Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​ኦሕዴድ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አገደ

​ኦሕዴድ የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አገደ

ቀን:

  • አቶ አባዱላ ገመዳ ድርጅቱ ራሱን ይፈትሽ ሲሉ አሳስበዋል
  • የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በጉባዔው ውጤት አልተደሰቱም

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለማጥራት ሰሞኑን ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባዔ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩትን የክልሉን የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘለዓለም ጀማነህን እስከ ቀጣዩ የድርጅቱ ጉባዔ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴው አገደ፡፡

ሪፖርተር በየካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትሙ ከኦሕዴድ አመራርነትና ከክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊነት በብቃት ማነስ ሳቢያ፣ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌና የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኩቹ መነሳታቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ለአምስት ቀናት ያካሄደውን አስቸኳይ ጉባዔ የካቲት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ባጠናቀቀበት ወቅት ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ዘለዓለም ጀማነህ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እስከ ቀጣዩ የድርጅቱ ጉባዔ ማገዱን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው ውሳኔውን ያሳለፈው ‹‹ከሁሉም በፊት መስመራችን ያስመዘገባቸውን አንፀባራቂ ድሎች ያቆሸሹ የግለኝነትና ጥገኝነት፣ እንዲሁም የጎራ መደበላለቅን በጥልቀት በመመርመር ከሥራ አስፈጻሚና ከማዕከላዊ ኮሚቴ ጀምሮ በከፍተኛ አመራሮች ላይ ያለምንም ርህራሔ ዕርምጃ ተወስዷል፤›› በማለት ነው፡፡

አቶ ዘለዓለም ጀማነህ በኦሕዴድ ውስጥ በተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ ለረጅም ዓመታትም የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል፡፡

በፓርቲው የአምስት ቀናት ውይይት ወቅት ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፣ በፌዴራል ፓርላማ ውስጥ የኦሕዴድ መሠረታዊ ድርጅት አባላት ለማዕከላዊ ኮሚቴው ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡

ከእነዚህም መካከል የሰው ሕይወትና ንብረት ከመጥፋቱ በፊት ኦሕዴድ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ለምን ተቸገረ? የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የቆመው በ2006 ዓ.ም. ነው በማለት መረጃ ሲሰጥ ከቆየ በኋላ፣ በድጋሚ በ2008 ዓ.ም. የተቀናጀ ማስተር ፕላኑ ውድቅ ተደርጓል ብሎ ለምን የተጋጨ መግለጫ ሰጠ? በ2006 ዓ.ም. ቆሞ ከነበረስ በወቅቱ ለሕዝብ ለምን ይፋ አልተደረገም ነበር? የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ያላት ልዩ ጥቅም የማግኘት መብት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፋ ይሆናል መባሉ ተገቢ ነው ወይ? መቼ ተጠንቶ እንዴት በአጭር ጊዜ ይፋ ሊሆን ይችላል? ማግኘት የሚገባበት ጥቅም ወደኋላ ተመልሶ የ21 ዓመታት ጥቅምን ያስገኛል የሚሉ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም በውይይቱ ተነስተዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ የተሳተፉት የማዕከላዊ ኮሚቴው አባልና የፓርላማው አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ‹‹ዋናው ችግር ያለው የፓርቲው አመራር ላይ ነው፡፡ ራሳችንን እንፈትሽ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የተፈጠረው ችግር የራሳችን የሙስና ችግር ነው፡፡ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት ካልቻልን አንዱ በአንዱ ላይ እየተደራረበ አገር ይፈርሳል፤›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹ትልቁ ውድቀት የሕዝብ ጥያቄን መመለስ ሳንችል ስንቀር ነው፡፡ ስለዚህም ራሳችንን እንፈትሽ፤›› ያሉት አፈ ጉባዔው፣ ‹‹ይኼን ጊዜ እዚሁ ቁጭ ብለው መረጃ የሚልኩ ይኖራሉ፡፡ የድርጅታችን ችግር እኛ ውስጥ ነው ያለው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ የአቶ አባዱላ አባባል ጉባዔውን ያሳቀ ሲሆን፣ እንዳሉትም የጉባዔው የድምፅ መረጃ አፈትልኮ ወጥቷል፡፡

ኦሕዴድ ጉባዔውን አጠናቆ በደረሰበት መደምደሚያ ላይ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደስተኛ አለመሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ጉባዔው እንዳለቀ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በአዳማ ከተማ ከኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች ጋር እየመከሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊነት የተነሱት አቶ ሰለሞን ኩቹ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪ ሆነው መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ (ውድነህ ዘነበ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...