በኢትዮጵያ በርከት ያሉ የእግር ኳስ ክለቦች የምሥረታ ዕድሜያቸውን ከመቁጠር ባለፈ በተለይም እግር ኳስ በአሁኑ ወቅት ከደረሰበት ደረጃ አኳያ የራሳቸውን ማዘውተሪያ ከመገንባት ጀምሮ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ መቆየታቸው እሙን ነው፡፡ በውድድር ዓመቱ 80ኛ የምሥረታ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን እያከበረ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ሌሎችም የአገሪቱ ክለቦች የራሳቸውን ዘመናዊ ስታዲየምና ተያያዥ ግንባታዎች ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በ1975 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የስፖርት ማኅበር በሚል የመሠረተውና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስተዳደረው የሚገኘው ይኼው የስፖርት ማኅበር፣ ከእግር ኳስ በተጨማሪ የአትሌቲክስና የጠረጴዛ ቴኒስ ክለብ አቋቁሞ ማኅበራዊ ግዴታውን እየተወጣ ቢገኝም፣ ቀድሞ የስፖርት ማኅበሩን ሲያስተዳድር በነበረው ብሔራዊ ባንክ በ1992 ዓ.ም. ዘመናዊ ስታዲየምን ጨምሮ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ከሊዝ ነፃ መሬት ወስዶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘውና 50,000 ሜትር ካሬ የሚሸፍነው መሬት ላይ የስፖርት ማኅበሩን ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እያስተዳደረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሱን ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት የሚያስችለውን 500 ሚሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን ይፋ አድርጓል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የዘመናዊ ስታዲየሙ አንድ አካል የሆነው ጊዜያዊ ስታዲየም በ4.5 ሚሊዮን ብር አስገንብቶ በይፋ አስመርቋል፡፡ በቅርቡም ዋናውንና ዘመናዊ ስታዲየሙን ለመገንባትም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጭምር የስፖርት ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
በዮሐንስ ዓባይ የግንባታ አማካሪ ድርጅትና በራሱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግንባታ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ተገንብቶ ለምርቃት የበቃው ጊዜያዊ ስታዲየምም፣ የሜዳው ስፋት 105 በ65 እንደሆነም ተነግሯል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አምበሳው እንየው፣ ሌሎች የአገሪቱ ክለቦች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተሞክሮ በመውሰድ የራሳቸውን ማዘውተሪያ ለመገንባት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