ብታስተያየው የእኛ አነስተኛ መሆኑን ትረዳለህ፡፡

ሪፖርተር፡- እርግጥ እንዳሉት የአገሪቱ ባንኮች ያላቸው የካፒታል መጠን አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ እያንዳንዱ ባንክ በተናጠል ያለው ካፒታል አነስተኛ በመሆኑ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱ ባንኮች ከዚህ በኋላ ወደ ውህደት መሄድ አለባቸው ወደሚል አመለካከት እየወሰደ ነው፡፡ በቅርቡም ሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮችም ተዋህደዋል፡፡ የግል ባንኮች መዋሀድ አለባቸው የሚለውን አመለካከት በማኅበራችሁ በኩል የተነጋገራችሁበት ነው? በእርግጥስ የግል ባንኮች እየተዋሀዱ ሊሄዱ ይችላሉ? በዚህ ላይ የግል አስተያየትዎ ምንድነው?

አቶ አዲሱ፡- በነገራችን ላይ ውህደትና ‹አኩዩዚሽን› ሲባል በሌላው አገር በጣም የሚጠቀሙበት ነው፡፡ እኛ አገርም በጉልበትም ቢሆን በሶሻሊዝም ሥርዓት ወቅት ባንኮች አንድ ላይ ተጨፍልቀው ነበር ሦስት መንግሥታዊ ባንኮች የሆኑት፡፡ በሒደትም ደግሞ እንደ አዲስ ባንክ ያሉት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተዋሀዱበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ የኮንስትራክሽንና የቢዝነስ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተዋህዷል፡፡ ይኼንን ውህደት ሕጉን ጠብቆ ማከናወኑ ትምህርት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይኼ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ውህደት በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችልም መታሰብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ ውህደቶች ሊፈጠሩ የሚችሉበት ምክንያት ምንድነው? እርስዎ እንዳሉት ምክንያት የሚሆነው ነገር ምንድነው?

አቶ አዲሱ፡- አንዱ ባንኮች ችግር ውስጥ ሲወድቁ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የተሻለ አቅም ለመፍጠር ነው፡፡ ተቀራራቢ አቅም ያላቸውም ቢሆኑ የሚዋሀዱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ አንዱ ባንክ በአንድ የባንክ አገልግሎት ጠንካራ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ባንክ በሌላ አገልግሎት ጠንካራ ነው ከሚባለው ባንክ ጋር በመዋሀድ ገበያ ውስጥ ተሰሚነት እንዲኖረው የማድረግ አሠራር አለ፡፡ በእኛ ሁኔታ ሲታይ የወደፊቱ አቅጣጫ ውህደት ሊኖር ይችላል፡፡ ግን በማኀበራችን ደረጃ አሁን በስፋት ይዘን የሄድንበት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ነገሩን እያሰብንበት ነው፡፡ ምን ዝግጅት ያስፈልጋል የሚለውንም እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ባንኮች ወደ ውህደት ቢሄዱ ይሻላል የሚለው ሐሳብ በሰፊው እየተነገረ ቢሆንም፣ አሁን ያሉት አብዛኞቹ የግል ባንኮች አፈጣጠር ግን እርስ በርሳቸው ለመዋሀድ የማያመች ነው ይባላል፡፡ ምክንያቱም አንድን ነገር ማዕከል በማድረግና በቡድተኝነት የተቋቋሙ በመሆናቸው፣ አንዳቸውን ከሌላው ማዋሀድ ሊያስቸግር ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ማኅበራችሁ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለው? ሥጋቱንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ አዲሱ፡- ያልከው ነገር አለ፡፡ በስፋት እንደሚታወቀው የባንኮች ባለአክሲዮኖች ጓደኛሞች፣ የአንድ አካባቢ የሆኑ፤ አንዳንድ ጊዜም በሃይማኖትና በመሳሰሉት መንገዶች የተቋቋሙ ናቸው በማለት የሚሰጡ አስተያየቶች አሉ፡፡ ይህ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል አመለካከት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ካፒታል ድንበር ስለሌለው አዋጭ ወደሆነ ቢዝነስ መሄድ አለበት፡፡ ስለዚህ የባንኮች ውህደት ወደድንም ጠላንም የማይቀር  ነው፡፡

