Tuesday, March 5, 2024

የሃምሳ ዓመታት የምርምር ጉዞና ግብርናውን የማዘመን ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሰባዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙት አዛውንቱ አርሶ አደር አረፈ አድሃኔ በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምሥራቅ ከውቅሮ ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘው የሉጉዳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሙሉ የዕድሜ ዘመናቸውን በግብርና ሥራ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በማስተዳደር ላይ የሚገኙ የአካባቢው አርሶ አደር ናቸው፡፡ ዝናብ ጠብቀው በክረምት አርሰዋል፣ በፀደይ ወራት በቡቃያው ተስፋ አይተዋል፣ አጭደዋል፣ ምርት ሰብስበዋል፣ በበጋው ወራት ምርት ለገበያ አውጥተው ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡ በሸጡትም ለየዕለት ኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ አስቤዛ ሸምተዋል፡፡

2008 ዓ.ም. ገና ከጅምሩ ሲገባ ግን ለአዛውንቱ አርሶ አደር አረፈ አዲስና ብሩህ ዓመት አልነበረም፡፡ እንዳለፉት ከ60 ዓመታት ያዩት ዓይነት ሳይሆን አስደንጋጭ ‹‹ዓመተ ፍዳ›› ሆኖ እንደመጣባቸው ከገጽታቸውም ሆነ ከአገላለጻቸው ይነበባል፡፡ ዘንድሮ በወርኃ ጥቅምት አካባቢ ከግማሽ ሔክታር በማትበልጥ የስንዴ እርሻ ውስጥ አጎንብሰው፣ ለጎተራ የማትበቃ ቡቃያ በእጃቸው በመንቀል ተጠምደው ነበር፡፡ ‹‹ይህች ምኗ ለማጭድ በቅታ ነው ማጭድ የሚያርፍባት?›› ሲሉ ኤልኒኖ ባስከተለው የዝናብ እጥረት ፍሬ ማፍራት ያልቻለውን ቡቃያ ለምን በእጃቸው መሰብሰብን እንደመረጡ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ በሉጉዳና አካባቢው ድርቁ በፈጠረው ተፅዕኖ ቀደም ብለው ዘር ዘርተው ፍሬ አልባ ቡቃያ የሆነባቸው፣ ለአርሶ አደሩ ቤተሰብ ለምግብነት የሚውል በቂ ምርት ባለማግኘታቸው የተነሳ ቡቃያውን ለከብቶች መኖነት ያዋሉት አንዱ እኚሁ አዛውንቱ አረፈ ናቸው፡፡ ‹‹በሕይወት ዘመኔ እንዲህ አስደንጋጭ ጊዜ አይቼ አላውቅም፤›› በማለት አዛውንቱ ያክላሉ። በርግጥም የእሳቸው ችግር የአንድ ገበሬ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በዝናብ ላይ የተመሠረተው የአገሪቱ የግብርና ይዞታ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አንድ ማሳያ ነው፡፡

በአንፃሩ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ከሚገኙትና መልክዓ ምድራ አንድ በሆነው የአርሲ አካባቢ የ58 ዓመቱ አርሶ አደር አበበ ደገፋ፣ በዚሁ የዝናብ በረከት ላይ በተመሠረተው የግብርናው ዘርፍ ከሚተዳደሩት አንዱ ናቸው፡፡

በወርኃ ኅዳር ከሁለት ሔክታር በላይ በሆነ የእርሻ መሬት ላይ የተንጣለለው የስንዴ ቡቃያ፣ ለአርሶ አደሩ አበበ ያላበሳቸውን ዕርካታና ከወራት በኋላ ሊያጎናፅፋቸው የሚችለውን ገቢ ታላቅነት ፈካ ብሎ ከሚታየው ገጽታቸው ለማወቅ አያዳግትም፡፡ በአርሶ አደሩ አበበና በትግራዩ አዛውንት አረፈ የምርት ዘመኑ ያበረከተላቸው ፈፅሞ የተቃረነና ልዩነቱ የሰፋ ነበር፡፡

በእርግጥ በአገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ ከሚሸፍነው በግብርና ሥራ ላይ ኑሮውን ከመሠረተው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ፣ ሞዴል አርሶ አደር ተብለው ከሚጠሩት መካከል አንዱ የአርሲው አቶ አበበ ናቸው፡፡

