Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​መራር እውነት!

እነሆ መንገድ ከኮተቤ ወደ መገናኛ። ቀልዱና ሽሙጡ አይነኬውን ይነካል። ድግግሞሹ የሕይወት አዙሪት ውስጥ ተሳፋሪውን እያፍታታ ትዝብቱንና ብሶቱን ቀላቅሎ ያዛምደዋል። “ወይኔ የት ጣልኳት እባክህ? ኪሴ ውስጥ ስከታት ትዝ ይለኛል፤” ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ፌዘኛ ወጣት ይንቆራጣል። “ምንድናት እሷ? ላፋልግህ?” ከጎኑ የተሰየመች የጠይም ቆንጆ ትጠይቃዋለች። “አቤት ሰው። ይኼኔ የኑሮዬ ዳና ጠፍቶኝ ቢሆን እንኳን ልታፋልጉኝ ጨመር ጨመርመር አድርጋችሁ ጥፋቱን ታፋፉት ነበር፡፡ አይ ሰው!” ይላል ወጣቱ። “ቆይ ምን ጠፍቶት ነው?” ሲለኝ መሀል መቀመጫ ላይ ከጎኔ የተሰየመ ጎልማሳ ሲጠይቅ፣ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ተስፋፍቶ ተቀምጦ ስልኩን የሚጎረጉር ወጣት፣ “ስልኩን ጥሎ ነው፤” ብሎ ከባለቤቱ አውቆ ቁጭ። “ኡኡኡ! ስልኩንማ ከጣለ ምኑን ሕይወት አለኝ ሊል ነው? በበቃኝ ለምን አይወጣም?” መጨረሻ ወንበር በመፋቂያ ንጣቱን ለማስለቀቅ ይመስል ጥርሱን አሳር እያሳየ የሚልግ ወጣት ጣልቃ ገባ።

 “ከየት ነው የሚወጣው?” አለቸው አጠገቡ የተየመች ወይዘሮ እግሯ ሥር ያስቀመጠቸውን ዘንቢል እያንሸራሸረች። አልተመቻትም። “ከሪንጉ ነዋ፤” ይላል ያ ጣልቃ ገብ። “ታክሲ ላይ መስሎኝ የተሳፈረው። የምን ሪንግ ነው?”  የወጣቶቹ ሽሙጥ ስላልተገለጸላት ተደናግራለች። “ምንድነው ዘንድሮ ሰው ነገርና ገንዘብ እየዘረዘረ ጥፋት በጥፋት መሆን የሚያምረው?” ሲል አጠገቤ የተቀመጠው፣ “ይኼ ግልጽነት የሚባል የግሎባላይዜሽን ዘይቤ ነዋ። አይገርምም ሁሉም ነገር አደባባይ ሲውል ሁሉም ነገር እርቃኑን ስናየው፣ እንዴት ኑሯችን ጣዕም አልባ እየሆነ እንደመጣ እየታዘባችሁ ነው?” ብሎ የተነሳንበትን ትቶ እንዳመጣለት ሲናገር፣ “ሪንግ የሚልሽ ኑሮን ነው፤” ብሎ ሌላው ተረጎመላት። “እኮ ስልክ ጣልኩ ተብሎ ኑሮን በበቃኝ?” ወይዘሮዋ ብያኔው የምር እንደሆነ ሁሉ ስትደነግጥ፣ “ታዲያ! ያለ ኔትወርክ ዘንድሮ ምንስ ሥራ ምንስ ደመወዝ አለ?” ባለመፋቂያው ተናግሮ ልቡ ጠፋ። እስከ መቼ አንድ ዓይነት የአደባባይ ሚስጥሮች ላይ እያላገጥን እኛም ዕድሜያችን እንደሚያልቅ  እንጃ!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀምራለች። “ወንዳታ! አገኘኋት…” ብሎ ያ ኪሱ እስኪቀደድ ራሱን በራሱ የሚበረብር ወጣት ሃምሳ ሳንቲም አወጣ። “ለሃምሳ ሳንቲም ነው ይኼ ሁሉ ሽብር? ሙሰኛ ያጋለጥክ ነው የምትመስለው፤” ብሎ ጎልማሳው ተበሳጨ። “ወንድሜ ሃምሳስ ብትሆን ዛሬ ማን ያበድራል? መቼም ለሃምሳ ሳንቲም ብድር ባንክ አናስቸግር?” አለው ዕጦቱና ግኝቱ የተጣጣለበት ተሳፋሪ። “እንዲያው ሌላው ቢቀር ምናለበት በደፋናው ገንዘብ ጠፍቶብኝ ነው ምናምን ብትል? ሃምሳ ሳንቲም ጠፋ ብለህ ይኼን ያህል ዘመን በመረዳዳትና በመደጋገፍ አብሮ የኖረ ወገንህን ታሳጣለህ?” ቢለው መልሶ፣ “እሱን ጊዜን ጠይቀው፤” እያለ ከመፋቂያው የሚረግፉትን ስንጥሮች የሚተፋብን ያ ወጣት ጣልቃ ገባ። “እንዴት?፤ ጎልማሳው ለወሬ ጉጉ እንደሆነ መላ ህዋሱ ያሳብቃል።

 “እንዴት ማለት ጥሩ ይባል ነበር በደህናው ጊዜ። እንዴት ባይ እያለ። አየህ ይኼም ጊዜን ይመለከታል። ወደ ዋናው ጉዳይ ስገባ . . . እእ . . . ናና ጋቢና የተቀመጡትን ልጆች ሒሳብ እንዳትቀበላቸው ረዳት። ተከፍሏል። . . . አዎ ወደ ዋናው ነጥብ ስገባ እኛ ሳንለያይ ጊዜ ያለያየን ዘመን ላይ ደርሰናል የሚለው ነው። ሐበሻ ዛሬ የተረፈው የታሪክ እንጂ የኑሮ እሴት ትሩፋት አይደለም። ይህን ለማወቅ ገንዘብ ሳትይዝ ታክሲ ተሳፈረህ ማየት ነው። ብንከፍልልህ እንኳ ዓይናችን ላይ የምታየው የበላይነት ስሜት፣ አፍ ያላወጣ እሰያችን ዕድሜህን ባያሳጥረው ከምላሴ ፀጉር፤” ብሎ አረፈው። ተቃዋሚ ስንጠብቅ “እሱስ እውነት ነው፤” ብሎ ሁሉም ዝም አለ። “ያለ ‘ዳታ’ ያለ ጥናት ይህን ያህል ስለራሳችን እናውቃለን ካልን ታዲያ ለምን ይሆን የለውጥ ማዕበል ከአለት አለት እያላጋ የያዝነውን ሲያስጥለን ዝምታ የመረጥነው?” የሚለኝ ከጎኔ የተቀመጠው ነው። እኛ ምኑን አውቀን ወዳጄ!

በስፖንሰር የሚጓዙት ጋቢና የተሰየሙት ታዳጊዎች ለብቻቸው ሊንሾካሾኩበት የሚገባቸውን ጨዋታ ገሃድ ያወጡታል። “ስማ ያቺ ልጅ ምን አለችህ?” ይላል አንደኛው። “ምን ትላለች? እኔ እንደ አንጆሊና ጆሊ እንደ ካትሪን ዚታ ዓይነት የውበት እመቤት እንጂ እንደ አንቺ ዓይነት ውበት አላደንቅም አልኳት። ከዚ ምን ብትለኝ ጥሩ ነው ‘አንተ አፍቅረኝ እንጂ ሆሊውድም ባልነግሥ በነገሥኩበት ባደግኩበት መንደሬ ሁነኛ ባለሙያ ፈልጌ ሰርጀሪ እሠራለሁ’ ብላ አሾፈችብኝ። ቀልዴን መስሏት እኮ ነው፤” ይላል። “እኔንማ አትዋሸኝ እንደዚያ ሙዝዝ ያልከው ወደሃት አልነበር እንዴ?” ሲለው ልጁ መልሶ፣ “ምን ላድርግ? የልጅቷ ትምህርት ዓላማ የሴቶች አርዓያ መሆን ነው፡፡ ‘ዋት ኤቨር’ ብቻ ህልመኛ ነገር ናት። እኔ ደግሞ ምርቃና ላይ ካልሆነ እንዲህ ዓይነት ህልም አይመቸኝም፤” ይለዋል። ይኼን እየሰማ አዋቂው ራሱን ይነቀንቃል።

“አይ ጊዜ ገና ሳያድጉ ፍቅር ፍቅር ሲሉ፣ እነሱም አያፍሩ እኛም አንናገር ብለን ዝም አልን። ወላጅ ልጁን የፈራበት ዘመን፤” ትላለች ወይዘሮዋ። “የማንን ልጅ ማን ይቀጣል?” ጎልማሳው ይተባበራታል። “እነሱ ምን ያድርጉ? እኛስ ምን እናድርግ? መንግሥት ነው ተጠያቂው፤” ይላል ሌላው። “ኤጭ እስካሁን ደህና ስንጫወት ቆይተን ደግሞ ጀመረው። የፈረደበት መንግሥት፤” ትላለች ጠይሟ። “ተይ እንጂ! የውጭውን ትተሽ የአገር ውስጡን ብታይ እኮ ለታዳጊው የሞራልና የእሴት ግንባታ ምን ያህሉ የሚዲያ ፕሮግራም ይዘቱ ታስቦበት ነው የሚተላለፈው? እዚህ መንግሥት ባለበት አገር ቆይ ግን እኛ፣ ስለሚዲያ ፕሮግራሞች ይዘት እንጨነቅ ስለዘይት?” ሲላት ጎልማሳው፣ “ዘይት ሲጠፋ ችግር። ይዘት ሲሳሳ ችግር። መንግሥት ጣልቃ አይገባ። ሲገባ በዚያው የነፃ ኢኮኖሚ ቀበኛ። በዚህ የነፃ ፕሬስና ሚዲያ አፈና። ወይ ዕዳ!” ብሎ ባለመፋቂያው ተናገረ። ፍቅር ይዘት አጣ ተብሎ ዕድሜን ተንጠላጥሎ መንግሥትን ሲያጥላላ፣ ምርጫ ያለው ጆሮውን በኢርፎን ጠርቅሞ ዓይኑን ጨፈነ። ዘንድሮስ ካገባው ያላገባው የተሻለ ዕድሜ ሳይኖር አይቀርም!

ወያላው ጋቢና የተሰየሙትን ታዳጊዎች ሸኝቶ አንዲት ፈረንጅና ሐበሻ ወዳጇን አሳፈረ። ባለመፋቂያው ወርዶ በምትኩ አንድ የዕድሜ ባለፀጋ ተተኩ። ጉዟችን ቀጠለ። ሾፌሩ ዝምታውን ለመስበር ሬዲዮኑን ከፍ አደረገው። “በአንድ ጥናት መሠረት ከውሻቻው ጋር ረጂም ጊዜ የሚያጠፉ እንስቶች በአሜሪካ ለትዳር ተመራጭ ሆነዋል ተባለ፤” ይላል ጋዜጠኛው። አዛውንቱ፣ “ምንድነው ያለው?” ብለው አጠገባቸው የተቀመጡትን ጠየቁ። የጥናቱ ውጤት ተደገመላቸው። “የዘመኑ ጥናት ደግሞ አበዛው፤” ብለው ፈገግ አሉ። “እንዴት?” ሲሏቸው፣ “ገና ለገና ጥናት ሲባል ሰው አደብ ገዝቶ ያዳምጠናል እያሉ ይኼው የማይመስል ነገር አረጋገጥን ሲሉ አትሰሙም። እኛ እንኳን ከውሻ ከሰው ጋር መዋል ትተን መስሎኝ? መቼም አያውቁም እያለ የማይጫወትብን የለም፤” ብለው ዝም አሉ።

“አባት ጥናቱ አሜሪካን እንጂ እኛን እኮ አይመለከትም፤” ሲላቸው አንዱ፣ “ድሮስ! እንኳን ከነቡቺ ከአምሳዮቻችን ጋር ውለንስ የእኛ ልብ ይታወቃል እንዴ? እኛን ማጥናት የሚችል እሱ የፈጠረን ብቻ ነው፤” ሲሉ ተራውን ተሳፋሪው ፈገግ አለ። “እውነታቸውን ነው! ለዚያም ነው በአለንጋና በዱላ ስንገዛ የኖርነው። ለነገሩ አሁን ዴሞክራሲ ላይ ነን፤” የሚለኝ ያ አጠገቤ የተቀመጠ ተሳፋሪ ነው። “አቤት! አቤት! ሰው ሰውን ጠልቶ፣ በራስ ፍቅር አብዶ፣ ከእንስሳት ጋር በሚውለው አዋዋል ፈጣሪ ሌሎችን እንዲያፈቅር የሰጠውን ልዩ የማፍቀር ለመፈቀር ፀጋ ጥሎ እንዲህ የጉድ መናኸሪ ይሁን፤” አዛውንቱ ለብቻቸው ሲያጉተመትሙ “አልቋላ ዘመኑ! ከእንግዲህ የቀረን ዓይኑን አፍጦ በፍትሕ ስም በሰላም ስም ኑሮን በማርከስ ስም አምባገነን የዓለም መሪ ሲመጣ ማየት ብቻ ነው፤” ብላ ወይዘሮዋ መለሰችላቸው። ይኼኔ ጎልማሳው፣ “ትራምፕ ይሆን እንዴ?” እያለ ጭንቀቱን አባባሰው። ዴሞክራሲ ሆይ በስምሽ የሚመጣ የተባረከ ነው እንዳልተባለ ዛሬ በዴሞክራሲ ስም አምባገነንና ትምህክተኛ ለመንገሥ ሲሯሯጥ እናይ ጀመረ። ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል አሉ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። “እግዚኦ ለመጀመርያ ጊዜ በሕይወቴ ቅበላን በሽሮ አሳለፍኩ፤” ብላ ወይዘሮዋ የመዝጊያውን ምዕራፍ ስትጀምር፣ “በሞትኩት ምነው?” አሉዋት አዛውንቱ። “ምነው አለው እንዴ ሰውን እያዩት። እኔ ምለው ይኼኛው ሁዳዴ የመጫረሻ ነው ተብሏል እንዴ?” ብላ አዳንቃ ጠየቀች። “ይኼኔ ጋቢና የተቀመጠችው ፈረንጅ ወይዘሮዋ ለምን እንደጮኸች ሐበሻውን ጠየቀችው። አብራራላት። ዓይኗን አፍጣ ደረቷን ነፍታ ወደ ኋላዋ ዞረችና፣ “በእውነቱ ኢትዮጵያውያን ደስ ትላላችሁ። የተለየ ባህል፣ እምነትና አቋም ነው ያላችሁ። ለምሳሌ እኔ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሥጋ የመብላት ቀን ዓይቼ አላውቅም ነበር። ቅበላ በጣም ደስ የሚል ባህላችሁ ነው ቀጥሉበት፤” ብላ እየተኮላተፈች ንግግር አደረገች።

አዛውንቱ አበዱ። “ኧረ እባክሽ ሴትዮ ቅበላ ፆም መያዣ ነው። ማነህ በደንብ ንገራት እንጂ። ሥጋ የመብላት ቀን? የሁዳዴ ፆም መያዣ ነው ሃይማኖታዊ ነው አትላትም እንዴ አንተ?” እያሉ ወጣቱ ላይ ጮሁ። “ምን ታድርግ እሷ አባት። ሥጋ ‘ሜርኩሪ’ ሆኖ የዋለበት ፆም መያዣ ላይ ደረሰች። የምታየውን አየች። ሰበብ ፈጥረን ሰበብ አግኝተን ስንበላ ስንጠጣ ስንሳከር አየች። ስንኖረው አላየች። ታዲያ ይኼ እኮ አይደለም ለእሷ ለእኛም ዓላማው ግራ ገብቶናል። ከሃይማኖታዊ ሥርዓትነቱ ይልቅ የቁርጥና የጥብስ ካርኒቫል ሆኖብናል፤” ሲላቸው ጎልማሳው መለስ አሉ። ይኼኔ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ አራገፈን። አዛውንቱ  በሳቅ እንዳልተቀላቀሉን ፊታቸውን አጨፍግገው “ቂም በቀል ነው እንዴ ቅበላ?” እያሉ ፊት ፊት ሄዱ። መለስ ብለው ግን፣ “ወገኖቼ ለባዕዳን አጉል የታሪክ ማስታወሻ አንሁን፡፡ ጥሩ መሆን ለራስ ነው …” ሲሉ እኛም በየፊናችን ተበታተንን። “ለካ አልፎ ሒያጅ የፈረንጅ ጸሐፊን ስንከተል ነው የራሳችንን መገለጫዎች ያጣነው?” የሚል ፍምፅ እየተሰማን መንገዱን ነካነው፡፡ መራር እውነት ማለት ይኼ አይደል? መልካም ጉዞ!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት