ኢትዮጵያ በቡና መስክ ከውጭ ምንዛሪ ጠቀም ያለ ገቢ ስታገኝ ቆይታለች፡፡ የአገሪቱ 25 ከመቶ የውጭ ምንዛሪ ከዚሁ ከቡና ንግድ ይመነጫል፡፡ የአገር ውስጥ የቡና ገበያው ምን እንደሚመስል ተወት እናድርግና ከውጭ ገበያ አኳያ ያሉትን እውነታዎች እንመልከት፡፡
በአገሪቱ ሃያ ሚሊዮን የሚገመት አባወራ የዕለት ኑሮውን በቡና ላይ መሥርቶ፣ ከቡና በሚያገኛት እርጥባን ይተዳደራል፡፡ ልጆቹን ያሳድጋል፡፡ አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልከው ቡናም 800 ሚሊዮን ዶላር አንዳንዴም ከዚህም ከሚጠበቀውም ገንዘብ ያነሰ ገቢ እያስገኘ የሚገኘው ቡና፣ በዚህ ዓመት 900 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ማስገኘት ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡
የአገሪቱ የቡና ጣዕም፣ የተፈጥሮ መዓዛም ሆነ ሌሎችም የቡና ተፈጥሯዊ መመዘኛዎች የቱንም ያህል የኢትዮጵያን ቡና የተለየ ቢያሰኙት፣ አገሪቱ ‹‹ኮፊ›› ለሚለው የቡና ስያሜ ከፋ ከሚለው የቡና የትውልድ ሥፍራ ድረስ ለዓለም ያበረከተች መሆኗን ብታስተጋባ፣ ዓለም ቢዘምርላትም የቡና መገኛነቷን የሚመጥን ምርት አታመርትም፡፡ በዓመት 6.4 ሚሊዮን ኬሻ ወይም 290 ቶን በማምረት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በየትኛውም መስፈርት የዓለም የቡና ገበያን የምትወስንበት ዕድል የላትም፡፡
በአንፃሩ እንደ ብራዚል ያሉ የዓለም ቀንደኛ ቡና አምራቾች በዓመት ከ40 ሚሊዮን በላይ ኬሻ ወይም ሁለት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ቡና በማምረት የዓለምን የቡና አቅርቦት ተቆጣጠረዋል፡፡ ከብራዚል በታች እነ ኮሎምቢያ፣ ቬትናም፣ ኤኳዶርና ኢንዶኔዥያ ትልልቆቹ የዓለም ቡና አምራች አገሮች ስለመሆናቸው የዓለም የቡና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ከአፍሪካ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የአውራነቱን ቦታ ብትቆናጠጥም፣ በእስያና ኦሽንያ፣ በሜክሲኮና መካከለኛው አሜሪካ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ትልልቅ ቡና አምራች አገሮችን ለመቀናቀን ማቀዷን ይፋ አድርጋለች፡፡
የቡና ጉባዔና የቡና ዘመን
መጪው አምስት ዓመት ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛዋ ቡና አምራች አገር የምትሆንበት ጊዜ እንደሆነ ባለሥልጣናት ይፋ ያደረጉት፣ በዓለም ለአራተኛ ጊዜ የሚካሔደውን የዓለም የቡና ጉባዔ መካሄድ በተጀመረበት ወቅት ነው፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽ መካሔድ የጀመረው ጉባዔ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ፣ ኢትዮጵያ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ባለው ሁለት የቡና ዘመን ጊዜ ውስጥ ብራዚልን ተከትላ ሁለተኛዋ የዓለም ቡና አምራች ትሆናለች ብለዋል፡፡
ከሚጠበቀው በላይ ተሳታፊ ከአገር ውስጥም ከውጭም ታድሞበት 1400 ሰው ያስተናገደው የዓለም የቡና ጉባዔ፣ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ እንደመሆኑና እንደ ትልቅነቱ ለአዘጋጁ አገር ትልቅ ዕውቅና ማስገኘቱ ዕሙን ነው፡፡ ነገር ግን በተጨባጩ ለኢትዮጵያ ምን ያስገኝላታል ወይስ ይፈይድላታል? ለሚለው ጥያቄ ከሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ባሻገር የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን አግራው ከገጽታ ባሻገር አዲስ አበባ ያስተናገደችው ጉባዔ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ይዘረዝራሉ፡፡
ከሁሉ ይልቅ ከ500 ያላነሱ የውጭ ተሳታፊዎች በታደሙበት የቡና ጉባዔ ወቅት በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ገዥዎች በመገኘታቸው፣ የቡና ግዥ ስምምነቶች በብዛት ሊፈረሙ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በዚህ ዓመት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን 900 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከቡና ማግኘት የሚቻልበት ዕድል እንደሚፈጠር ተስፋ አላቸው፡፡ ከዚህ ሲልቅም ከአገሪቱ ዋና ዋና የልዩ ጣዕም ቡናዎች መገኛ ከሆኑት ውስጥ በሲዳማና በይርጋጨፌ በሚደረግ የማሳ ጉብኝትም የአገሪቱን የቡና ዝርያዎችና የቡና ሀብት ለማስተዋወቅ እግረ መንገዱንም አገሪቱ ላላት ጥራት ያለው ቡና የሚከፈላት ዋጋ በጎብኝዎች እንዲታይላት (‹‹ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል›› ብሒልን ልብ ይሏል) ያሰበችበት እንደሆነ አቶ ወንድይራድ አብራርተዋል፡፡
ይህ እግንዲህ የስብሰባው ፋይዳ ተብለው ከተጠቃቀሱት ውስጥ ሚዛን የደፋው ሲሆን፣ እንደሚባለው ምን ያህል ሽያጭ ተካሄደ ለሚለው ቀጣዮቹ ቀናት የሚመልሱት ይመስላል፡፡ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ የግዥ ስምምነቶችና ውሎች ይፋ ይደረጉ ይሆናል የሚል ግምት አጭሯል፡፡ በዚያም ላይ ጊዜው ቡና የሚደስርበት በመሆኑ፣ ከፍተኛ ቡና ወደ ውጭ እንዲወጣ መደረግ እንዳለበት አቶ ሁሴን አሳስበዋል፡፡
ጉዞ ብራዚል
በዓለም ላይ በመጀመሪያው ረድፍ የምትቀመጠው ብራዚል፣ ከፍተኛውን የቡና ምርት በዓለም ገበያ በማቅረብ በዋጋም፣ በገበያ ይዞታም ገበያዎችን ተቆጣጥራለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2014/15 ባለው ጊዜ ውስጥ የብራዚልን የቡና አቅርቦት የሚገዳደረው አልተገኘም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 50.8 ሚሊዮን ኬሻ የነበረው የብራዚል ምርት እርግጥ እየቀነሰ መጥቶ እ.ኤ.አ. በ2014/15 የታየው የምርት መጠን 43.2 ሚሊዮን ኬሻ ላይ አርፏል፡፡
የዓለም የቡና ድርጅትም በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት ሮቤሪዮ ኦሊቬራ ሲልቫ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ ባደረጉት ትንበያ መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ2015/16 ይመረታል የተባለው የቡና መጠን 143.4 ሚሊዮን ኬሻ ቡና ነው፡፡ ካለፈው የቡና ግብይት ዓመት ከነበረው 141 ሚሊዮን ኬሻ ምርት አኳያ መጠነኛ ጭማሪ ያሳየ እንደሆነ ሲልቫ አብራርተዋል፡፡ የብራዚል የአየር ንብረት ማዛባት የምርት መቀነስ ማስከተሉት የጠቀሱት ሲልቫ፣ እንደ ቬትናም፣ ኮሎምቢያና ኢንዶኔዥያ ያሉ ተቀናቃኝ አገሮች የአቅርቦት ጉድለቱን እንደሚሞሉት ተስፋ ተደርጓል ብለዋል፡፡
አፍሪካ በተጻራሪው 25 አገሮች በቡና አምራችነት ተመዝግበው የሚገኙባት አኅጉር ብትሆንም፣ የዓለምን 12 ከመቶ ወይም 17 ሚሊዮን ኬሻ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ እንደምትቀጥል የገለጹት ሲልቫ፣ የኢትዮጵያ ድርሻ ምን እንደሚመስልም የምርትና አቅርቦት ግምቱን አስቀምጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚጠበቀው የቡና ምርት መጠን 6.4 ሚሊዮን ኬሻ ቡና ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ምርት አኳያ በ3.4 ከመቶ ዝቅ ያለ መሆኑን ለምርቱ መቀነስ የዝናብ መዛባት በቡና ተክል ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2016/17 ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው የምርት መጠንን በሚመለከትም ሲልቫ ሲያብራሩ፣ በብራዚል ከ49 እስከ 52 ሚሊዮን ኬሻ ቡና ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ ኮናብ እየተባለ በአጽንኦት የሚጠራው የብራዚል የቡና ባለሥልጣን፣ በዚህ ዓመትና በሚቀጥለው ዓመት በሚኖረው የብራዚል ቡና ምርት ላይ መሻሻል እንደሚኖር መተንበዩንም ሲልቫ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የዓለም የቡና ፍጆታን በሚመለከት እ.ኤ.አ. በ2015 በነበረው የዓለም የቡና ድርጅት ትንበያ መሠረት፣ ቡና በሚገዙ አገሮች ዘንድ ይኖራል ተብሎ የነበረው የፍጆታ መጠን 104.9 ሚሊዮን ኬሻ እንደነበር የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሲልቫ አስታውሰዋል፡፡ ቡና አምርተው የሚልኩ አገሮች ከ47 ሚሊዮን ኬሻ በላይ ቡና ለፍጆታቸው የሚያውሉ በመሆኑ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ልዩነት መከሰቱን፣ ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ ሆኖ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ይፋ በተደረገው የዓለም የቡና ድርጅት ትንበያ መሠረት ኢትዮጵያ ታመርታለች ተብሎ የሚጠበቀው የቡና መጠን ሰባት ሚሊዮን ኬሻ ነው፡፡ ይህም ካምናው የአንድ ሚሊዮን ኬሻ ጭማሪ የሚኖረው ነው፡፡ በመሆኑም አሥር የዓለም ቡና አምራች ከሆኑ አገሮች ውስጥ ከአፍሪካ በኡጋንዳ ተበልጣ ስምንተኛው ላይ እንደምትገኝ የድርጅቱ ሪፖርት ያመላክታል፡፡
ይህ ቢሆንም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ቁንጮ የሆነችውን ብራዚልን በመከተል፣ እነ ቬትናምን፣ ኮሎምቢያን፣ ኢንዶኔዥያን፣ ፔሩን፣ ህንድን፣ ኡጋንዳን፣ ሆንዱራስንና ሜክሲኮን አስከትላ በመጪዎቹ አምስት ወይም ሰባት ዓመታት ውስጥ ከዋና አምራችነት ቁንጮዎች ተርታ ትመደባለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ፣ ለዚህ ትልም ማብራሪያ ቢሰጡም ዝርዝሩን አላስቀመጡም፡፡ እርግጥ አገሪቱ ከዚህ በኋላ ቡናን ከዝናብ ይልቅ በመስኖ ለማልማት መዘጋጀቷን ተናግረዋል፡፡
ይህ ዕቅድ ምን ያህል ለእውነተኛነት የቀረበ ነው? ምን ያህል ይሳካል? ተብለው ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ወንድይራድ፣ ምላሻቸው አገሪቱ በዓለም ዕውቅ ባለሙያዎችን አሰማርታ አስጠንታለች፣ ቡና በገፍ ለማምረት የሚስማማና ያልተነካ በሚሊዮን ሔክታር የሚቆጠር መሬት አለን ብዋለዋል፡፡ ይህ በደፈናው የተነገረው ነገር በተግባር ሲተረጎም ዝርዝሩ ምን ይመስላል? በአምስት ዓመት ውስጥ ይህ ሲታሰብ በያመቱ ምን ያህል ያስገኛል? ወዘተ. የሚሉ ዝርዝር ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡
በዚህ ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም እንኳ ሲታይ ይህ ዕቅድ ምን ያህል ያስኬዳል የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ያስቀምጠዋል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና 104 ሺሕ ቶን ወይም 2.3 ሚሊዮን ኬሻ የሚጠጋ ነው፡፡ ምንም እንኳ በመጠን ረገድ ለዓመቱ ከታቀደው 206 ሺሕ ቶን አኳያ የመሳካት ዕድል እንዳለው ቢያመለክትም፣ በገቢ ደረጃ ሲታይ ግን አሁን የተገኘው 350 ሚሊዮን ዶላር ለዓመቱ ከታቀደው 900 ሚሊዮን ዶላር ገደማ አኳያ ጉድለት የሚታይበት ነው፡፡ አገሪቱ ከምታመርተው ቡና ውስጥ ከ50 ከመቶ በላይ በአነስተኛ አርሶ አደሮች ተመርቶ ለአገር ውስጥም ለውጭ ገበያም እንደሚቀርብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በጠቅላላው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ24 በላይ ዝርያ ያላቸውን የቡና ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡ አገሪቱ ለቡና የሰጠ፣ የተመቸ የአየር ንብረትና መልክዓ ምድር ቢኖራትም፣ በቡና አምራችነት የሚታወቁት ጥቂት አካባቢዎች ናቸው፡፡ በዚያም ላይ በየጊዜው በሚዋዥቀው የቡና ዋጋ ሰበብና ገበሬው በሚያገኘው ዝቅተኛ ገቢ ሳቢያ ከቡና እርሻ ይልቅ በሌሎች ሰብሎች ላይ መሰማራትን ሲመርጥ የታየበት ጊዜም ሩቅ አይደለም፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ሁሉ ክፍተቶች ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ መንግሥትም ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ያለውንና ቀድሞውን ዘርፉን በመምራት ረገድ ረጅም ታሪክና ተሞክሮ የነበረውን የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን መልሶ ለማደራጀት ተገዷል፡፡
የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሳኒ ረዲን በዋና ዳይሬክተርነት በመሾም፣ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን የተባለውን መሥሪያ ቤት በአንድ መልክ በግብርና ሚኒስቴር ሥር አዋቅሯል፡፡