Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢዎችን መረጠ

የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢዎችን መረጠ

ቀን:

ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔውን የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ያደረገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ዋና ጸሐፊ ምርጫ አደረገ፡፡

በዚህም መሠረት የካፒታል ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ወ/ሮ ትዕግሥት ይልማ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ከበደ ምክትል ሰብሳቢ፣ እንዲሁም የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ገነት ጎሳዬ ጸሐፊ እንዲሆኑ መርጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምክር ቤቱ የአንድ ወር ተኩል የሥራ እንቅስቃሴ በምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ አማካይነት ቀርቧል፡፡ እንዲሁም በዕለቱ ምክር ቤቱን የተቀላቀሉ አሥር አዳዲስ አባላት ዝርዝራቸው ተገልጿል፡፡  የምክር ቤቱን በጀትና የአባላት መዋጮን በተመለከተም ለምክር ቤቱ ሪፖርት ቀርቧል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ባቀረበው ሪፖርት፣ ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የምሥረታ ጉባዔ በመተዳደሪያ ደንቡ የቀረቡ የፓናል አባላት ቁጥርን፣ የምክር ቤቱን የገንዘብ ምንጭን፣ በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ በቃላት አጠቃቀም የትርጉም ችግር ያስከትላሉ የተባሉት አንቀጾች ላይ ማስተካከያ ማድረጉን በሪፖርቱ አካቷል፡፡

ለምክር ቤቱ ሕጋዊ ሰውነት ለማስገኘት ስለተደረገው እንቅስቃሴ በተመለከተ፣ “ከበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ በተገኘው መረጃ መሠረት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የተለያየ አደረጃጀትና ዓላማ ባላቸው ለትርፍና በትርፍ የማይሠሩ ተቋማት ስብስብ በመሆኑ ምክንያት፣ ምክር ቤቱን ለመመዝገብ አስቸጋሪ መሆኑን ተረድተናል፤” በማለት ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ጉዳዩን ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ማስረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በጎ ምላሽ እንደተገኘና ምክር ቤቱ የምዝገባውን ሒደት የሚከታተል ባለሙያ በመመደብ ምዝገባውን ለማካሄድ ሒደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን አክለው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር “አብዛኛው የምዝገባ ሥራዎች በመጠናቀቃቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የምዝገባውን ጉዳይ ጨርሰን ሕጋዊ ዕውቅና እናገኛለን፤” በማለት ሰብሳቢው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱን በጀት በተመለከተ ሦስት ደረጃዎች መዘጋጀታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የሙያ ማኅበራት ከ1,000 ብር እስከ 10,000 ብር ዓመታዊ መዋጮ ያደርጋሉ፡፡ በንግድ ላይ ተሰማርተው ነገር ግን ዓመታዊ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ተቋማት ከ11 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር የሚደርስ ዓመታዊ መዋጮ ያደርጋሉ፡፡ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ ግብር ከፋዮችና የመንግሥት ኮርፖሬሽኖች ደግሞ ከ51 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር ድረስ ዓመታዊ መዋጮ እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ይህ ዓመታዊ መዋጮም በፍላጎት የሚደረግ ከመሆኑም በላይ፣ ሕገ ደንቡ ማንኛውም አባል እኩል መብት እንዳለው በሚደነግገው መሠረት በአባላት መካከል ልዩነትን የማይፈጥር መሆኑን ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ይህ የአባላት መዋጮ የምክር ቤቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ለማከናወን የሚውል ነው፡፡ በመነሻ በጀትነት የምክር ቤቱን ጽሕፈት ቤት ለማቋቋምና ሠራተኞች ቀጥሮ ለማሠራት በመጀመሪያው ዓመት ቢያንስ 500 ሺሕ ብር ለቁሳቁስ ግዥዎች፣ የቤት ኪራይና የሠራተኞች ደመወዝን ጨምሮ እንደሚያስፈልጉ በመታመኑ የተዘጋጀው የበጀት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ፀድቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምክር ቤቱን ፓናልና እንባ ጠባቂ ምርጫን የሚያከናውኑና ጥቆማ የሚቀበሉ አምስት አባላትን በመምረጥ ምክር ቤቱ ጉባዔውን አጠናቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...