- ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ፕሮጀክት ቀርጿል
ፀሐይ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የገዛውን የቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ቀሪ ክፍያ ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ይተካሉ የተባሉ አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ሁለት የማስፋፊያ ሥራዎችን እንደሚያካሂድ ገለጸ፡፡
ፀሐይ ኢንዱስትሪ ከሦስት ዓመት በፊት ከ555 ሚሊዮን ብር በላይ የቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካውን ሲገዛ የመጀመርያውን ክፍያ በመክፈል ቀሪውን በአምስት ዓመት ለመክፈል ተዋውሎ ነበር፡፡ በዚሁ ውለታ መሠረት ቀሪውን ክፍያና በተጨማሪ ከግዥው ጋር እንዲካተት የተረደረጉ ምርቶችን ጨምሮ፣ በጠቅላላው ከ671.2 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ በመፈጸም ፋብሪካውን በስሙ አዙሯል፡፡
ይህንንም ክፍያ ከውለታው በፊት የከፈለው ከባንክ በመበደር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ክፍያውን በማጠናቀቁም ፋብሪካው ወደ ተሻለ የማምረት ሥራ እንዲሸጋገር እያስቻለው መሆኑን የፀሐይ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማቲዎስ አሰሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መነሻነት ከውጭ የሚገቡ የጥሬ ዕቃዎችንና የተለያዩ የኮንስትራክሽን ግብዓት ምርቶችን በፋብሪካው ለማምረት ዝግጅት እያደረገና ወደ ምርት እየገባ መሆኑ ታውቋል፡፡
በቅርቡም ማምረት ከጀመራቸው ምርቶች መካከል የከባድ ተሽከርካሪዎች ተሳቢና አካላት አንዱ ነው፡፡ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ወደ ሥራ የገባው የከባድ ተሽከርካሪና አካላትን ምርት ፕሮጀክት ወደ ማምረት ተሸጋግሯል፡፡ እንዲህ ዓይነት ምርቶችን በማምረት የሚታወቁ ሁለት ፋብሪካዎች ያሉ ቢሆኑም፣ በገበያ ውስጥ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር ወደዚህ ምርት መገባቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ከአቶ ማቲዎስ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ አክሰሉን ከጀርመኑ ቢፒኤም ከተባለ ኩባንያ በማስመጣት ቀሪውን የብረት ሥራ እዚሁ በማምረት ለገበያ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ አሁን ፋብሪካው ባለው አቅም በ2008 በጀት 150 ተሳቢዎችንና የከባድ ተሽከርካሪ አካላትን ለማምረት ታቅዷል፡፡ የፈሳሽ ማመላለሻና የደረቅ ጭነትና ተሳቢዎችን አካላት ለማምረት የሚያስችሉ አዲስ የማምረቻ ግንባታ ሥራም መጀመሩም ታውቋል፡፡
ፋብሪካው ሁለት ዓይነት የማስፋፊያ ሥራዎችን የሚያከናውን መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አንዱ ከውጭ አገር ለፋብሪካው ምርት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በፋብሪካው ማምረት ነው፡፡ ይህም በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ውስጥ ወሳኝ የሆነውን የኮልድሮሊንግና የጋልቫናይዜሽን ሥራውን እዚሁ ለማምረት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጋልቫናይዝድ የተደረገ ምርትን ሲያስገባ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ዋናውን ጥሬ ዕቃ በማስገባት እዚሁ ጋልቫናይዝ በማድረግና ኮልድሮድ ምርቱን በማዘጋጀት ለተለያዩ ምርቶች ማምረት የሚያስችለውን ፕሮጀክት ሥራ ላይ ያውላል፡፡
የኮልድሮሊንግና ጋልቫናይዜሽን ሥራውን ለማሠራት የሚያስችለው ማምረቻ ፕሮጀክት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሥራ ላይ ከሆነ ጋልቫናይዝድ ተደርጎ ለሚመጣው ምርት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል ተብሏል፡፡
ይህ ከውጭ ሲመጣ ዋጋው ወደድ ያለና ብዙ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ ነው ያሉት አቶ ማቲዎስ፣ ምርቱ ወደ አገር ተጓጉዞ ሲመጣ የሚያጋጥመውን ብልሽት በማስቀረት ጭምር ይረዳል ብለዋል፡፡ በዚህ እሴት በተጨመረበት ምርት የተለያዩ ምርቶች ይመረታሉ፡፡ ጋልቫይናይዝድ በተደረገው ምርት ደግሞ ለጣራ ክዳንና ለግድግዳ ሽፋን የሚሆኑ ምርቶችን በቀላሉ ለማምረት ይቻላል ተብሏል፡፡ ሁለተኛው የፋብሪካው ማስፋፊያ ሥራ ደግሞ የተሳቢና የጭነት አካላት ማምረቻ ነው፡፡ የዚህ ማምረቻ ግንባታው ተጀምሯል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፍሪ ፋብሪኬትድ ስቲልስ ለማምረት እየተዘጋጀ ነው፡፡
በሲቪል ሥራ በኮንክሪት የሚመረቱ ቋሚዎችን በብረት ስትራክቸር ለመሥራት ያስችላል የተባለው ይህ ምርት፣ እስካሁን ከውጭ ሲገባ የነበረ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ይህንንም አገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ለማስቀረት የሚያስችለውን ፕሮጀክት ወደ ሥራ ለማስገባት የማምረቻው ግንባታ ተጀምሯል፡፡
እነዚህ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹ የሚመረቱት ምርቶች ወደ ገበያ ሲወጡ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጡና የውጭ ምንዛሪን በማዳንና የግንባታ ጊዜን በመቆጠብም ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን መቶ በመቶ የሚባል ምርቶችን እያመረተ ያለው ቃሊቲ ብረታ ብረት፣ ከውጭ የሚገባ ነበር የተባለውን 120 በ120 መጠን ያለው አዲስ ቱቦ እዚሁ ለማምረት ዝግጅቱን አጠናቆ በቅርቡ ማምረት ይጀምራል፡፡ ይህ ቱቦ ለድልድልይ ሥራም እንደሚያገለግል አቶ ማቲዎስ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ከውጭ ይገባሉ የተባሉ ተመሳሳይ ምርቶችን ለማምረት ውጥን እንዳለውም ተገልጿል፡፡ ቀደም ብሎ ቢሆን በአትራፊነቱ የሚታወቀው ይህ ፋብሪካ፣ ወደ ግል ከተዘዋወረ በኋላ ደግሞ የበለጠ አትራፊ እየሆነ መምጣቱ ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ከፋብሪካው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2006 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 32.2 ሚሊዮን ብር፣ በ2007 በጀት ዓመት ደግሞ 38.4 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ በ2006 በጀት ዓመት 415.9 ሚሊዮን ብር የነበረው ዓመታዊ ሽያጩ፣ በ2007 በጀት ዓመት ወደ 484.5 ሚሊዮን ብር ሊያድግ ችሏል፡፡
በ2008 ዓ.ም. ስምንት ወራትም የሽያጭ መጠኑ 351.9 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የሽያጭ መጠን ጋር የአሥር በመቶ ዕድገት ታይቶበታል፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት የምርት መጠኑም ቢሆን በ45 በመቶ እንደጨመረ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም. በስምንት ወራት 11,204 ቶን የነበረው ምርቱ፣ በ2008 በስምንት ወራት 16,249 ቶን መድረሱ የፋብሪካው የምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ የገጠመው ችግር ባይኖር፣ ፋብሪካው ከዚህም በላይ ያመርት እንደነበር ከአቶ ማቲዎስ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