በአገርም ደረጃ ስንመለከት የአውሮፓ አገሮች በፖለቲካው ገና ቢሆኑም፣ በኢኮኖሚ የገንዘብ ኅብረት እየፈጠሩ ነው፡፡ ይህንን ያደረጉት እንጠቀማለን በሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጥቅም የሚያስገኝና አትሪፊ እስከሆነ ድረስ ምንም ጥያቄ የለውም፣ የአገራችንም ባንኮች ወደ ውህደት ይሄዳሉ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሳይወድ በግድ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመርያም መጀመሪያ በፈቃደኝነት እንዲሆን ዕድል ይሰጣል፡፡ ሁለተኛ በዕርምጃ ሊያስገድድ ይችላል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ጣልቃ ገብቶ እንዲዋሀዱ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የመጨረሻውን ምርጫ ማንም የሚፈልግ አይኖርም፡፡ ሁለተኛውንም ብናይ ነገሩ በጉልበት ከሚሆን አስቦበትና ተዘጋጅቶበት ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ ውህደትና አኩዩዚሽን የተለመደ ነው፡፡ እኛም ዘንድ ቢሆን ይህ የማይሠራበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በውህደት ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ማድረግ አለባችሁ ያላችሁ ነገር አለ?

አቶ አዲሱ፡- የለም፡፡ ግን መመሪያ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት መመርያ?

አቶ አዲሱ፡- ባንኮች ከፈለጉ መዋሀድ ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ ብሔራዊ ባንክ እንዲዋሀዱ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

ሪፖርተር፡- መመርያው ላይ እንዲህ በግልጽ የተቀመጠ ነገር አለ?

አቶ አዲሱ፡- አዎ አለ፡፡ ይኼ በየትኛውም አገር ያለ ነው፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) ስትገባና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸ አገሮች ጋር ስትቀላቀል ክፍት የምናደርጋቸው ዘርፎች ይኖራሉ፡፡ ባንኮችም ክፍት ይሆናሉ፡፡ ወደ የዓለም ንግድ ድርጅት የምንገባው መቼ ነው? የሚለው ባይታወቅም መግባታችን ግን ስለማይቀር መዘጋጀት አለብን፡፡ ምክንያቱም የሌሎችን አገሮች ልምድ ስናይ ጐረቤቶቻችን እንኳን ታንዛንያ፣ ኬንያ ባንኮች ጠንካራ ባልሆኑበት ሁኔታ የውጭዎቹ ሲገቡ የአገር ውስጥ ባንኮችን ደፍጥጠው የውጭዎቹ የበላይነት ይይዛሉ፡፡ ስለዚህ የአገር ተጠቃሚነት መታሰብ አለበት፡፡ እነሱ ምን ተጠቀሙ ስንል በአብዛኛው ተጠቃሚዎቹ የውጭ ባንኮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የተሻለ ካፒታል፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ይዘው የሚገቡት የውጭዎቹ ናቸው፡፡ በቀላሉ ይቆጣጠሩታል፡፡ ስለዚህ እኛም በዚያ ደረጃ ማደግ አለብን፡፡ ከወዲሁ መዘጋጀት አለብን፡፡ ይህንን ካላደረግን ያስቸግራል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ግድ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የአገር ውስጥ ባንኮች እንዲጠናከሩ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ስለዚህ የአገሪቱ ባንኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በስትራቴጂ ደረጃ የቀረፃችሁት ዕቅድ አለ ወይ? እርግጥ የመንግሥት ዕቅድ አለ፡፡ ባንኮች እዘህ መድረስ አለባቸው ብሎ ያስቀመጠው ነገር ቢኖርም በማኅበራችሁ ደረጃ ምን የተሠራ ነገር አለ?  

አቶ አዲሱ፡- እዚህ ላይ ማኅበሩ የተቋቋመበት ዓላማ መታየት አለበት፡፡ ለምን ተቋቋመ ሲባል የምናገኛቸው መልሶች አሉ፡፡ እርግጥ ከማናቸውም ጉዳይ በላይ ይህንን ጉዳይ እናያለን ብለናል፡፡ በማኅበራችን በኩል የባንክ ኢንዱስትሪውን በሚመለከት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዳስጠናነው ሁሉ ለዚህም ዕድል እንሰጣለን፡፡ ለዚያ የሚደረገው ዝግጅት ምን ይሁን የሚለውን እናያለን፡፡ አማካሪ ድርጅት ቀጥረንም ቢሆን ባንኮች ይኼን አቅጣጫ አውቀው እንዲጓዙ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የተለመደ ነው፡፡ መሆንም ያለበት ነው፡፡

ሪፖርተርማኅበራችሁ የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪን የተመለከቱ ብዙ ጥናቶችን አስጠንቷል፡፡ ጥናቱንም ለተቆጣጠሪው ብሔራዊ ባንክ ጭምር አቅርቧል፡፡ በጥናታችሁ መሠረት ውጤት የተገኘበት ነው የምትሉት ነገር አለ? የእናንተ ጥናት ግብዓት ምን ያህል ጠቅሟል ማለት ይቻላል?

አቶ አዲሱ፡-  ይኼ ወደ ሰፊ ጉዳይ ሊያስገባን ነው፡፡ የማኅበሩ ዓላማ ተነስቶ ምን ምን ሥራዎች ሠራ? ብሎ ማየትም ያስፈልጋል፡፡ ዓላማው በአባል ባንኮች መካከል የመተባበርና የመተማመን መንፈስ መፍጠር፤ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ በባንክ ኢንዱስትሪው ዕድገትና መስፋፋት ላይ መሥራት ነው፡፡ ይኼ በቋሚነት በየወሩ አሥራ ሁለት የቦርድ አባላት ተገናኝተው ይመክሩበታል፡፡ በየስድስት ወራት ደግሞ የአባል ባንኮች ፕሬዚዳንቶች ኢንዱስትሪውን በሚመለከት እኛ ባቀድነው መሠረት እየተጓዘ ነወይ? የሚለውን ተሰብስበን ውሳኔ እናሳልፋለን፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ጋርም በየሦስት ወራት ተገናኝተን እንወያያለን፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም እያየንና እየመከርን የሚፈቱበትን መንገድ የጋራ መድረክ ፈጥረን እየሠራንበት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በማኅበሩ በኩል ተሠርተዋል ብለን የምንጠቅሳቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ባንኮች ለብድር ዋስትና የሚይዙዋቸው ንብረቶች ወጥ የሆነ ቋሚ አሠራርን የሚመለከት ነው፡፡ አንድ ባንኮች ለብድር ንብረት ሲገምቱ በተቻለ መጠን ገበያውን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ አንድን ተመሳሳይ ንብረት አንዱ ባንክ አንድ ሚሊዮን ብር ሌላው ደግሞ አራት ሚሊዮን ብር በማለት የሚገምትበት አሠራር ነበር፡፡ ይህንን ያህል ልዩነት ለምን ይፈጠራል ብለን በባንኮች ደረጃ ተነጋግረን፣ አማካሪ ቀጥረን አስጠንተን ደረጃውን የጠበቀ ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡ ይኼ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ አሁን ድጋሚ እየተከለሰ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የጋራ ጠቀሜታ ያላቸው የማጣሪያ ቢሮዎች፣ የገንዘብን ዝውውር ሥርዓቶች፣ እንዲሁም በባንኮች መካከል የሚደረግ የእርስ በርስ የብድርና የገንዘብ ገበያን የመሳሰሉ የባንክ ሥራዎችን ማደራጀትንና ማራመድ፣ በማኅበሩ አባላት መካከል አለመግባባት ሲፈጠር አለመግባባቱ በእርቅ ወይም በግልግል እንዲያልቅ ጥረት ማድረግና የመሳሰሉትን ሥራዎች በመሥራት ላይ ነው፡፡   

ኢትስዊችን በጋራ መሥርተናል፡፡ የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን የሠራነው ሥራ ነው፡፡ ሥራው በቅርቡ ይጀመራል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በተመባበር የቼክ ስታንዳርዳይዜሽን ፕሮጀክት ጥናት ተደርጎ እንዲተገበር አድርገናል፡፡ ባንኮች ላይ የሚፈጸምን ማጭበርበር ላይ ሥራ ሠርተናል፡፡ የኮሚሽን መቆራረጥ ላይ ያለውን ችግርና የመብራት ችግርን ለመቅረፍ የተሠራም አለ፡፡ ማኅበሩን ለማጠናከር መዋቅር አስጠንተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለብድር ማስያዣነት የሚውሉ ንብረቶች ወጥ የሆነ ተመን ይኑራቸው የሚለውን አሠራር እንዲተገበር ስታደርጉ የመቆጣጠሪያ ሥልትስ አላችሁ?

