Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአክሰስ ሪል ስቴት መሥራች ላይ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ምርምራ ለአምስተኛ ጊዜ ተፈቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

   – ጽፈዋል የተባለው ደረቅ ቼክ እያከራከረ ነው

 ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ደረቅ ቼክን በሚመለከት ዋስትና ሰጥቷል›› የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ጠበቃ

‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ስለጻፈው ደብዳቤም ሆነ ዋስትና አናውቅም›› መርማሪ ፖሊስ

‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ደብዳቤ ከጻፈና ዋስትና ከሰጠ ምርመራውን ለምን አያስቆምም?›› ፍርድ ቤት

የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋን ከሁለት ሺሕ በላይ ደንበኞች ላይ ገንዘብ ሰብስበው ቤት ገንብተው ባለማስረከባቸው በከባድ የዕምነት ማጉደል ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለፍርድ ቤት እያስረዳ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ ለአምስተኛ ጊዜ ሐሙስ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠየቀባቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደለት፡፡

በቁጥጥር ሥር ውለው ከታሰሩ በዕለቱ 50 ቀናት እንደሞላቸው የተገለጸው አቶ ኤርሚያስ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ ምርመራውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንዳልቻለ ፖሊስ ገልጾ፣ የምርመራ ሥራውን ለሚያቀርብለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ከየካቲት 14 እስከ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ያከናወነውን ምርመራና የሚቀረውን አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተፈቀዱለት ተጨማሪ አሥር የምርመራ ቀናት፣ በባንክ በቂ ስንቅ ሳይኖራቸው አቶ ኤርሚያስ ደረቅ ቼክ የጻፉላቸውን ሰዎች ቃል መቀበሉን ተናግሯል፡፡ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ሰነዶችን መሰብሰቡን፣ ለአቶ ኤርሚያስ ቤትና መሬት የሸጡ ሰዎችን ቃል መቀበሉን፣ ለዘመን ባንክ፣ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ለሌሎችም ተቋማት ደብዳቤ መጻፉን፣ እንዲሁም የተጠርጣሪውን ተጨማሪ ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ከቤት ገዢዎችና ከ600 በላይ ከሚሆኑ የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ባለድርሻዎች የተቀበሉትን ገንዘብ የት እንዳደረሱ የተለያዩ መረጃዎች እየደረሰው በመሆኑ እያጣራ መሆኑን፣ ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በሪል ስቴት ሥራ ላይ መሰማራታቸውንና ድርጅቶች ማቋቋማቸውን የሚመለከቱ ማስረጃዎችም እንደደረሱት ገልጾ፣ በማጣራት ላይ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ በባንክ በቂ ገንዘብ (ስንቅ) እንደሌላቸው እያወቁ ደረቅ ቼኮች በመጻፋቸው ዘመን ባንክ፣ ኅብረት ባንክ፣ ዓባይ ባንክና ሌሎችም ባንኮች ‹‹በቂ ገንዘብ የለውም›› እያሉ በቼኮቹ ላይ ማረጋገጫ በመምታት የመለሱ በመሆናቸው፣ የባንኩን ሠራተኞች ቃል መቀበል እንደሚቀረውም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

አክሰስ ሪል ስቴት ኦዲት እየተደረገ በመሆኑ ገና ውጤቱን ማግኘት እንዳልቻለ፣ በመሆኑም ይኼ የምርመራ ሒደት እየቀረው ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ ምስክሮችን ለማባበልና መረጃ ማጥፋት ስለሚችሉ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጐ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተፈቀዱለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት የሠራውንና የሚቀረውን የምርመራ ሒደት ባቀረበው ሪፖርት ላይ፣ ‹‹መቼም ፍርድ ቤቱ ሳይሰለቸን አልቀረም፤›› በማለት ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት የአቶ ኤርሚያስ የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ ናቸው፡፡

መርማሪ ቡድኑ በዕለቱ ያቀረበው የምርመራ ሥራ ቀደም ብሎ ካቀረባቸው ‹‹ሠራሁና ይቀረኛል ካላቸው›› የምርምራ ሥራዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሞላ፣ ከደረቅ ቼክ ጋር በተገናኘ መርማሪ ቡድኑ ያነሳውን ክርክር አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡

ከቼክ ጋር በተያያዘ ፍትሕ ሚኒስቴር የጻፈው ደብዳቤ ሕገወጥ ነው ካልተባለ በስተቀር፣ ወይም መርማሪ ቡድኑ የደብዳቤውን ሕገወጥነት ወይም ፍትሕ ሚኒስቴር ደብዳቤውን ለመጻፍ ሥልጣን እንደሌለው መርማሪ ቡድኑ ፍርድ ቤቱን ካላሳመነ በስተቀር ምርመራ ማድረግ እንደማይችል አቶ ሞላ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱም የፍትሕ ሚኒስትሩ በአቶ ኤርሚያስ ላይ ቼክን በሚመለከት የተጀመረ ምርመራም ሆነ ክስ ካለ የተቋረጠ መሆኑን በፊርማቸው በተረጋገጠ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እንዲያውቁት በማድረጋቸው መሆኑን አክለዋል፡፡