የአርሲ አካባቢ የዘንድሮ የዝናብ እጥረት ብዙም ተፅዕኖ ካላሳደረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም የአርሶ አደር አበበ የስንዴ እርሻ እንደ ጥሩ ማሳያ ተደርገው 50ኛውን የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለጉብኝት ከተመረጡት አንዱ የእርሻ ማሳ ነበር፡፡ አርሶ አደሩም በተቋሙ ሥር ከሚተዳደሩ የምርምር ማዕከላት አንዱ በሆነው የቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በምርጥ ዘር፣ በግብርና ቴክኖሎጂና በባለሙያ የክትትል ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሞዴል አርሶ አደሮች ውስጥ ይገኙበታል፡፡

‹‹በምርምር ተቋሙ ከሚደረግልኝ እገዛና የምርጥ ዘር አቅርቦት በተጨማሪ በአካባቢያችን ቴክኖሎጂን በመጠቀሜና ሞዴል አርሶ አደር በመሆኔ የሚሰማኝ ኩራት ትልቅ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት የምሰበስበው የምርት መጠን እየጨመረ ነው፤›› በማለት ነበር ሪፖርተር በወቅቱ በሥፍራው በመገኘት ለጠየቃቸው ጥያቄ የመለሱት፡፡ የተመሠረተበትን የወርቅ ኢዮቤልዩ አስመልክቶ ዓመታዊ ዝክረ በዓሉን ቀደም ብሎ የጀመረው ኢንስቲትዩቱ፣ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ጀምሮ ያለፈባቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲያከብር ቆይቷል፡፡ ከጉዞና ጀምሮ በሲምፖዚየም፣ በዐውደ ርዕይ፣ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች የሃምሳ ዓመታት ጉዞውን በማክበር፣ የካቲት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል ለአንድ ሳምንት ባዘጋጀው የፖሊሲ አውጪዎች፣ የግብርና ተመራማሪዎችና ባለሟሎች በተሳተፉበት የምክክር መድረክ አጠናቋል፡፡

በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በራሱና በሚያስተባብራቸው ተቋማት ተግባራት በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት መስኮች የተከናወኑ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎችን በማወደስ ለአገሪቱ የግብርና ዕድገትና ምርታማነት ‹‹የጎላ አስተዋጽኦ›› ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ተቋሙ ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ጀምሮ በግብርናው እየተመዘገበ ባለው የምርታማነት ዕድገት ቁልፍ ሚና ነበረው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹የግብርና ቴክኖሎጂንና መረጃዎችን በማቅረብ ስኬታማ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፣ ይህ በሌሎች መስኮች ከሠራናቸው ተግባራት ጋር ተዳምሮ ግብርናችን እያስመዘገበ ለመጣው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የሰብልና የአዝርዕት ዓይነቶችን በመመራመርና ምርታማነታቸውን በማሻሻል የምርምር ተቋሙ ለግብርናው ዘርፍ ያመጣውን ዕድገት በዝርዝር ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በአገር በቀልና ከውጭ ገብተው በተላመዱ የእንስሳት ሀብት በመመራመርም የእንስሳት ዝርያ፣ አረባብና አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የሚቻለውን ያህል ጥረት ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡

‹‹የግብርና ምርምር ተቋማችን በየወቅቱ የሚፈለጉ ተስማሚ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ባያቀርብልን ኖሮ፣ ዛሬ የደረስንበት የምርትና የምርታማነት ደረጃ መድረስ አዳጋች ይሆን እንደነበር ለመገመት አይከብድም፤›› ሲሉም ዶ/ር ሙላቱ በውይይት መድረኩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት (በቀድሞው አጠራር የእርሻ ምርምር አንስቲትዩት) በ1958 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፣ ላለፉት 50 ዓመታት ለግብርና ልማቱ የሚሆኑ የተለየዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ መረጃዎችንና እውቀቶችን በማቅረብ አሁን ለተመዘገበው አገራዊ የግብርና ልማት ውጤት ከፍተኛውን ሚና መጫወቱን የተቋሙ  ሰነዶች ይገልጻሉ።

ኢንስቲትዩቱ በሰብል ምርምር ዘርፍ በብርዕና አገዳ፣ በጥራጥሬ፣ በቅባት እህሎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በመዓዛማና መድኃኒት ሰብሎች፣ በቅመማ ቅመሞች፣ በቡናና ሻይ፣ በኃይልና ሥነ ሕይወታዊ ነዳጅ ሰብሎች፤ በእንስሳት ምርምር መስክ በዳልጋ ከብቶች፣ በጋማ ከብቶች፣ በግና ፍየል፣ ዶሮ፣ ዓሳና ንብ ምርምሮች ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ደግሞ በአፈር አሲዳማነት፣ ጨዋማነት፣ ኮቲቻ አፈር ማጥፈፍ፣ በአፈር የኬሚካል፣ ኦርጋኒክና ሥነ ሕይወታዊ ማበልፀጊያ ዘዴዎች፣ በመስኖ፣ በመሬትና ውኃ አያያዝና ጥበቃ መስኮች ላይ የምርምር ተግባራትን ማከናወኑም እንዲሁ፡፡

በሰፊው የታወቁ እንደ ቢኤች 660 እና ቢኤች 540 ያሉ ዲቃላ በቆሎዎች፣ ቁብሳ የስንዴ ዝርያ፣ ቁንጮ የተባለው የጤፍ ዝርያ፣ የስፔሻሊቲና የዲቃላ የቡና ዝርያዎች፣ የምስርና የሽምብራ ዝርያዎች፣ የድንች ዝርያዎች ኢንስቲትዩቱ በአጠቃላይ የአገሪቱ የግብርና ምርምር ሥርዓቱና በአገራዊ የምርት ዕድገት ላይ ለነበረው የጎላ አስተዋፅኦ እንደ አብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው ተብሏል፡፡

 ከቴክኖሎጂ ሥርፀት አኳያም ስንዴ ከ62 እስከ 96 በመቶ፣ በቆሎ ከ56 እስከ 64 በመቶ፣ ጤፍ 76 በመቶ፣ ምስር 40 በመቶ፣ ሽምብራ 26 በመቶ፣ የቢራ ገብስ መቶ በመቶ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በሽምብራና በመሳሰሉት ሰብሎች ምርት ቀዳሚ እንድትሆን፣ በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ያለፉትን 50 ዓመታት ጉዞ በመሠረታዊነት መቀየር ይገባዋል ተብሏል፡፡ በአሠራር፣ በተደራሽነት፣ በትኩረት መስክ፣ በምርምር ዓይነት፣ አቅም፣ ወዘተ. ከፍታ በማምጣትና የለውጥ ተቋም በመፍጠር የልማቱን ችግሮች በብቃት ለመፍታት በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዎቹ ይገልጻሉ፡፡

የግብርና ዘርፉ ካለፉት 12 ዓመታት ጀምሮ በተከታታይነት እያስመዘገበው መጥቷል ተብሎ የሚነገርለት ዕድገት፣ በአገሪቱ አጠቃላይ እየተመዘገበ ላለው ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለው ድርሻ ቀዳሚነቱን እንደሚወስድ መንግሥት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ምንም እንኳ የዕድገት ጉዞው በተከታታይ የቀጠለ መሆኑን ቢነገርም፣ ግብርናው በሚፈለገው መጠን አድጓል ወይም ‹‹ትራንስፎም›› አድርጓል ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም በአገሪቱ የግብርናም ሆነ አጠቃላይ አገራዊ የኢኮኖሚ ዘርፍ ጎልቶ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የግብርናው ልማት ለረዥም ዓመታት ሲድህ ከቆየ በኋላ ትክክለኛ ፖሊሲ በመቅረፅ ግብርናንና ገጠርን ልማት ማዕከል በማድረግ፣ በቴክኖሎጂ እገዛ ላይ ትኩረት ሰጥቸዋለሁ ሲል መንግሥት ይደመጣል፡፡

ነገር ግን ከዝናብ ጥገኝነት ሊላቀቅ ያልቻለው የግብርናው ዘርፍ አሁንም ትራንስፎርም ማድረግ አለመቻሉን መንግሥትም ሆነ የተለያዩ የዘርፉ ባለሟሎች የተስማሙበት ሆኖ ይታያል፡፡

‹‹በርካታ የግብርናው ሴክተር ችግሮች የተሟላ መፍትሔ ያላገኙ በመሆናቸው ሴክተሩ ትራንስፎርም አላደረገም፤›› በማለት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ገልጸዋል፡፡ እንደ መንግሥት ሁሉ የዘርፉ ባለሟሎችን ግብርናው አገሪቱ የምትፈልገውን ያህል ትራንስፎርም አለማድረጉን ቢስማሙበትም፣ በዚህ ረገድ የሚያቀርባቸው ምክንያቶች ግን የተለያዩ ሆነው ይታያሉ፡፡

በውይይት መድረኩ ሰፋ ያሉና የተለያዩ ፍሬ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ቢደረግባቸውም፣ በተማራማሪዎችም ሆነ በመንግሥት ተወካዮች ሰፊ ክርክርና ውይይት የተደረገባቸው ሁለት ምክንያቶች እንደነበሩ ለማስተዋል ተችሏል፡፡ እነዚህም የመሬት ፖሊሲውና ከመስኖ ውኃ ዝቅተኝነትና የቴክኖሎጂ አቅምን ከመጠቀም ጋር የተያያዙ ዓብይ መነጋገሪያ ሆነው ተነስተዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከኢትዮጵያ የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የተወከሉት አቶ አጌና ጁሉ የግብርናው ዘርፍ ወደተሻለ ዕድገት ለማሸጋገርም ሆነ በአጠቃላይ በገጠር የሚደረገው የልማት ሥራ ከመሬት ፖሊሲ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ፣ ከመሬት ባለቤትነት ጋር ቀድሞ ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹ግብርናችንን ለማሸጋገር ስንንቀሳቀስ በገጠር መሬት ፖሊሲ አጠቃቀም ባለቤቱ ማነው የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ነው? ወይስ የሌላ አካል? ምክንያቱም የተለያዩ ክፍሎች የተለያየ አደረጃጀት ነው ያላቸው፡፡ ይህን ሊመልስ የሚችልና ወጥ በሆነ መንገድ ሊመራ የሚችል ማንስ ነው? ፖሊሲው እስከ መቼ ነው መሬት ወርዶ የሚተገበረው?›› በማለት ከገጠር ልማት ፖሊሲና የግብርና ምርት ከማሳደግ ሒደት ጋር ተያያዥነት አላቸው ያሉዋቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ከትግራይ ግብርና ምርምር ማዕከል የመጡት አቶ ተስፋይ ብርሃኔ ሲሆኑ፣ ‹‹መሬት እንዲህ ተቆራርጦ እንዴት ግብርናውን ማሸጋገር ይቻላል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ተስፋይ ባቀረቡት ሐሳብ አርሶ አደሩ አሁን በነፍስ ወከፍ ከያዘው አነስተኛ የእርሻ መሬት ከፍ ብሎ ሰፋፊ እርሻ ላይ ተሰማርቶ በሜካናይዝድ አስተራረስ ካልታገዘ፣ የአገሪቱ ግብርና ከሥጋት ሊላቀቅ የማይችል ግብርና ሆኖ ይቀራል ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

እኚህ ባለሙያ የአገሪቱ ሌላኛው ተግዳሮት ሲሉ ያመለከቱት ተጨማሪ ጉዳይ፣ የአገሪቱ አማካይ የድኅረ ምርት ብክነት ከፍተኛ መሆኑንና ለብዙ ዘመናትም መሻሻል አለማሳየቱን ነው፡፡ እሳቸው አማካይ የድኅረ ምርት ብክነት 30 በመቶ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርናው ዘርፍ ምርታማነት እያሳየ ያለው ዕድገት፣ በአጠቃላይ አገሪቱ በዘርፉ የሽግግር ተስፋ እያያችበት የሚመስል ምልክት ቢሆንም፣ በየጊዜው የሚከሰተው የድርቅ አደጋና ያስከተለው የምግብ እጥረት በግብርናው ዕድገት (ሽግግር) ላይ ‹‹አስደንጋጭ›› ጥያቄ እንደጫረባቸው የሚገልጹት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃኔ ገብረ ኪዳን ናቸው፡፡

