Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​የመንግሥት ተቋማት ሙስናን ለመከላከል አዲስ ስትራቴጂ እንዲቀርፁ ታዘዙ

​የመንግሥት ተቋማት ሙስናን ለመከላከል አዲስ ስትራቴጂ እንዲቀርፁ ታዘዙ

ቀን:

ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ሙስና የሚከላከሉበት አዲስ ስትራቴጂ ቀርፀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ታዘዘ፡፡ ስትራቴጂውን ቀርፀው ተግባራዊ ሳያደርጉ ቀርተው ለሚደርሰው ጥፋት ተቋማቱን የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት በቀጥታ ተጠያቂ እንደሚሆኑ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስጠንቅቀዋል፡፡

ማክሰኞ የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የመንግሥት ተቋማት የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ውይይት በተካሄደበት ወቅት፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደተናገሩት፣ የመንግሥት ኃላፊዎች የተመደበላቸውን በጀት፣ ንብረትና የሰው ኃይል ከሙስና በፀዳ መንገድ ማስተዳደር አለባቸው፡፡

‹‹ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ነድፈው ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚከሰት ችግር ተጠያቂው ኃላፊዎቹ ናቸው፤›› በማለት አቶ ደመቀ ከዚህ በኋላ መንግሥት የሚከተለውን አሠራር ተናግረዋል፡፡

ከታኅሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደ ሦስተኛው አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጉባዔ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመንግሥት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች የራሳቸውን የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ነድፈው ተግባራዊ እንዲያደርጉ መንግሥት መወሰኑን አስታውቀው ነበር፡፡

በዚህ መሠረት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት መነሻ የሚሆን ስትራቴጂካዊ ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፌዴራልና የክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች በሁሉም መሥሪያ ቤቶች የመከላከል ሥራ ማከናወን ስለማይችሉ መሥሪያ ቤቶች የራሳቸውን ትግል ማካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡

የፀረ ሙስና ተቋማት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መስፋት አንፃር የሚኖራቸው ሚና ውስን በመሆኑ፣ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው በማለት አቶ ወዶ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም በሁሉም የመንግሥት ተቋማት የሥነ ምግባር መኮንኖች መዋቅር እንዲከፈት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው ግምገማ፣ የተወሰኑ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ የሥነ ምግባር መኮንኖች ውጤታማ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ግን ደካማ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ መሆናቸው ታይቷል፡፡ የመሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎችም እንደማይተባበሯቸው፣ ከዚያም ባለፈ ጭራሽ የፀረ ሙስና ሐሳቡንም የማይደግፉ መኖራቸውን ተገንዝበናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚመድበው በጀት ከፍተኛ መሆኑ፣ የመንግሥት ተቋማት እየበዙ መምጣታቸው፣ በአንፃሩ ደግሞ የተጠያቂነት አሠራር  በተለይ በከተሞች አካባቢ መዳከሙ ሙስና እየተንሰራፋ እንዲካሄድ ምክንያት መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረው፣ ‹‹ሙስናን በበለጠ ቁርጠኝነት መዋጋት የሚገባን ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ሙስናን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትንና መልካም አስተዳደርን ለመዋጋት ቁርጠኛ እንደሆነ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዕለት ከዕለት እየተናገረ ቢሆንም፣ በሒደቱ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ጥቂት ግለሰቦች ውጪ ተግባራዊ እንቅስቃሴው ከንግግሩ ጋር አብሮ አይሄድም በሚል እየተተቸ ይገኛል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...