አቶ አዲሱ፡- መታየት ያለበት ማኅበራችን በጎ ፈቃደኛ ማኅበር ነው፡፡ አንድ ባንክ የተስማማንበትን ነገር ሲጥስ ልክ ተቆጣጣሪ ባንኩን እንደሚያደርገው የምንቀጣበት ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ እንወያይበታለን፡፡ እንተማመንበታለን፡፡ ከዚያም የማስፈጸም ጉዳይ ነው፡፡ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ተገናኝተን እንነጋገርበታል፡፡ ይኼ ነገር ችግር እያስከተለ ነው ብለን የምንናገርበት መድረክ አለ፡፡ ከዚህ ሥራ ጐን ለጐንም ለባንኮች የሥነ ምግባር ደንብ ተቀርፆ እንዲሠራበት ለማድረግም ማኅበሩ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከሁሉም በላይ የፋይናንስ ዘርፉን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች ሲወጡ በየጊዜው እንገመግማለን፡፡ የማሻሻያ ሐሳቦችን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል የማቅረብ ሥራ ሠርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ካቀረባችኋዋቸው ማሻሻያዎች ተፈጻሚ ሆነውልናል የምትሉዋቸው አሉ?

አቶ አዲሱ፡- ለምሳሌ በ1954 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ቁጥር ሕግ ቁጥር 1723 በባንኮች ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሕግ ማሻሻያ ለመንግሥት ቀርቦ ማሻሻያው እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የማሻሻያው ሐሳብ በማኅበሩ በኩል የቀረበ ነው፡፡ ማሻሻያውም ተበዳሪዎች በፍርድ ቤት በባንኮች ላይ ክስ እየመሠረቱ ያስያዙትን ንብረት ነፃ ለማድረግ ያደርጉት የነበረውን እንቅስቃሴ እንዲገታ አድርጓል፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ባቀረብነው ሐሳብ ላይ ተመሥርተው የተስተካከሉ ነገሮች አሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣቸው መመርያዎችና ደንቦች ላይ ማሻሻያ አቅርበን የእኛን ሐሳብ ተቀብሎ ያስተካከላቸው አሉ፡፡ በአንፃሩም በዚሁ እፀናለሁ ብሎ የሄደበትም ሁኔታ አለ፡፡ ሐሳባችን ያልተተገበሩበት አጋጣሚዎችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- መቼም ብሔራዊ ባንክ ሐሳባችሁን አንቀበልም ብሎ ከፀናባቸው ጉዳዮች አንዱ ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ ያውሉት የሚለው መመርያ እንደሚሻሻል ጥያቄ ያቀረባችሁበት ይመስላል፡፡

አቶ አዲሱ፡- አዎ፡፡ ይህ መመርያ ሊስተካከል ይገባል ብለን ከብሔራዊ ብንክ ጋር አራት አምስት ጊዜም ተሰብስበናል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ከማስተካከል ውጪ እኛ ባቀረብነው መንገድ ሊስተካከል አልቻለም፡፡  

ሪፖርተር፡- የብዙ ባንኮች ቀዳሚ ጥያቄ ግን ይህ 27 በመቶ መመርያ ሊለወጥ ይገባል የሚል ነው፡፡ ቢያንስ ይስተካከልም የሚሉ ነበሩና ይህንን የባንኮችን ሐሳብ አንፀባርቃችኋል?

