Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

​ግልጽነት የጎደለው አገር የአጥፊዎች መፈንጫ ይሆናል!

ያለንበት ዘመን መረጃ በብርሃን ፍጥነት ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍበት ነው፡፡ ከዚህ ፈጣን ግስጋሴ ጋር እኩል ለመራመድ አለመቻል ፈተናው ብዙ ነው፡፡ አንድ ማኅበረሰብ ከዚህ ዘመናዊ ዓለም ጋር ፍጥነቱን ካላስተካከለ፣ የሚከፍለው ዋጋ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ግልጽነት መርህ የሆነበት ይህ ዘመን ፈጣን የሆነ የመረጃ ፍሰትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ይጠይቃል፡፡ ግልጽነት ለማንኛውም ተግባር ከሚያስፈልግባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ጥራትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ደረጃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ውጤት ማግኘት የሚቻለው ከዘመኑ እሳቤ ጋር እኩል መራመድ ሲቻል ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ግልጽነት ከሌለ ግን፣ ለዘመናት ከነበረው የኋላቀርነት አዙሪት ውስጥ መውጣት አይቻልም፡፡

ግልጽነት ለመንግሥት፣ ለገዥው ፓርቲ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ለሕዝቡ፣ ለንግድ ድርጅቶች፣ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ለፍትሕ አካላት፣ ለሚዲያ፣ ለትምህርትና ለምርምር ተቋማት፣ ወዘተ በጣም አስፈላጊ መርህ ነው፡፡ በአገራችን ውስጥ እንደ ልማድ አስረው ከሚጎትቱ ችግሮች መካከል ዋነኛው የግልጽነት አለመኖር ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዚህ መጥፎ ልማድ እስረኞች በመሆናቸው፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለው የመረጃ ፍሰት በጣም ያሳፍራል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ መልካም ከሚባሉ ጉዳዮች ውጪ የሚያጋጥሙ ሌሎች ክስተቶች ሲደባበቁና ሲድበሰበሱ ይታያሉ፡፡ በመረጃ ዕጦት ወይም መዛባት ምክንያት ከእውነታዎች ይልቅ ሐሜቶችና አሉባልታዎች የበላይነት ይይዛሉ፡፡ ግልጽነት የጎደለው ኅብረተሰብ አንዱ መገለጫ ይኼ ነው፡፡

የመንግሥት አሠራር በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ መመራት እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በወረቀት ላይ የሠፈረው በተግባር ሊታይ ባለመቻሉ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በፍትሕ መነፈግና በሙስና አሳሩን ሲበላ ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ ሕዝብ የበደሉ ሹማምንት ሥልጣናቸውን ያላግባብ እየተገለገሉበት ምሬት ሲፈጥሩ፣ የአገር ሀብት ሲመዘብሩ፣ መሬት ወረው ሲሸጡና ትርምስ ሲፈጥሩ በደካማ ግምገማ ሒሳቸውን ውጠው ሌላ ቦታ ሲሾሙ ይታያል፡፡ ሕዝቡ እንዴት እንደተገመገሙ ሳያውቅ በሌላ ሹመት ለሌላ ጥፋት ይታጫሉ፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽ ባለመሆኑ ምክንያት ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ሻካራ ይሆናል፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የሚወሰዱ አንዳንድ ደካማ ዕርምጃዎች አርኪ ባለመሆናቸው ቅሬታውና ቅራኔው ይቀጥላል፡፡ ግልጽነት በሌለበት ከዚህ የተሻለ ምንም ዓይነት ጤናማ ሁኔታ አይኖርም፡፡

ሕዝቡ የመንግሥትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና የአገሩን የዕለት ሁኔታ በተመለከተ ፈጣንና አስተማማኝ መረጃ ስለማያገኝ፣ በገዛ አገሩ ጉዳይ ባይተዋር እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች፣ ቅሬታዎች፣ ግጭቶችና የመሳሰሉት ሲከሰቱ እነዚህን ጉዳዮች ወደ ጎን በመግፋት ሌሎች ተራ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ያለንበት ዘመን መረጃ በፍጥነትና በጥራት የሚተላለፍበት በመሆኑ ዜጋው የአገሩን ጉዳይ ከውጭ ሚዲያዎች ለመስማት ይገደዳል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው የሕዝብ ተቃውሞ መሆኑ በአንድ ጎን እየተነገረ፣ በሌላ በኩል የጥፋት ኃይሎች ሴራ ነው ተብሎ ሲወራ መደነጋገር ይፈጠራል፡፡ ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ ምን እንደሆነ በግልጽ ሳይታወቅ፣ ጠቃሚ ያልሆኑ አሰልቺ ወሬዎች ይበዛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ግልጽነት በመጥፋቱ ሕዝብ ግራ ይጋባል፡፡ ከግራ መጋባት በላይም ከመንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ይበላሻል፡፡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ይሸረሸራል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ ድርጊቶችን የሚመለከቱ መረጃዎች በተደበቁ ቁጥር የሕዝብ ትችትና ተቃውሞ ይበረታል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ይፈጠራል፡፡

ዘመኑ መረጃ በነፃነትና በፍጥነት የሚተላለፍበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ መረጃ በገፍ በነፃ የሚገኝበት ነው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መረጃ ሲነፈግ ወይም ሲዘባበት፣ ብስጭቱ ከመጠን በላይ ይጨምራል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ዓለም አቀፉ የፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ አበረታች ንጥረ ነገር የተጠቀሙ ተጠርጣሪ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዝርዝራቸውን ልኳል፡፡ በሹክሹክታ እነማን መሆናቸው እየታወቀ፣ ለሕዝቡ በፍጥነት ለምን አይገለጽም? በአገሪቱ ውስጥ ድንገተኛና ያልተጠበቁ ክስተቶች ሲፈጠሩ መንግሥት በፍጥነት መረጃውን ለመስጠት ሲቸገር፣ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ነው ዝርዝሩ የሚሰማው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት መነሳቱ ሳይሆን፣ ከከራረመ በኋላ ግጭቱ እንዴት እንደተፈታ ይወራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ግልጽነት የጎደለው አሠራር ከዘመኑ ጋር አይሄድም፡፡ ከዘመኑ ፈጣን ግስጋሴ ጋር መራመድ ያቃታቸው ወገኖች በሚፈጥሩት ችግር አገር ትጎዳለች፡፡ ሕዝቡ መረጃ ያጣል፡፡  ወይም የተዛባ መረጃ ይይዛል፡፡

በየትኛውም ሥፍራ ተቀባይነት ካላቸው አሠራሮች አንዱ የተመረቱ ምርቶች ለተጠቃሚዎች በግልጽ መቅረብ መቻላቸው ነው፡፡ ማንኛውም ምርት የተመረተበት ጊዜ፣ አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜና የተመረተባቸው ንጥረ ነገሮች በግልጽ ይሰፍራሉ፡፡ መድኃኒት፣ ምግብ፣ ውኃ፣ የመዋቢያ ቁሳቁሶች፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ምርቶች እነዚህ መግለጫዎች በግልጽ ካልሰፈሩባቸው ለተጠቃሚዎች አይቀርቡም፡፡ ለገበያ እንዲቀርቡም አይደረጉም፡፡ ይህ ዓይነቱ የግልጽነት ጥንቃቄ የሚደረገው በሕዝብ ጤና ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነው፡፡ ማንኛውም ኅብረተሰብ አኗኗሩ ግልጽነት ከጎደለው ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣል፡፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ካልተነጋገሩ የልጆቹ አስተዳደግ ይበላሻል፡፡ የንግድ ተቋማት ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በግልጽነት ላይ ካልተመሠረተ አገልግሎታቸው ይስተጓጎላል፣ ለኪሳራ ይዳረጋሉ፡፡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሥራቸውን በግልጽነት ካላከናወኑ ማኅበረሰቡን ይጎዳሉ፡፡ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ግልጽነት ከሌላቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ ሚዲያው የሕዝብ አመኔታ ካጣ ተቀባይነቱ ይጠፋል፡፡ ሕዝብና መንግሥትም ግንኙነታቸው በግልጽነት ላይ ካልተመሠረተ በአገር ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ ግልጽነት የዘመናዊነትና የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን በጣም እየጎዳት ያለው የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡ የዘር፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ባለበት አገር ውስጥ ግልጽነት ከሌለ እንዴት ልዩነትን ለማቻቻል ይሞከራል? በማንኛውም ጊዜና አጋጣሚ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው ግልጽነት ሲኖርና መረጃ በነፃነት መፍሰስ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ግልጽነት ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለዴሞክራሲ መዳበር፣ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ለሐሳብና ለንግግር ነፃነት፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገልና በአገር ግንባታ ተሳትፎ ለማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ግልጽነት በሌለበት ሌብነትና ሕገወጥነት ይበረታሉ፡፡ አምባገነንነት ይንሰራፋል፡፡ ማናለብኝነት ይገናል፡፡ ሐሰተኞችና አጭበርባሪዎች ይፈነጫሉ፡፡ አገሪቱ በትክክለኛ ጎዳና ላይ እንድትራመድ ከተፈለገ ግን ሕዝቡ፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው በሙሉ ግልጽነት እንዲሰፍን ይረባረቡ፡፡ ግልጽነት የጎደለው አገር የአጥፊዎች መፈንጫ ይሆናል!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...