‹‹ይህ የኤልኒኖ ክስተት እስከመጣ ጊዜ ድረስ ግብርናችን ሽግግር እያሳየ ነው የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ዛሬም እንደገና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ጋዜጦች ኢትዮጵያ ተራበች የሚል እንደ ማንበብ የሚያመኝ ነገር የለም፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹ግብርናችን ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ መቀየር ካልቻልን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ግብርና ደግሞ አሁንም ከእጅ ወደ አፍ የሚሄድ አካሄድን ነው የሚወልደው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አካሄዳችንን ካልቀየርንና ሰፋፊ እርሻዎችን መጠቀም ካልቻልን፣ አርሶ አደራችን ሰፋፊ እርሻ ተጠቅሞ ከራሱ አልፎ ለገበያው ማቅረብ የሚችል ምርት ካላመረተ የትም አያደርሰንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ አባተ በቀለ የተባሉና በግብርናው ምርምር ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያ በበኩላቸው ደግሞ፣ የግብርናው ዘርፍ የተሻለ ሽግግር እንዲያመጣ ካስፈለገ በአርሶ አደሩ በኩል የዝንባሌ ለውጥ መፍጠር መቻል አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ ራሳቸው በቅርቡ ሠርቼዋለሁ ካሉት ጥናት በመነሳት ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ በስድስት ወረዳዎች እንዳካሄዱት በገለጹት የዳሰሳ ጥናት፣ ጥናቱ ከዳሰሳቸው አርሶ አደሮች ውስጥ 18 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ግብርና የቢዝነስ ምንጭ እንደሚሆናቸው ግንዛቤ ሲኖራቸው፣ የተቀሩት 82 በመቶ የሚሆኑት ግብርና ለሕይወታቸው ማቆያ ከመሆን ባሻገር ተጨማሪ ገቢ ማግኛ አድርገው እንደማያስቡት ገልጸዋል፡፡

ሌላው በስፋት የተነሳው ጉዳይ የአገሪቱን የውኃ ሀብት በመስኖ በአግባቡ መጠቀም አለመቻሉ ነው፡፡ ዘርፉን ማሳደግ የሚቻለውን ያህል እንዳልተሠራበት ባለሙያዎች በጋራ የተስማሙበት ጉዳይም ነበር፡፡

በውይይቱ ተገኝተው ከነበሩት የመንግሥት ተወካይ አንዱ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ፣ 2.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬትን በመስኖ ለማልማት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ መታሰቡን ገልጸዋል፡፡

ዕቅዱን በጥሩ ጎኑ እንደተቀበሉት አስተያየት የሰጡት ተመራማሪዎች ግን፣ ‹‹መቼ ነው አገሪቱን በመስኖ ማጥለቅለቅ የምንችለው?›› በማለት ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ‹‹በተለይ አነስተኛ አርሶ አደሮች በመስኖው ተጠቅመው ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ግብርና ማሳደግ እንዲቻል መደረግ አለበት፤›› ሲሉ አንድ ተሳታፊ ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህቺ አገር ማደግ ካለባት ከዝናብ ጥገኝነት ተላቃ ብዙ የመስኖ ግድቦችን ገንብታ መጠቀም አለባት፡፡ እንደ ህዳሴ ግድብ ዓይነት የመሳሰሉ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና ሌሎች የልማት ሥራዎችና የመሠረተ ልማት ተግባሮች ለማካሄድ፣  ለመስኖ ልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶ አርሶ አደሩን የመስኖ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ ካልተቻለ፣ የዚህ አገር ግብርና የትም አያደርሰንም፤›› ሲሉም ሌላ ተሳታፊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተመራማሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያና መልስ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ፣ ግብርናውን ትራንስፎርም ከማድረግ ጋር የተነሱት ጥያቄዎችም ሆኑ አስተያየቶች ገንቢ ከመሆናቸው በላይ፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ዕቅድ ውስጥ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቷቸው መካተታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ሰፋፊ መሬቶችን በማዘጋጀት አርሶ አደሩን ከተበጣጠሰ የእርሻ መሬት ውስጥ አውጥቶ ከራሱ አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ምርትን ማምረት እንዲችል የማድረግ ዕቅድ የተያዘ መሆኑን፣ አተገባበሩ ግን ተጨማሪ ገቢና ከፍተኛ ገንዘብና ሀብት የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በገጠር ያለውን ወጣት በማሠልጠን በሰፋፊ እርሻ በመሰማራት ግብርናው ገበያ ተኮር ምርት ማምረት የሚያስችለው ደረጃ ለማድረስ፣ ፓኬጅ ተቀርጾ ለሙከራ የተጀመረ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት ዘመናዊ አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና  ብድር ለማመቻቸት በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ አቅም ስለሚጠይቅ በሒደት የሚኬድበት ተግባር መሆኑን አቶ ወንድይራድ ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን የግብርና አካሄድ በተመለከተ አቶ ወንድይራድ ሲመልሱ፣ ‹‹ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ሥርዓት ሒደት ነው፡፡ ይህንን በአንዴ  ሳይሆን በሒደት የሚቀየር ነው፡፡ ለዓመታት እየተገነባ የመጣ የአስተሳሰብ ሥርዓት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የመለወጥ ሥራው በጥሩ ጅምር ላይ እንዳለ ነው የምንገምተው፡፡ የግብርናው ኮሜርሻላይዜሽን ስትራቴጂያዊ መሠረት ወደ መሬት እየወረደ መሆኑን በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ለማየት እየተሞከረ ነው፡፡ ትራንስፎርሜሽን በዋናነት ለምንድን ነው የሚሠራው ወይም የሚለማው ብሎ አስቀድሞ በማወቅ፣ የሚያለማውን በመለየት ወደ ልማት የመግባት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ይመጣል፣ የውሳኔ አሰጣጡንም ይመለከታል፡፡ ከዚያም የምርማነቱንና የገበያ ትስስሩን የሚመለከት ሒደት ነው፤›› በማለትም ሚኒስትር ዴኤታው የግብርና ልማቱን ስትራቴጂ በመጥቀስ አክለዋል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን በአምስት ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ መካተቱን አቶ ወንድይራድ ያነሱ ቢሆንም፣ በትግበራ ላይ ግን ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ በተለይም ቴክኖሎጂው ትልቁ ፈተና ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ‹‹አቅማችንን መገንባት ግን የግድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከመስኖ ልማት ጋር የተነሳውን ችግር በተመለከተ አገሪቱ ገና ብዙ እንዳልተጠቀመችበት ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ድረስ የአገሪቱ የገጠር ኢንቨስትመንት በገጠር መንገድ ግንባታና በሌሎች መሠረቶች ልማት ላይ ነው፡፡ ዋነኛው ግን ውኃ ላይ ነው መሆን ያለበት፤›› በማለት ያስረዱት አቶ ወንድይራድ፣ ‹‹ገና ሰፋፊ ኢንቨስትመንት አልተጀመረም፡፡ አጠቃላይ ሴክተሩ እየታየ ሲሆን እንደተባለው ሴክተሩ ውስንነት ይታይበታል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የገጠር መሬት አጠቃቀም ፖሊሲው በዋናነት የአነስተኛ  አርሶ አደሮችን መሬት የማግኘታቸውን መብት መሠረት አድርጎ የሚተገበር በመሆኑ፣ የአርሶ አደሩን አቅም በማጎልበትና ከራሱ አልፎ ለገበያ የሚሆን ምርት እንዲያመርት ማድረግ እስከተቻለ ድረስ፣ ግብርናውን ትራንስፎርም ማድረግ እንደሚቻል ደግሞ የገለጹት የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ስለሺ ጌታሁን ናቸው፡፡