አቶ አዲሱ፡- ይህንኑ የባንኮች ጥያቄ ይዘን ለብሔራዊ ባንክ በተደጋጋሚ አቅርበናል፡፡ ያውም በጥናት አስደግፈን ጭምር ነው ያቀረብነው፡፡ እንዲያውም እኛ መጀመሪያ ላይ ያቀረብነው ሐሳብ በተለይ ይህ መመርያ አዳዲስ ባንኮችን ይገላል የሚል ነው፡፡ ነባር ባንኮችም የተወሰነ ጊዜ ሊሠሩ ይችላሉ እንጂ ያጠፋቸዋል የሚልም ሐሳብ ይዘን ቀርበን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ነገር ግን የታሰበው አልሆነም? እንዲያውም መመርያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የባንኮች አትራፊነታቸው  እየጨመረ መምጣቱ  ብዥታ ፈጥሮ ነበር፡፡ ቀድሞ ከታሰበው ውጪ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ አዲሱ፡- ከእኛ ሥጋት ውጭ ባንኮች አትሪፊነታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በ27 በመቶ እየሠሩ የሚያወጡትን ገንዘብ ለመተካት፣ ባንኮች ቅርንጫፋቸውን በማስፋፋት ተቀማጭ ገንዘባቸውን ለማሳደግ ካደረጉት ጥረት ጋር ይያያዛል፡፡ መመርያው አተጋቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ትርፋቸው እየጨመረ የመጣው፡፡ ተደራሽነታቸው በጣም ጨመረ፡፡ ኢኮኖሚውም እያደገ በመምጣቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህ መመርያ ላይም ብሔራዊ ባንክ ከመጀመሪያው ጀምሮ እናንተን ለመግደል ብዬ መመርያ አላወጣም ሲል ነበር፡፡ የቆምኩት ጤናማ በሆነ መንገድ እንድትሠሩ ለመርዳት እንጂ፣ ለማጥፋት አይደለም ብሎ በዚህ ጉዳይ ላይ የምታቀርቡት ጥያቄ መሠረት የለውም የሚል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- 27 በመቶው መመርያ እናንተ ካሰባችሁት ውጪ ቢሆንም ጉዳት የለውም ማለት ይቻላል?

አቶ አዲሱ፡- እንደኔ እንደኔ ይህ መመርያ አትግቶናል፡፡ የራሱ ተፅዕኖም አለው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በ27 በመቶው መመርያ የሚሰበስበው ገንዘብ የሚውልበት ዓላማ ስንመለከት ደግሞ በተለየ የምናይበትን ስሜት ይፈጥራል፡፡ በ27 በመቶው የሚሰበሰበው ገንዘብ ወደ ልማት ባንክ ገብቶ ለእርሻና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብድር ይውላል፡፡ ይህንን በማድረጉ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ለእኛ ሥራ እየፈጠረልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ አዲሱ፡- እነዚህ ተበዳሪዎች ከልማት ባንክ በወሰዱት ብድር የሚሠሩትን ሥራ ቆይተውም ቢሆን ከባንኮች ጋር ነው የሚሠሩት፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ከእኛ ጋር ነው የሚሠሩት፡፡ ግድቡ ላይ ነው የሚውለው ከተባለ ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረግ ትልቅ የዜግነት አስተዋጽኦ ነው፡፡ ይህ የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መመርያው አትግቶን ብዙ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ብንችልም፣ 27 በመቶውን ገንዘብ ብናበድረው የምናገኘው ትርፍ ሊጨምር ይችል ነበር፡፡ ይህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተሻለ ትርፍ ይገኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የዚህ መመርያ ተፅዕኖው እንደታሰበው ባለመሆኑ ሊያሻሽል ይገባል ብላችሁ ታቀርቡ የነበረውን ጥያቄ እንድታቋርጡ ያደርጋል ማለት ነው?

አቶ አዲሱ፡- ጥያቄው አለ፡፡ እናቀርባለን፡፡ እኛ እንዲያውም የምንለው ቋሚ ይሁን፣ ወይም ከተቀማጫችንና ከብድራችን ጋር ይስተያይ የሚል ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ለ27 በመቶው የምናስቀምጠው ገንዘብ የሚታሰብልን ወለድ ወጪያችንን ሊሸፍን ይገባል፡፡ ምክንያቱም አምስትና ከዚያም በላይ በሆነ ወለድ ከፍለን የምንሰበስበውን ገንዘብ ለቦንድ ግዥው ሲውል የሚታሰብልን ሦስት በመቶ ወለድ ነው፡፡ በሦስት በመቶ ወለድ ማስቀመጡ ኪሳራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በባንኮች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ማኅበራችሁ የሚገባበት አሠራር እንዳለ ይነገራል፡፡ ለግጭቶቹ ምን ዓይነት መፍትሔ ሲሰጥ ነበር?

አቶ አዲሱ፡- በባንኮች መካከል ግጭቶች አሉ፡፡ ግጭቶችን እንይዝና አንድ ቡድን አቋቁመን ለየብቻ እናነጋግራቸዋለን፡፡ ቡድኑ የውሳኔ ሐሳብ ለቦርዱ ይቀርባል፡፡ ቦርዱ ደግሞ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ባሉ የማጣራትና የመሸምገል ሥራችሁ የቀጣችኋቸው አሉ?

