Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ችግር ላይ ተቀምጦ መፍትሔ አለመፈለግ ያስጠይቃል!

የአንድ መንግሥት አገርን በብቃት የመምራት ጥንካሬው የሚለካው በተቋማት አደረጃጀትና በአመራር ብቃት በሚያገኘው ውጤት ነው፡፡ ጠንካራ ተቋማትና ብቁ አመራር በሌለበት ሁኔታ ውስጥ አገርን መምራት አዳጋች ከመሆኑም በላይ፣ ዙሪያ ገባውን የሚደመጠው ችግር ብቻ ነው፡፡ ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ማመንጨት ያልቻለ መንግሥት፣ የፈለገውን ያህል ላይ ታች ቢልም አይሳካለትም፡፡ በችግር ላይ ችግር እየተደራረበ የራሱንም የአገርንም ህልውና መቀመቅ ይከታል፡፡ ነገር ግን ብቁ አደረጃጀት ያላቸው ተቋማትና በትምህርት፣ በልምድና በልዩ ተሰጥኦ የዳበሩ አመራሮች ሲኖሩ ችግሮችን ደጋግሞ ከማስተጋባት ይልቅ፣ ለመፍትሔ ቅርብ ይሆናል፡፡  የመንግሥትን አሠራር በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ አለመምራት ግን ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ከተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር አንዳንድ ጉዳዮችን እናውሳ፡፡

በመላ አገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት አሉ፡፡ ከወረዳ ጀምሮ የተዋቀሩት እነዚህ ተቋማት ያላቸው አደረጃጀት ምን ይመስላል? ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ደረጃስ እንዴት ይመዘናል? በሰው ኃይል፣ በበጀት፣ ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ግብዓቶችና በመሳሰሉት የተደራጁ ናቸው? ወይስ በዘልማድ ነው የሚመሩት? መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከት ግን ብዙዎቹ ብቁ የሰው ኃይል፣ በጀትና አስፈላጊ ግብዓቶች ሳይሟሉላቸው በደመነፍስ የሚያዘግሙ ናቸው፡፡ ተቋማቱ ጥንካሬ ስለሌላቸውና እንደሚመሩዋቸው ግለሰቦች ባህሪያት ተለዋዋጭ ስለሚሆኑ፣ ወጥ የሆነ ተቋማዊ ብቃት ማሳየት አይችሉም፡፡ ይልቁንም በጣም ደካሞች ናቸው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ የተፍረከረኩ ተቋማት ውጤት ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህንን ደካማነት ለማስተባበል በሚደረግ አጉል ጥረት ይበልጥ እየኮሰመኑ ናቸው፡፡ ከመፍትሔ አመንጪነት ይልቅ ራሳቸው ችግር ናቸው፡፡

ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ለፖለቲካዊ ወገንተኝነት የተጋለጡ በመሆናቸው፣ የመንግሥት ሥራን በአግባቡ መምራት የማይችሉ አመራሮች መሰብሰቢያ ሆነዋል፡፡ በዕውቀታቸው፣ በሥራ ልምዳቸውና በክህሎታቸው አንቱ የተባሉ አመራሮችና ሠራተኞች ያሉትን ያህል፣ እዚህ ግባ የሚባል ችሎታ የሌላቸው ደግሞ በየቦታው ሞልተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሥራ እየወዘፉ ተገልጋዮችን ያበሳጫሉ፡፡ የአገልጋይነት መንፈስ ስለሌላቸው ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ደንታ የላቸውም፡፡ ብቃት ስለሌላቸው መወሰን አይችሉም፡፡ የግል ጥቅማቸውን ሲያባርሩ ስለሚውሉ ለመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ለሙስና መስፋፋትና ለፍትሕ መስተጓጎል ዋነኛ ምክንያት ናቸው፡፡ በየተቋማቱ ተሰግስገው የሀቀኛ ሠራተኞችን ሞራል ይገድላሉ፡፡ አድልኦና መድልኦ እንዲነግሥ ተግተው ይሠራሉ፡፡ ለተቋማቱ ውድቀትና ለአገር ክስረት መንስዔ ከመሆናቸውም በላይ የሾማቸውን መንግሥት ሳይቀር ያሳፍራሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ከሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የተቋማትንና የአመራሮችን አካሄድ በትኩረት የሚከታተል ማንኛውም ዜጋ የሚጠይቀው፣ መንግሥት ለምን ሕዝቡ በቀጥታ የሚናገረውን አያዳምጥም የሚለውን  ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ካልተደማመጡ ሁሌም ችግር ይኖራል፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለብኝ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡ በትክክል የሚፈልገው ምንድነው ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሚገኘው በአደረጃጀቶች አማካይነት በሚገኝ ግብረ መልስ አይደለም፡፡ የሕዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት የሚታወቀው በቀጥታ ከራሱ አንደበት ነው፡፡ በካድሬዎች ተቀባብቶ የሚቀርብ ሐሰተኛ ሪፖርትና በአደረጃጀት መድረኮች በሆያ ሆዬ የሚቀርቡ ማስመሰያዎች ዋጋ እንደሌላቸው በተግባር እየታየ ነው፡፡ በደካማ ተቋማትና አመራሮች ምክንያት ልቡ የቆሰለ ሕዝብ ግን ሲናገር በትክክል ጥያቄው ይታወቃል፡፡ ምላሹም በዚያ መጠን ይሆናል፡፡ የሕዝብን ችግር ተገንዝቦ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ባለመቻል ምክንያት፣ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ፈተና በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

