Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኢሕአዴግ መመርያ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ጠንከር ያለ ግምገማ እያካሄዱ ነው

በኢሕአዴግ መመርያ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ጠንከር ያለ ግምገማ እያካሄዱ ነው

ቀን:

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በሰጠው መመርያ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች ግምገማ ተቀምጠዋል፡፡ ከወትሮው ጠንከር ብሎ እየተካሄደ በሚገኘው ግምገማ አመራሮቹ ሂስና ግለሂስ እያደረጉ ሲሆን፣ በርካታ አመራሮች ራሳቸውን መከላከል ሳይችሉ እንደቀሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከየካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በቀጠለው ግምገማ ከፍተኛ አመራሮች የጥፋተኝነት መረጃ እየቀረበባቸው ራሳቸውን እንዲከላከሉ ዕድል እየተሰጣቸው እንደሆነ ምንጮች አመልክተዋል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቀሱት ከዚህ ግምገማ በኋላ የሚሰናበቱ በርካታ ባለሥልጣናት ይኖራሉ፡፡ ግምገማውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረ ጻድቃን እስካለፈው ዓርብ ድረስ እየመሩት ነበር፡፡

በግምገማው ሒደት በቅርቡ በመሬት ዘርፍ አመራሮችና በሠራተኞች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከዚህ በተጨማሪም በንግድ ቢሮ፣ በመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ በንግድ ውድድርና በሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት፣ በውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከንቲባ ድሪባ እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ የመሬት መዋቅር ላይ የተወሰደው የማፅዳት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከላይ በተዘረዘሩት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሕዝቡን የሚያማርሩና በሙስና የተዘፈቁ አመራሮች ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

“የሚወደሰው ዕርምጃ በሕግ እስከመጠየቅ የሚደርስ ነው፡፡ ለዚህም አስተዳደሩ ከፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ተባብሮ ይሠራል፤” በማለት ከንቲባ ድሪባ የአስተዳደሩን ቀጣይ አቅጣጫ እንደጠቆሙ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር ችግርና የሙስና መስፋፋትን በተመለከተ ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ችግሩ እጅግ ተባብሶ የቀጠለ በመሆኑ ጉዳዩ የፌዴራል መንግሥትን ጭምር በማሳሰቡ፣ የፌዴራል መንግሥት የሚወሰደው ዕርምጃ በታችኛው መዋቅር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆን እንደሌለበት መመርያ መስጠቱን ምንጮች አመልክተዋል፡፡ በዚህ መነሻ ከየካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቅልና በቡድን እየተካሄደ በሚገኘው ግምገማ፣ በርካታ ባለሥልጣናት ራሳቸውን መከላከል አለመቻላቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡  

ከዚህ ቀደም ራሳቸውን መከላከል ባልቻሉ ባለሥልጣናት ላይ ሲወሰድ የቆየው ዕርምጃ፣ ከቦታ በማንሳት ወደ ሌላ መቀየር ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ ኅብረተሰቡ ቅሬታውን በሰፊው ሲያቀርብ በመቆየቱ ጠበቅ ያለና አስተማሪና ዕርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መሰጠቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የኦሕዴድ 81 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አዳማ ከተማ ከተው ሰንብተዋል፡፡ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መቋጫ ባልተገኘለት የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ መደፍረስ መንስዔና የአመራሩ ሚና ላይ፣ እንዲሁም በክልሉ በሚታየው የመልካም አስተዳደርና የሙስና መንሰራፋት ላይ የተመሠረተ ግምገማ እያካሄደ ነው ተብሏል፡፡

በዝግ የሚካሄደውን ይህ የግምገማ መድረክ የኦሕዴድ ሊቀመንበር አቶ ሙክታር ከድርና ምክትል ሊቀመንበሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ እየመሩት ነው፡፡ በዚህ ግምገማ በርካታ አመራሮች ከቦታቸው እንደሚነሱ ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባና በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው ግምገማ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ ምሽት ድረስ በይፋ ባለመውጣቱ የተወሰደውን ዕርምጃ ማወቅ አልተቻለም፡፡

በሌላ በኩል የብአዴን ማዕከላዊ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ፣ ከቅማንት ማኅበረሰብ ማንነት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ችግርና የግጭት አፈታት ተግባራትን፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በፀገዴ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግርና በሁለቱ ክልሎች የተደረገውን ምክክር፣ በክልሉ በድርቅ የተጠቁ 2.3 ሚሊዮን ዜጎችን በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለሦስት ቀናት መክሯል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