አቶ አዲሱ፡- የቀጣናቸው ባንኮችም አሉ፡፡ በአንድ ድርጊት የተፈጸመ ግድፈት ሲኖር እከሌ ባንክ ለእከሌ ባንክ ይህንን ያህል ብር ክፈል ብለን በገንዘብ ጭምር ውሳኔ የሰጠንበት ጊዜ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲያው የቅጣቱን መጠንና የቅጣቱን ምንጭ ይነግሩናል?

አቶ አዲሱ፡- እሱ ይቆይ፡፡

ሪፖርተር፡- ከማኅበሩ ዓላማዎች አንፃር ባንኮች እርስ በርስ ገንዘብ እንዲበዳደሩ ማድረግ የሚለውን ጠቅሰውልኛል፡፡ ይህ ተፈጻሚ እየሆነ ነው? የሚታወቀው ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ሲበደሩ ነው፡፡

አቶ አዲሱ፡- መበዳደር ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ አሁን ገና ነው፡፡ ነገር ግን ‹ታይም ዲፖዚት› የሚባለውን እናስቀምጣለን፡፡ እንደ ብድር ማለት ነው፡፡ ዋስትና አስይዞ መበደር ላይ ግን ገና ነው፡፡ የማኅበሩ ሥራ ከዚህም በላይ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአባል ባንኮች ጥበቃና ደኅንነት የተረጋገጠ እንዲሆን የጦር መሣሪያ የሚገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት ግን ባንኮች ለጥበቃ የሚሆን የጦር መሣሪያ ፈቃድ ለማግኘት ተቸግረው ገንዘባችንን በዱላ እየጠበቅነው ሲሉ ይሰማ ነበር፡፡ ይህንን ችግር መቅረፍ ተችሏል ማለት ነው?

አቶ አዲሱ፡- አሁን ተፈቅዷል፣ ወስደዋል፡፡ በፊት በነፃ የሚሰጥ ነበር፡፡ አሁን ገንዘብ እየከፈልን እየወሰድን ነው፡፡ ማኅበሩ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን ችግሩ እንዲፈታ አድርጓል፡፡ በቂ መሣሪያ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለደኅንነትና ለጥበቃ አባላትም በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና በጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥልጠና እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ (ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች) አሉባቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ክፍተቶች ውስጥ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የራሳቸው የማሠልጠኛ ተቋም የላቸውም የሚለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠርቷል፡፡ የግል ባንኮች ግን የባለሙያዎች እጥረት እያለና በዚሁ ምክንያት ሠራተኞች እስከመነጣጠቅ እየደረሱ የሰው ኃይል ማብቂያ ማዕከል የላቸውም፡፡ ለምን?

አቶ አዲሱ፡- በነገራችን ላይ ማኅበሩ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አለው፡፡ ከዕቅዱ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ ይህንን የሥልጠና ማዕከል ማቋቋም ነው፡፡ አስፈላጊነቱንም በማየት ተባብረን ብንሠራው ይሻላል በሚል መንፈስ እየተንቀሳቀስንና እየተዘጋጀን ነው፡፡ ከቻልን ሕንፃ ገንብተን፤ ካልቻልን ተከራይተን ለመሥራት አስበናል፡፡ ምክንያቱም ሠራተኛን በማብቃት ጉዳይ ከፍተኛ ክፍተት ያለብን ስለሆነ ይህንን እንሠራለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ተመካክረናል፡፡ አቃቂ ያለው የብሔራዊ ባንክ ማሠልጠኛ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በደረጃ እየተመለሰለት ነው፡፡ ይህንን ለመጠቀም ይቻላል ተብለናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንም የልቀት ማዕከል እየተጠቀምን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባንኮች መካከል የባለሙያዎች መነጣጠቅ ብዙ ሲተችበት ቆይቷል፡፡ ይህ መነጣጠቅ ባንኮችን እርስ በርስ ያጋጨም ነው ይባላል፡፡ ድርጊቱ የባንኮችን ወጪ እስከማናር ደርሷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በማኅበራችሁ በኩል የወሰዳችሁት ዕርምጃ አለ?

አቶ አዲሱ፡- በተደጋጋሚ ተነጋግረንበታል፡፡ ከሥር ከመጀመሪያ ደረጃ የምንወስደውን ማጠናከር አለብን፡፡ ሥራ ከተሠራ ሠራተኞች በሚለቁበት ጊዜ ከታች ያሉት የሠለጠኑ እስከሆኑ ድረስ ይተኳቸዋል፡፡ የሥልጠና ማዕከሉ ቢኖር ደግሞ እናበቃላቸዋለን፡፡ ሠራተኞች ሲለቁ እንተካላቸዋለን፡፡ አሁን መነጣጠቁን በተመለከተ በመካከለኛ ማኔጅመንትና ከዚያ በላይ ያለውን ደግሞ በራሱ በምርጫ የሚሄድ ነው፡፡ ሕጉ የሠራተኞችን ዝውውር በተመለከተ ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ ሌላው ሠራተኛ ቢሆን ክፍት ነው መሄድ ይችላል፡፡ ግን ሌላውን ባንክ የሚጎዳ መሆን የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ መወሰድ አለበት፡፡ አንድ ባንክ ውስጥ ያለ የአይቲ ባለሙያ ምትክ የሌለው ዓይነት ነገር ከሆነ፣ ይህንን አማልሎ መውሰድ ሥራው እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክም እንዲህ ያለው ችግር እንዳይፈጠር ያስገደደው ነገር አለ፡፡ ለሥልጠና ትልቅ ወጪ መደረግ አለበትም ብሏል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ ባንኮች ከጠቅላላ ወጪያቸው ሁለት በመቶውን ለሥልጠና መያዝ አለባቸው፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ለውጥ ያመጣል፡፡ ተተኪዎችንም የማዘጋጀት ሥራ ይሠራል፡፡ ይህ ትልቅ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ እኛም ክፍተቱን ለመድፈን ከሥር እያፈራን መሄድ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመቅረፍ በማኅበራችሁ በኩል ምን ሠርታችኋል? ችግሩስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አዲሱ፡- የውጭ ምንዛሪ እጥረት በብዙ አገሮች ያለ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪውን ቆንጥጠው ይዘው ነው የሚያስተዳድሩት፡፡ እንደኛ ያለ ታዳጊ አገር በተለይ ዕድገት እየታየ በመጣበት አገር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ፍላጎቱና አቅርቦቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክም ባደረገው ጥናት እንዳሳየው ከእጥረቱ ጋር ተያይዞ በማኔጅመንት አካባቢ ችግር መፈጠሩን ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በምንመለከትበት ጊዜ ከእርሻ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወቅታዊነት አለው፡፡ ዓመቱን በሙሉ የእርሻ ምርቶች ወደ ውጭ ስለማይላኩ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ክፍተት አለ፡፡ ከየካቲት ጀምሮ እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ቡና በዚህ ወቅት የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ይመጣል ብለን ኤልሲ እንከፍታለን፡፡ ነገር ግን ይመጣል የተባለውን ያህል የውጭ ምንዛሪ የማይመጣ ከሆነ ከዚህ ጋር ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ሁለት ሦስት ወር ይፈጅ ይሆናል፡፡ ይህ የኛንም ሆነ የአገሪቷን ገጽታ ያበላሻል፡፡ ስለዚህ ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ ከሌለ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ አዲሱ መመርያ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ የሚሰጥበትን አሠራር አስቀምጧል፡፡ ቅድሚያ የትኛው ይሰጠዋል በሚልም የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ መጀመርያ ለመጣ መጀመርያ ይሰጣል፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ለተባለው ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ ችግር ሲነሳ አንዳንድ ባንኮች ውስጥ በኮሚሽን የሚሠሩ በአንድ ዶላር ይህንን ያህል ጥቅም አስቡልን የሚሉም አሉ ይባላል፡፡

አቶ አዲሱ፡- እንዲህ ያለ ነገር በድብቅ የሚሠራ ነው፡፡ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ማረጋገጥ ያዳግታል፡፡ ከሁሉም በላይ በማኅበራችን በኩል የተነጋገርንበት ግልጽ አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ ከእጥረቱ አንፃር ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግም፣ በኃላፊነት እንዲሠራ እያደረግን የሥራ መሪዎች ኃላፊነትም ከፍተኛ ነው፡፡

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...