እዚህ አገር ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ በነፃነት መደራጀት፣ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ፍትሕና ርትዕ ማግኘት፣ የሕግ የበላይነት፣ ወዘተ የመሳሰሉት እንደ ተስፋ ዳቦ ርቀው የተሰቀሉ ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩት እነዚህ መብቶች በተግባር ካልተረጋገጡ በጽሑፍ ሰፍረው በመቀመጣቸው ብቻ ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡ እነዚህ መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ የሚሟገቱ ሲቪክ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል? ብዙዎቹ ደካማ አመራሮች በሕገ መንግሥቱም ሆነ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ የሠፈሩትን መብቶች እያነሱ ይደሰኩራሉ፡፡ የተጻፈው መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መስተጋብር ካልፈጠረ ፋይዳው ምንድነው? ሕጉን በተግባር መፈጸም ይሻላል? ወይስ ስለተጻፈው ሕግ ማነብነብ? መንግሥት ወደ ራሱ ይመልከት፡፡

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ከሕዝቡ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙኃን ጠያቂና መርማሪ የመሆን ጥንካሬ ስለሌላቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደማጭነታቸው ብቻ ሳይሆን ተዓማኒነታቸው እየጠፋ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑ ተቋማት ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ የአመራሮቻቸው ጥንካሬ ጭምር ባለመፈለጉ ብልሹ አሠራሮችን በማድበስበስና በገሐዱ ዓለም የሌለ ምናባዊ ምሥል በመፍጠር እውነት ያዛባሉ፡፡ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ያሉ ዝርክርክነቶችንና የሀብት ብክነቶችን በማጋለጥ እርምት እንዲወሰድ ከማድረግ ይልቅ፣ መሸፋፈንና የሌለውን እንዳለ አድርገው በማሳየት ይቀጥፋሉ፡፡ ችግሮች ከመጠን በላይ ሆነው ሊፈነዱ ሲቃረቡ ግን ከየት መጡ ሳይባሉ ድንገተኛ ውርጅብኝ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው መንግሥት በእነሱ አማካይነት የሕዝቡን ፍላጎት ማግኘት አለመቻሉን ነው፡፡ ይኼ አንድ መለስተኛ ማሳያ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ችግር በአንክሮ የሚከታተል በሚገባ ይረዳዋል፡፡

ሁሌም የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር እንደሌለ ሲነገር ይሰማል፡፡ ነገር ግን ትንንሽ ችግሮች መፍትሔ በማጣታቸው ምክንያት ሲባባሱ ነው የሚታየው፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች በተሠራ ጥናት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት የቅርብ ጊዜ ውይይት የተሰማው፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ምን ያህል ክፍተት እንደተፈጠረ ነው፡፡ በመንግሥት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ያለ መሬት የደላላ መጫወቻ ሆኗል ሲባል ምን ማለት ነው? የሕዝቡን ቅሬታ ሰምቶ የሚፈታ አካል የለም ተብሎ ሲነገር ምንን ያሳያል? አገሪቱ ውስጥ ስንትና ስንት አንቱ የተባሉ በትምህርት፣ በሥራ ልምድና በተሰጥኦ የበለፀጉ ዜጎች እያሉ ሕዝቡ በብቃት አልባዎችና በራስ ወዳዶች እስከ መቼ ይታመሳል? የፖሊሲ ችግር ከሌለ በአግባቡ ፖሊሲ የሚያስፈጽሙ ለምን አይፈለጉም? ብቃት የሌላቸው በአገር ላይ እስከ መቼ ይቀልዳሉ? ይኼ እንቆቅልሽ መፈታት አለበት፡፡

የኤክስፖርት አፈጻጸም ደካማ ነው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፣ ሙስና አገር እየለበለበ ነው፣ መልካም አስተዳደር ጠፍቷል፣ ሰብዓዊ መብት አይከበርም፣ በነፃነት ሐሳብን መግለጽ አይቻልም፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተሸጠ ነው፣ በኔትወርክ የተሳሰሩ ሌቦች አገር እየዘረፉ ነው፣ እሴት ሳይጨምሩ በአንድ ጀንበር ሚሊዮኖች እየተፈጠሩ ነው፣ ጠባብ ብሔርተኝነት እየተስፋፋ ነው፣ አክራሪነት ሥጋት ነው፣ የሕዝቡ እሮሮ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው፣ ወዘተ የሚባሉ ችግሮች በተደጋጋሚ ይሰማሉ፡፡ ሁሌም ችግር ብቻ ነው የሚሰማው፡፡ ከችግሮች ባሻገር ያለውን ተስፋ ማን ያምጣው? ችግር ካለ መፍትሔ እንዴት አይኖርም? መፍትሔ የሌለ ይመስል የምን ዝምታ ነው? በየተገኘው አጋጣሚ ችግር የሚያወራ አንደበት መፍትሔ ለመፈለግ ምን ያቅተዋል? መፍትሔ እያለ ችግርን በማብሰልሰል ምንም የሚገኝ ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው ከደካማ አመራር ችግር እንጂ መፍትሔ አይጠበቅም የሚባለው፡፡ በሕገ መንግሥቱ እንደሰፈረው መንግሥት ለሕዝብ ተጠያቂነት አለበት፡፡  በመሆኑም ችግር ላይ ተቀምጦ መፍትሔ አለመፈለግ ያስጠይቃል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...