አቶ ሞላ ይህንን ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ ፍርድ ቤቱ በመሀል አስቁሟቸው፣ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፎ ከሆነ ለምን ምርመራውን አያስቆምም? ስላልገባኝ ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ጠበቃ ሞላም ‹‹እኔም አልገባኝም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ሞላ በሌሎች ቀጠሮዎች ደጋግመው የገለጹትን መድገም እንደሚሆን በማስታወስ፣ አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩበትና አደረጉ የሚባሉት ነገሮች በሙሉ በአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ስም እንጂ በተጠርጣሪው ስም ምንም ነገር አለመደረጉን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ማኅበሩ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ ሠርቶ ከሆነ መጠየቅ እንዳለበት አክለው፣ አክሲዮን መሸጥ ግን የማኅበሩ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በንግድ ሕጉና በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፣ ጠቅላላ ጉባዔው ለቦርዱ በሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ ቦርዱ ሥልጣን (ኃላፊነት) ሰጥቷቸው ሲሠሩ እንደነበር ጠበቃው አስረድተው፣ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ካሉ ሕጉን ተከትለው መክሰስ ከሚችሉ በስተቀር በስሜት የሚናገሩትን ተከትሎ አቶ ኤርሚያስን ማሰርም ሆነ መወንጀል ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

አክሰስ ከተለያዩ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ጋር መገበያየት፣ መሸጥና መለወጥ እንደሚችል የተናገሩት አቶ ሞላ፣ መርማሪው ጠፍቷል የሚለው ገንዘብ የት የት እንደገባና ምን ምን እንደተገዛበት የማኅበሩ ፋይናንስ ኮሚቴ ባለድርሻዎችን ሰብስቦ በቅርቡ ሪፖርት ሲያደርግ አንድም ተቃውሞ እንዳልቀረበበት አስረድተዋል፡፡

ባለድርሻዎቹ በጭብጨባ ያፀደቁትንና ሌላው ማኅበረሰብ በመገናኛ ብዙኃን የሰማውን ሪፖርት፣ ገንዘቡ የት ገባ የሚያስብል እንዳልሆነም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በአሁኑ ጊዜ ደመወዝ፣ ቤት፣ መኪናም ሆነ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ እንደሌላቸው በመግለጽ በዋስ ተለቀው ቢወጡ ምስክር የሚያባብሉበትም ይሁን መረጃ የሚያጠፉበት አቅም እንደሌላቸው በማስረዳት፣ የመርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ጊዜ ውድቅ ተደርጐ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው አቶ ሞላ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ፖሊስ በድጋሚ ባደረገው ክርክር የተጠርጣሪው ጠበቃ ፍትሕ ሚኒስቴር ጽፏል ስለሚሉት ደብዳቤ ተቋሙ የደረሰውም ሆነ የሚያውቀው እንደሌለ በድጋሚ ገልጿል፡፡ ደረቅ ቼክ በቂ ስንቅ እንደሌለው እየታወቀ በመጻፉና የባንክ ባለሙያዎችም በቼኩ ላይ መትተው ተመላሽ በማድረጋቸው ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ቢሆንም፣ የሚያንቀሳቅሱት አቶ ኤርሚያስ በመሆናቸው ሊጠየቁ እንደሚገባ መርማሪ ቡድኑ ተከራክሯል፡፡

አክሰስ ለአራት ዓመታት ኦዲት ተደርጐ እንደማያውቅ የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ አሁን ከዋና ኦዲተር በተመደቡ ባለሙያዎች እየተመረመረ መሆኑን አስረድቶ፣ የተጠርጣሪው ጠበቃ ኦዲት ተደርጐ ለባለአክሲዮኖች ሪፖርት ቀርቧል የሚሉት ዕውቅና የሌለውና ለናሙና ተብሎ የተሠራ የኦዲት ምርመራ መሆኑን ጠቁሞ ሕጋዊነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ገንዘብ፣ ቤት መኪናና በባንክ ገንዘብ እንደሌላቸው በጠበቃቸው የተገለጸውን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ አቶ ኤርሚያስ ከ18 ባንኮች ገንዘብ ሲያወጡ ነበር፡፡ ገንዘባቸው የታገደ ቢሆንም ብዙ ገንዘብ ወጪ በማድረጋቸው ያስቀመጡበት ስለማይታወቅ እንጂ ገንዘብ የላቸውም ለማለት እንደማይቻል በመግለጽ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል፡፡ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ በአየር ላይ ተበትኖ እያለ በኦዲት የተረጋገጠ ገንዘብ እንዳለ መናገር ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ለቀሪ የምርመራ ጊዜ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀዱለት በድጋሚ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የአቶ ኤርሚያስ የዋስትና መብት ጥያቄን ውድቅ በማድረግ፣ ለመርማሪ ቡድኑ አሥር ተጨማሪ ቀናት በመፍቀድ ለመጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች