Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ-ከንግድ ባሻገር

​የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ-ከንግድ ባሻገር

ቀን:

ዕለቱ እሑድ በመሆኑ የወትሮው የሜክሲኮ አካባቢ ግርግር የለም፡፡ ዋቢ ሸበሌ አካባቢ በመልሶ ማልማት እየፈረሰ ሲሆን፣ ከፍርስራሹ በቅርብ ርቀት ‹‹እግረ መንገድ፤ የጠፉ መጻሕፍት ዐውደ ርዕይ›› የሚል ማስታወቂያ ይነበባል፡፡ ማስታወቂያውን ተከትለው በፈራረሰው ሰፈር ወደተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ሲያመሩ ካስተዋልናቸው መካከል አንጋፋ ደራስያንና ሐያስያን ይገኙበታል፡፡

በዐውደ ርዕዩ ለንባብ ከበቁ ዓመታትን ያስቆጠሩና በቀላሉ የማይገኙ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም ልብ ወለድ መጻሕፍት ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ስለ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ ሥነ ጽሑፍና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚያትቱ ቀደምት መጻሕፍትም በዐውደ ርዕዩ ተካተዋል፡፡ የአብዛኞቹ መጻሕፍት ሽፋን ከዕድሜ ብዛት ወይቧል፡፡ በተለያዩ መንግሥታት ዘመን የተጻፉና ቀድሞ በአምስት፣ በአሥር ወይም ከዚህ ብዙም በማይበልጥ ዋጋ ይሸጡ የነበሩ መጻሕፍት በዐውደ ርዕዩ እስከ 500 ብርና ከዛም በላይ ተሸጠዋል፡፡ ከቀረቡት መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹን በሽሚያ የሚገዙ ሸማቾች አስተውለናል፡፡

የካቲት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ለዘጠነኛ ጊዜ በተዘጋጀው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ያገኘነው ጎልማሳ በአንድ የውጭ ድርጅት የፖሊሲ አማካሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያና አጎራባች አገሮች ላይ ጥናት ያካሂዳል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ለሥራው የሚያግዙትንና ከዚህ ቀደም ሊያገኛቸው ያልቻለ መጻሕፍትን ገዝቷል፡፡

‹‹አባ ጤና ኢያሱ›› በጎበዜ ጣፈጠ የተጻፈ የታሪክ መጽሐፍ ሲሆን፣ ልጅ ኢያሱ ወደ ሥልጣን ያመሩበትን ሒደትና ሌሎችም ልጅ ኢያሱ ላይ ያተኮሩ ታሪካዊ ሁነቶችን ይዳስሳል፡፡ መጽሐፉን ገበያ ላይ ለማግኘት እንደሚያስቸግርና በ500 ብር እንደገዛው ይናገራል፡፡ የማሞ ውድነህን ‹‹ዮሐንስ›› በ80 ብር፣ የብርሃኑ ዘሪሁንን ‹‹የታንጉት ምሥጢር›› በ70 ብርና የአበራ ጀንበሬን ‹‹የእስር ቤቱ አበሳ›› በ80 ብር ገዝቷል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ በዐውደ ርዕዩ የቀረቡት አብዛኞቹ መጻሕፍት በቀላሉ የማይገኙ ናቸው፡፡ ስለ ዐውደ ርዕዩ በማኅበረሰብ ድረ ገጽ የተለቀቀውን መረጃ ሲያገኝም መሰል መጻሕፍት እንደሚያገኝ ገምቶ ነበር፡፡ ጥንታዊ መጻሕፍት ከያሉበት ለገበያ መዋላቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያምናል፡፡ ለጥናትና ምርምር መነሻ እንዲሁም በታሪክ ጥናት ረገድ መረጃ ያልተገኘባቸው ወቅቶችን ክፍት ለመሙላት እንደሚያግዙ ይናገራል፡፡ ‹‹ጥቅም ላይ ከማይውሉበት ቦታ ወጥተው ለሕዝቡ መቅረብ አለባቸው›› ይላል፡፡ የቀደምት መጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች በቋሚነት ቢዘጋጁ መጻሕፍቱ በተለይ በፖለቲካ፣ ታሪክና ፍልስፍና ጥናት እንደሚጠቅሙ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው እምነቱ ነው፡፡

ቀደም ባሉ ጊዜያት መጻሕፍት ታትመው በስፋት የማይሸጡበት ወይም ጥቂት ኮፒዎች ታትመው ከገበያ ይጠፉ እንደነበር ይናገራል፡፡ በልቦለድም ይሁን ኢልቦለድ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው የቆዩ መጻሕፍት በአንድም በሌላም መንገድ ሲጠፉ፣ መጻሕፍቱ ያሏቸው ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ለገበያ የሚያቀርቡበት መንገድ መፈጠር አለበት የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡

አልፎ አልፎ የመሰል መጻሕፍት ደራስያን ቤተሰቦች ወይም ወዳጆች መጻሕፍቱን በድጋሚ በማሳተም ለገበያ ሲያቀርቡ ይታያል፡፡ ሆኖም ለአሁኑ ትውልድ በስፋት ያልተዳረሱ የቆዩ መጻሕፍት በርካታ ናቸው፡፡ አስተያየት የሰጠን ግለሰብ ‹‹አንዳንዶቹን መጻሕፍት የደራስያኑ ቤተሰቦች ሳይቀር ዘንግተዋቸዋል፤ መጻሕፍቱ ያሏቸው ሰዎች ወይም ተቋሞች ለብዙኃኑ የሚያዳርሱበት መንገድ ካልተመቻቸ የተጻፉበት ዓላማ ግቡን ሳይመታ ቀረ ማለት ነው፤›› ይላል፡፡ የመጻሕፍቱ ገበያ ላይ መዋል የያዟቸውን መረጃዎች ለኅብረተሰቡ ከማስተላለፍ ባለፈ ደራስያኑ እንዲታወሱ እንደሚረዳም ይናገራል፡፡

የዐውደ ርዕዩ አዘጋጅ የሜክሲኮ ዐውደ መጻሕፍት ባለቤት ኤልያስ ገብረማርያም፣ ቆየት ያሉ መጻሕፍትን ከተለያዩ ግለሰቦችና መጻሕፍት አከፋፋዮች ያሰባስባል፡፡ ዐውደ ርዕይ ለማዘጋጀት መጻሕፍቱን ማሰባሰብ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡ መሰል ዐውደ ርዕዮችን በአጭር ጊዜ ልዩነት ማዘጋጀት የሚከብደውም መጻሕፍቱ በቀላሉ ስለማይገኙ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡ ጥንታዊ መጻሕፍት በብራና ላይ የተጻፈና በ20,000 ብር የሚሸጥ ቅዱስ ቁርዓንና በ12,000 ብር ለገበያ የቀረበ 80 አሐዱን ይጠቅሳል፡፡ የአዲስ ነገር ጋዜጣ የሁለት ዓመት እትም ተጠርዞም ለጨረታ ቀርቧል፡፡ የቆዩ መጻሕፍት በጉጉት ሲገዙና ከፍተኛ ገንዘብ ሲያወጡ የሚያዩ የጠፉ መጻሕፍት ደራሲያን ቤተሰቦች ወይም አሳታሚዎች መጻሕፍቱን በድጋሚ እንዲያሳትሟቸው እንደሚያነሳሳ ያምናል፡፡

በተመሳሳይ ቀን ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ፊትለፊት በሚገኘው ትራኮን ሕንፃ ‹‹መጻሕፍት ለሁሉም ቤት›› በሚል የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ተዘጋጀቶ ነበር፡፡ ዐውደ ርዕዩ በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ የተሰናዳ ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ በሚሰጡበት የየወሩ ማገባደጃ ላይ ይካሄዳል፡፡ አዘጋጆቹ በሕንፃው ላይ የሚገኙት ክብሩ የመጻሕፍት መደብር፣ እነሆ የመጻሕፍት መደብርና ሊትማን የመጻሕፍ መደብር ናቸው፡፡

በዐውደ ርዕዩ ከሜክሲኮው በተለየ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሕትመት የበቁ መጻሕፍት ለገበያ ቀርበዋል፡፡ የጠፉት መጻሕፍት ይሸጡበት ከነበረው ዋጋ በላይ ሲሸጡ የቅርብ ጊዜዎቹ ደግሞ ዋጋቸው ተቀንሷል፡፡ ከ25 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ የተደረገላቸው መጻሕፍት ነበሩ፡፡ በዐውደ ርዕዩ ደራስያን ከአንባቢዎች ጋር እንዲገናኙና በመጻሕፎቻቸው ላይ ፊርማ እንዲያኖሩ ተጋብዘዋል፡፡

ከአዘጋጆቹ አንዱ አቶ ክብሩ ክፍሌ እንደሚናገሩት፣ ዐውደ ርዕዩን ያዘጋጁት ብዙዎች በየወሩ አስቤዛ እንደሚሸምቱት ሁሉ መጻሕፍትን የመግዛት ልማድ እንዲያዳብሩ ነው፡፡ በየጊዜው የማኅበረሰቡ የንባብ ባህል መሻሻል እንዳለበት ይነገራል፡፡ ሙያቸው በቀጥታ ከንባብ ጋር የሚያገናኛቸው ሰዎች ሳይቀር ለንበባብ ያላቸው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ አቶ ክብሩ ያምናሉ፡፡ በመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ዋጋ በመቀነስ አንባቢያንን ማበረታት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ይህን ለማድረግም መጻሕፍት ሻጮች ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

እንደ አዘጋጁ ገለጻ፣ ከዐውደ ርዕይ ባለፈ የውይይት መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ ቀድሞ አንባቢያንና ደራስያን የሚገናኙባቸው መድረኮች ብዙ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በመርካቶ መጻሕፍት ተራ ደራስያን፣ መምህራንና ጋዜጠኞች እየተገኙ ይወያዩበት የነበረውን ጊዜ ያስታውሳሉ፡፡ ተመሳሳይ ውይይት በማዘጋጃ ቤትም ይዘወተር ነበር፡፡ አሁን የውይይት መድረኮች ብዙ እንዳልሆኑና ያሉትም ለረዥም ጊዜ መዝለቅ እንደሚያዳግታቸው ይናገራሉ፡፡

ሐሳባቸውን የሚጋራው ሌላው አዘጋጅ ኤርምያስ በላይነህ፤ ዐውደ ርዕዩ መጻሕፍትን በቅናሽ ከመሸጥ በዘለለ በርካታ ሥነ ጽሑፍ ነክ ዝግጅቶች እንዲኖሩት የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ይናገራል፡፡ ‹‹የመጻሕፍት ዋጋ መቀነስ ብቻ ሳይሆን በየወሩ አዳዲስ ሐሳብ እያመጣን የተሳታፊዎችን ቁጥር ማሳደግ እንፈልጋለን፤›› ይላል፡፡

በዐውደ ርዕዩ መጻሕፍት ስትገዛ ያገኘናት የትናየት የሻነው፣ ቫይበር ላይ የተለቀቀ ማስታወቂያ አንብባ ነው ከቦታው የተገኘችው፡፡ በመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች እየተገኘች የመግዛት ልማድ አላት፡፡ ብዙዎች መጻሕፍት ከመግዛት ወደ ኋላ ከሚሉበት ምክንያት አንዱ የዋጋ መወደድ በመሆኑ ቅናሹ ገዢን የሚያበረታታ ነው ትላለች፡፡ መጻሕፍትን መግዛት ብቻውን የንባብ ልምድ እንደማያዳብርና ዐውደ ርዕዮች መገበያያ ብቻ ከሚሆኑ ስለ ንባብ ልምድ ተሞክሮ መለዋወጫ ቢሆኑ መልካም ነው ትላለች፡፡ የመጻሕፍት ሒስ፣ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ውድድሮችና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ሥራዎች መካተት እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው መጻሕፍት እንዲገዛ፣ እንዲያነብና ስላነበበው መረጃ መለዋወጥን እንዲለምድ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮቹ ማንቂያ ደወል ይሆናሉ፤›› ትላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...