ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ፣ ከአረና ፓርቲና ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተከሰው በነበረበት የሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የቀረበባቸው እነ ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው ለፍርድ ቤት አቅርበውት የነበረው ጥያቄ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡
የተከሳሾቹ ጥያቄ ውድቅ የተደረገው፣ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ጥሪ የተደረገላቸው ቢሆንም፣ ሊቀርቡ ባለመቻላቸውና ተጠርጣሪዎቹም ጥሪው መድረስ አለመድረሱን ማረጋገጥ አለመቻላቸውን ከገለጹ በኋላ ነው፡፡
የቀረበውን የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሽ ዘለዓለም ከግንቦት ሰባት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጋር በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት ስለሽብር ድርጊት ሲጻጻፍ እንደነበር ማስረጃ እንደቀረበበት ገልጾ፣ አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ስለሚገኙ ቀርበው እንዲመሰክሩለት በተደጋጋሚ ማመልከቱንና ፍርድ ቤቱም በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
አቶ አንዳርጋቸውን ማቅረብ የማይቻል ከሆነም ከእሳቸው ጋር አድርጓል የተባለውን ግንኙነት በሚመለከት የቀረበበት የክስ ጭብጥ ቀሪ ተደርጐ ብይን እንዲሰጥለት፣ ተከሳሽ ዘለዓለም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የተከሳሹን አቤቱታ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ክርክር አቶ አንዳርጋቸውን አቅርቦ የማስመስከር ግዴታ የራሱ ነው፡፡ ይህንን ሳያደርግ ቀርቶ ‹‹በዓቃቤ ሕግ የተያዘው ጭብጥ ውድቅ ይደረግልን፤›› ማለት እንደማይችል በመግለጽም ተከራክሮ ነበር፡፡ ተከሳሹ ማቅረብ ባለመቻሉም እንደተወው ተቆጥሮ ብይን እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ ተከሳሹ ለመከላከያ ምስክሩ መጥሪያውን ማድረሱን ማረጋገጥ ስላልቻለ እንደተወው እንደሚቆጠር በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉንና ውሳኔ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ተከሳሽ ዘለዓለምን ጨምሮ በአምስቱ ተከሳሾች ላይ ፍርድ ለመስጠት ለመጋቢት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ፣ ሁለቱም ወገኖች የክርክር ማቆሚያ ንግግር ካላቸው ከቀጠሮ ቀን በፊት በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡም አዟል፡፡
በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ክስ ተመሥርቶባቸው መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ የተሰናበቱትና በይግባኝ ሳይፈቱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተከራከሩ የሚገኙት አቶ ዳንኤል ሺበሺ (የአንድነት) እና አቶ የሺዋስ አሰፋ (የሰማያዊ) ፓርቲዎች አመራሮች ችሎት በመድፈር ወንጀል ከተጣለባቸው አንድ ዓመት ከሁለት ወራትና አንድ ዓመት ከአራት ወራት ቅጣት ውስጥ ሁለት ወራት እንደሚቀራቸው፣ አቶ አብርሃ (አረና) ደግሞ አራት ወራት እንደሚቀራቸው ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህንን ያስታወቀው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምን ያህል ጊዜ እንደቀራቸው ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ነው፡፡