Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሰባት የኢትዮጵያ ሥጋ ላኪዎች በዱባይ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የንግድ ከተማ በሆነችው ዱባይ ውስጥ፣ ሰባት ኢትዮጵያውያን ሥጋ ላኪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ከአገር እንዳይወጡ ታገዱ፡፡

ሥጋ ላኪዎቹ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንዳይወጡ የተደረጉት፣ ከየካቲት 13 እስከ የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በዱባይ በተደረገው ‹‹ገልፍ ፉድ›› ኤግዚቢሽን ላይ ከተሳተፉ በኋላ ነው፡፡ ለግለሰቦቹ ከአገሪቱ እንዳይወጡ ምክንያት የሆነው፣ ከስድስት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ከተላከ ሥጋ ጋር የተገናኘ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥጋ ምርት ለምትቀበለው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ታሪቅ ኤል ሁዳ የተባለ ድርጅት ከ200 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ የሚሆን የበግ ሥጋ ከሰባት የኢትዮጵያ ቄራዎች ገዝቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሥጋ ወደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከተላከ በኋላ፣ የዱባይ ማዘጋጃ ቤት ሥጋው ተበላሽቷል ብሎ ወዲያው አቃጥሎታል፡፡

የታሪቅ አል ሁዳ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ሙባረክ አብደላህ ከኢትዮጵያ ያዘዙት ሥጋ በዱባይ ማዘጋጃ ቤት በመቃጠሉ ሰባቱ ቄራዎች ገንዘባቸውን እንዲመልሱላቸው ቢጠይቁም፣ ቄራዎቹ በታዘዙት መሠረት ሥጋውን በማቅረባቸው ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል፡፡ ለድርጅቱ ሥጋውን የላኩት ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ሉና ኤክስፖርት ቄራ፣ ሞጆ ዘመናዊ ኤክስፖርት ቄራ፣ ሃላል የምግብ ኢንዱስትሪ፣ ሃሺም የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ሥጋ ላኪ፣ ኦርጋኒክ ኤክስፖርት ቄራና አቢሲኒያ ኤክስፖርት ቄራ ናቸው፡፡

በኤግዚቢሽኑ ለመሳተፍ የሄዱትና ከዱባይ እንዳይወጡ የተደረጉት ሁለት የሉና ኤክስፖርት ቄራ ተወካዮች፣ ሁለት የኦርጋኒክ ኤክስፖርት ቄራ ተወካዮች፣ አንድ የሃላል የምግብ ኢንዱስትሪ ተወካይ፣ አንድ የሞጆ ዘመናዊ ኤክስፖርት ተወካይና የኢትዮጵያ ሥጋ አምራች ላኪዎች ማኅበር ጸሐፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከሰባቱ ኢትዮጵያውያን መካከል ግማሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ የተለቀቁ ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ እስር ቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳይውሉ ተሰውረው እዚያው ዱባይ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤት የቀረቡት ሥጋ ላኪዎች በመጀመሪያ ጉዳያቸው በሻርዣ ከተማ ፍርድ ቤት የታየ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ጉዳዩ መታየት ያለበት በዱባይ ፍርድ ቤት ነው ተብሏል፡፡ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መውጣት ያልቻሉት ሥጋ ላኪዎች በተፈጠረው ችግር እየተጉላሉ መሆኑንም ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቆንስላ ስለጉዳዩ መረጃ የደረሰው መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፣ እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሔ እንዳልተገኘ ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች