- ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የቡና ጉባዔ የሽያጭ ስምምነቶች ይጠበቃሉ
በአፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው የዓለም የቡና ጉባዔ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የዓለም የቡና ግብይት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ደሃ አርሶ አደሮች ፍትሐዊነት እንደሚጎለው በመግለጽ ኮነኑ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቡና ጉባዔውን በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ አዳራሽ ተገኝተው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ዓለም በየዓመቱ 500 ቢሊዮን ሲኒ ቡና በሚጠጣበት ወቅት ለሚጠጣው ቡና ምን ያህል ፍትሐዊ የሆነ ክፍያ ይከፍላል የሚል ጥያቄም ሰንዝረዋል፡፡
‹‹ሁላችሁም ራሳችሁን እንድትጠይቁ የምፈልገው ዓለም በየዓመቱ 500 ቢሊዮን ሲኒ ቡና በሚጠጣበት ወቅት፣ ይህንን ሲኒ ለሚሞላው ገበሬ ምን ያህል ፍትሐዊ ክፍያ እንደሚከለፈው ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ገበሬዎች የቱንም ያህል ጥረው ቡናን ለዓለም ገበያ ቢያቀርቡም ከቡና የሚያገኙት ጥቅም ግን ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከድፍድፍ ነዳጅ በመቀጠል በዓለም ላይ ሁለተኛው የበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ግብይት የሚፈጸምበት ቡና፣ ለገበሬዎች እያስገኘ ያለው ጠቀሜታ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፣ አምራቾች ፍትሐዊ የፋይናንስ ጥቅም የሚያገኙበትን ብልኃት ጉባዔው እንዲመክርበት አሳስበዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ቡና እንዲሁ የሚጠጡት ወይም እግረ መንገድ በጥድፊያ የሚጠጡት አይደለም፡፡ ቡና ማኅበራዊ ሥሪታችን የተዋቀረበት አካልና ክፍል ነው፡፡ ምንም እንኳ ቡና በብዙ መልኩ የባህላችንና የልማዳችን መገለጫ ቢሆንም በኢኮኖሚያዊ ጎኑ እንደሌሎች ቡና አምራች አገሮች ሁሉ፣ በእኛም አገር በርካቶች የዕለት ኑሯቸውን የሚመሩበት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው፤›› ሲሉ በንግግራቸው ያብራሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ቡና በማምረት ሳይታክቱ ለሚደክሙት ገበሬዎች የተረጋጋና ተስማሚ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸው ገቢ ከቡና ማግኘት እንዲችሉ መደረግ አለበት በማለት አሳስበዋል፡፡ ፍትሐዊ የቡና ተጠቃሚነትን ማስፈን የአምራቾችን ኑሮ ማሻሻል ብቻም ሳይሆን፣ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና በአስተማማኝ መጠን ለማቅረብ የሚረዳ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የአገሪቱን 24 በመቶ የወጪ ንግድ ድርሻ የያዘው ቡና ከአየር ንብረት ለውጥና ተዛማጅ ተፅዕኖዎች ለመከላከል፣ መንግሥታቸው ስለሚሠራው ሥራም ለስብሰባው ተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበውም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ንግግር አሰምተዋል፡፡ መንግሥት በዓለም በጣዕሙ ለሚታወቀው የዓረቢካ ቡና ዝርያ መጠበቅ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ያብራሩት አቶ ተፈራ፣ የዚህን የቡና ዝርያ ‹ጀርም ፕላዝም› ለማስጠበቅ የሚከናወኑትን ሥራዎች ጠቃቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የዓረቢካ ቡና ዝርያ አኳያ ዓለም የሚያመርተው አሥር በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተፈራ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቡና ዘረመል ሀብት የጥቅም ድርሻ ላይ የፍትሐዊነትን መርህ እንዲከተል ጠይቀዋል፡፡
የዓለም የቡና ዋጋና የገበያ መዋዠቅንም በሚመለከት አቶ ተፈራ ሲናገሩ፣ እንዲህ ያለው የገበያ አካሄድ የቡና ዘላቂ ልማትንም ሆነ የቡና ዘረመል ሀብት ጥበቃን መጉዳት የለበትም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም ሆኑ የዓለም የቡና ድርጅት ኃላፊዎች የቡና ዋጋ በፍላጎትና አቅርቦት ላይ የሚወሰንና በነፃ ገበያ የሚመራ ነው ቢሉም፣ በቡና ግብይት ላይ የሚታየው እውነታ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ የቆየ ነው፡፡ በዓለም ላይ የቡና አቅርቦት ከፍላጎት አኳያ አነስተኛ ሆኖ ሲቆይ ዘንድሮ የመጀመርያው እንዳልሆነ የዓለም የቡና ድርጅት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኦሊቬሮ ሲልቫም አቅርቦት ከፍላጎት ይልቅ ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ የቡና አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡ ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ በሚሆንበት ወቅት ዋጋ መጨመር ሲገባው በአንፃሩ እየወረደ የሚገኝ በመሆኑ፣ በዚህ ጉዳይ ላይም የዓለም የቡና ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡
በአንፃሩ በአገሪቱ የሚመረተው ቡና ከሌሎች ትልልቅ ቡና አምራች አገሮች አኳያ ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ አገሪቱ በሌሎች አገሮች ከፍተኛ ምርት ሳቢያ የሚወሰነውን ዋጋ ለመቀበል እንደምትገደድ መንግሥትም ሆኑ ላኪዎች ቢገልጹም፣ በዓለም ላይ ትልቅ የግብይት ሚናውን የሚዘውሩት እንደ ስታርባክስና ኔስሌ ያሉት ኩባንያዎች ከቡና አምራቾች ይልቅ ከፍተኛውን ጥቅም የሚያጋብሱ መሆናቸውን በሚመለከት ጥያቄ ሲቀርብ አይታይም፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ከዓለም የቡና ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አራተኛው የዓለም የቡና ጉባዔ ላይ ከውጭ እንደሚገኙ ከተጠበቁት ውስጥ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን፣ በጠቅላላው ከአገር ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ 1,200 ተሳታፊዎች ይጠበቁ እንደነበር፣ ነገር ግን ከ1,400 በላይ መገኘታቸውን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን አግራው፣ በስብሰባው በርካታ የውጭ ገዥዎች በመገኘታቸው የዓመቱን የቡና ሽያጭ ሊያሳካ የሚችል ግብይት ሊፈጸም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም የቡና ድርጅት ቀደምት አባላት ከሆኑት መካከል ስትመደብ፣ ድርጅቱን በአባልነት የተቀላቀለችው እ.ኤ.አ. በ1964 ጀምሮ እንደሆነ የድርጅቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