ከተሳታፊዎች የተነሳውን ሰፊ እርሻ የመጠቀም ጉዳይ እንዳለ ሆኖ አሁንም ቢሆን በአነስተኛ የእርሻ ሲስተም ቢሆን፣ በአነስተኛ የእርሻ ሥልትም ቢሆን ግብርናውን ትራንስፎርም ማድረግ እንደሚቻል የተሻለ ልምድ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ልምድ መቀሰሙን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ተመራማሪዎችንም ሆነ የፖሊሲ አውጪዎችን በጋራ ያግባባው ነገር ቢኖር፣ የሰፋፊ የእርሻ ሜካናይዜሽን መጠቀም የሚያስችል አቅም መገንባትና የመስኖ ልማትን እንደ ማንኛውም የአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክት መውሰድ ሲሆን፣ የምርምር አቅምን በማዳበር ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ወሳኝ መሆኑም በአጽንኦት ተነግሯል፡፡

ግብርናው ከእጅ ወደ አፍ ከሚባልበት ደረጃ በማላቀቅ ከሥጋት ነፃ የሚያደርግ አብዮት ማስፈለጉ የግድ መሆኑ ተወስቷል፡፡ ይህ ሲረጋገጥ ብቻ ነው በየዓመቱ በሥጋት ለሚሰቃዩት አርሶ አደር አረፈና ከ80 በመቶ በላይ ለሚሆኑት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ግብርናው ቤዛ ሊሆንላቸው የሚችለው፡፡ አስተሳሰብ ብዙዎችን አግባብቷል፡፡ ይህ ደግሞ የትግራዩን አዛውንት አርሶ አደር አረፈን እንደ አርሲው ሞዴል አርሶ አደር በግብርናው ከሥጋት ይልቅ የእርካታና የተስፋ ሐሴት ለመሙላት ያስችላል ማለት ነው፡፡  

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -