Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​የኦሮሚያ ባለሥልጣን በነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ ላይ ከቀረቡት አምስት ክሶች ሦስቱ ውድቅ...

​የኦሮሚያ ባለሥልጣን በነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ ላይ ከቀረቡት አምስት ክሶች ሦስቱ ውድቅ ተደረጉ

ቀን:

ጉቦ በመስጠት ከባድ የሙስና ወንጀል፣ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት የመያዝ የሙስና ወንጀል፣ በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ መያዝና በከባድ አታላይነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ወንድሙ ቢራቱ፣ ሦስቱ ክሶች ውድቅ ተደርገውላቸው በሁለቱ ክሶች ብቻ እንዲከራከሩ ብይን ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ብይን እንዳስታወቀው በአቶ ወንድሙ፣ በወይዘሮ እልፍነሽ ቢራቱና በወይዘሮ አሰገደች መንግሥቱ (የአቶ ወንድሙ ባለቤት) ላይ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ንብረት መያዝ የሙስና ወንጀል፣ በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ መያዝና ከባድ አታላይነት ፈጽመዋል በማለት ያቀረባቸውን ክሶች ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሦስቱን ክሶች ውድቅ ያደረጋቸው፣ አቶ ወንድሙ በጠበቃቸው አቶ መሐመድኑር አብዱልከሪም ያቀረቡትን የመጀመሪያ መቃወሚያ ሐሳብና ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን መልስ ከመረመረ በኋላ ነው፡፡ ጠበቃው በመጀመሪያ መቃወሚያቸው ባቀረቡት የመከራከሪያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ አቶ ወንድሙ ሙስና ፈጽመዋል ቢባል እንኳን ጉዳዩን (ወንጀሉን) የመመርመር ሥልጣን የክልሉ መንግሥት ነው፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 እና 52፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 7 (2) እና አንቀጽ 55፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 እና ማሻሻያዎቹ አዋጅ ቁጥር 138/95፣ 254/98፣ 321/95 እና 454/97፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 እና የኦሮሚያ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 71/95 መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር እንዳለበትና በፌዴራሉ የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(8) መደንገጉን በመጠቆም፣ ኮሚሽኑ በክልሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር የሚወድቅን የሙስና ወንጀል ጉዳይ ክስ የማየትና የማቅረብ የሕግ ፈቃድ ወይም ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ ጠበቃ መሐመድኑር አቶ ወንድሙን በመወከል በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 130/2ሠ/መሠረት መቃወማቸውን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

አቶ ወንድሙ ኮሚሽኑ ባቀረበባቸው አምስት ክሶች እያንዳንዱን ክስ ዝርዝር ነጥቦችን በማንሳት የተቃወሙ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግም በተለይ አቶ ወንድሙ ላይ በአንደኝነት ያቀረበውን ክስ በማንሳት ተከራክሯል፡፡ አቶ ወንድሙ ጉቦ በመስጠት ከባድ የሙስና ወንጀልና በሥልጣን የመነገድ ወንጀል ፈጽመዋል የተባለበት ድርጅት፣ በአዲስ አበባ ክልል ውስጥ የሚገኝ ፈቃድ የተሰጠው የፌዴራል ተቋም መሆኑንና ግብርና ታክስም የሚከፈለው ለፌዴራል ተቋም በመሆኑ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን እንዳለው አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመመሥረት ሥልጣን እንዳለው ወይም እንደሌለው፣ እንዲሁም ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? ተደራራቢ ክሶች መቅረባቸው አግባብ ነው አይደለም? የሚሉ አምስት ጭብጦችን ይዞ መርምሯል፡፡

አቶ ወንድሙ በአንደኛ ደረጃ የቀረበባቸው ክስ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ባህሩ ቢረዳ የተባሉ ግለሰብ (አብረው ተከሰዋል) ‹‹ጠጠር እየፈጩ በጅምላ መሸጥ›› የሥራ መስክ ተሰማርተው ይሠራሉ፡፡ ድርጅቱ ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ የነበረበትን ከ5.7 ሚሊዮን ብር በላይ የንግድ ትርፍ ግብርና ተጨማሪ እሴት ታክስ በወቅቱ ባለመክፈሉ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ተጣርቶ ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ነክ ጉዳዮች ክትትል ቡድን አስተባባሪ ለነበሩት አቶ መርክነህ ዓለማየሁ (አሁን በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰው ማረሚያ ቤት ናቸው) ይተላለፋል፡፡ አቶ መርክነህ ክሱን እንዳይመሠርቱ አቶ ወንድሙ በማግባባት፣ በማስፈራራትና ጉቦ በመስጠት በአቶ ባህሩ ቢረዳ ላይ ሊቀርብ የነበረውን ክስ ማዘጋታቸውን ክሱ እንደሚያስረዳ ፍርድ ቤቱ በዝርዝር ገልጿል፡፡ ድርጅቱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኝና በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚገኝ ተቋም በመሆኑ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ሥልጣን እንዳላቸው ፍርድ ቤቱ በብይኑ ገልጿል፡፡ የክልል መንግሥት ስለማይመለከተው ጉዳዩን የማየትና የመዳኘትም ሥልጣን እንደሌለው አስረድቷል፡፡

ሌላው ፍርድ ቤቱ የአቶ ወንድሙን መከራከሪያ ነጥብ ውደቅ ያደረገው፣ አቶ ወንድሙ በወቅቱ የነበራቸውን ሥልጣን ተጠቅመው እነ አቶ ባህሩ ቢረዳን ‹‹ጠያቂ ሳይኖርባቸው ተረጋግታችሁ እንድትሠሩ አደርጋለሁ፤›› በማለት የማስፈጸሚያ እንዲሰጧቸው ከጠየቋቸው አምስት ሚሊዮን ብር ውስጥ 3,310,000 ብር ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የቀረበባቸውን ክስ ፍርድ ቤቱ የማየት ሥልጣን እንዳለው በማስረዳት ብይን ሰጥቷል፡፡ ሌሎቹን ክሶች (ከላይ የተገለጹትን) የአቶ ወንድሙ ጠበቃ አቶ መሐመድኑር ጠቅሰው ባቀረቡት መቃወሚያ መሠረት ድርጊቱ ተፈጸመ የተባለው በክልሉ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት የማየት ሥልጣን እንደሌለው ገልጾ ብይን በመስጠት አቶ ወንድሙ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ አድርገዋል፡፡ አቶ ወንድሙም ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምኩም›› በማለት የተከሳሽነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ ወንድሙ ቢራቱን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ በሚያካሂድበት ወቅት ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ ለባለሥልጣናት የአውሮፕላን ትኬት እየገዙ በጉቦ መልክ ይሰጡ እንደነበር፣ በሰው መግደል ወንጀል መጠርጠራቸውንና ሌሎች በርካታ የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎችን በመጥቀስና ለተረኛ ችሎት በማቅረብ ተደጋጋሚ የ14 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ሲጠይቅባቸውና ፍርድ ቤቱም ሲፈቅድ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በአቶ ወንድሙ ላይ ከቀረቡት አምስት ክሶች ውስጥ ፍርድ ቤቱ የማየት ሥልጣን ባለው በሁለቱ ክሶች ላይ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ሚያዝያ 17 እና 18  ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲያሰማ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...