አርባ ዓመት ሊሞላው አራት ዓመት የቀረው ይህ (ፎቶ በግራ) ሞስኮ የተካሄደውን 22ኛው ኦሊምፒያድና ምሩፅ ይፍጠርን ያስታውሰናል፡፡ ሞስኮ ኦሊምፒክና ምሩፅ ይፍጠር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያስመሰለው ማርሽ ለዋጩ በ10,000 ሜትር እና በ5,000 ሜትር ሁለት ወርቅ ማግኘቱ ነበር፡፡
ይህ የምናየውና በጌቲኢሜጅስ (gettyimages) ማህደር ውስጥ የሚገኘው ፎቶ ዘመኑን ቢያስታውሰንም ካፕሽኑ (መግለጫው) ግን (Miruts Yifter of Ethiopia #191 passes compatriot Mohamed Kedir on his way to the gold medal in the Men’s 10,000 meters at the XXII Olympic Summer Games on 27th July 1980 at the Lenin Stadium in Moscow, Soviet Union.) ተዛብቷል፡፡
191 ቁጥር መለያ የለበሰው ምሩፅ ቢሆንም ከጎኑ ያለውና 182 ቁጥር መለያ የለበሰው ዮሐንስ መሐመድን በስህተት ‹‹መሐመድ ከድር›› ብሎታል፡፡ ሌላው ስህተቱ ፎቶው የተነሳበት ውድድር 10,000 ሜትር እንደሆነ አድርጎ መግለጹ ነው፡፡ ዮሐንስ በሞስኮ ኦሊምፒክ በ5,000 ሜትር ብቻ ነበር የተካፈለው፡፡ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ሁለት ዙር ገደማ ሲቀር ደህና ሄዶ ሳለ በነበረው ፍትጊያ ጫማው በመውለቁ ውጤታማ አልነበረም፡፡ በ10,000 ሜትር የተወዳደሩት ምሩፅ፣ መሐመድ ከድርና ቶሎሳ ቆቱ ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው ገቡ ሲባል (ፎቶ ከላይ) ከኋላ የደረሰው ፊንላንዳዊው ካርሎ ማኒንካ ሁለተኛ በመግባቱ መሐመድ ነሐስ፣ ቶሎሳ 4ኛ ሆኖ ዲፕሎማ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው የሪዮ ኦሊምፒክ የነምሩፅን ዓርማ ማን ያነሳ ይሆን?
(ሔኖክ ያሬድ)
***********************
ወንድማ…! ! !
አዬዬ እቱ
ወንድማ መች ጠፋ ብለሽ – የተፈጥሮ ድጉን የታጠቀ
የፆታ ስያሜ ፅናቱን – ወንድነቱን ያፀደቀ
ጎርናና ድምፁን ነዝሮ – ፍጥረታትን ያስደነቀ
በኩራት ኮርቻ ተንኳሎ – በወግ ያሸበረቀ
የዲግሪ ካባውን የጫነ – ሜዳልያ ያጠለቀ…
***
ሁሉም ወንድ ግን ወንድ አይሆን…
የትውልድ ቀየሽን ካልገራ
ለዘርሽ ምርጥን ካላረገ – በመስኩ ካልተሰማራ
ለክብርሽ ጌጣጌጥ ካልሆነ – በውስጥ ውበትሽ ካልበራ
ምኑን ‹‹የቤት ራስ›› ሆነ – ለሕንፃሽ ካስማን ካልሠራ
***
ወንድ ሚባለው ያኔ ነው …
ልጅሽ ባባቱ ሲጠራ
ለአለሙ ፋና ሆኖ – በድቅድቅ ሰማይ ሲበራ
የፈራረሱ ደጃፎችን – ሲያቀና ተዓምር ሲሠራ
መንጦላዕት አንደበቱ – ሙታንን ከቀብር ሲጠራ
ሚተራመሱ ‹‹በጎችን›› – ወደ ሕይወት መስክ ሲመራ…
ላመነበት ሲኖርለት
ለኖረለት ሊሞትለት
ፀንቶ ሚቆመው ነው
የወንድ ዘር የተካነው
ታዲያ ያንቺስ ‹‹ወንድ›› – ወንድ ነው?
ጳዝዮን – 2011
**********************
በማርች ኤይት የተደረጉ ንግግሮች
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ታይፒ ኤርዶጋን ሴቶች ከወንዶች እኩል አይደሉም፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም የአገር ክህደት ነው፣ ውርጃ ገደብ ሊጣልበት ይገባል፣ የቱርክ ሴቶች ቢያንስ ሦስት ልጆች መውለድ አለባቸው በሚሉት አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡
የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ ‹‹ሴቶች ከምንም በላይ ናቸው››፣ ‹‹ሴቶች እናት ናቸው፣ የሚናደዱ እንደሚኖሩ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ለእኔ ሴቶች ከእናትም በላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ቤተሰባዊነትን በማፍረስ ሴቶችን ነፃ ማድረግ አይቻልም›› ሲሉ መደመጣቸውን ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የካምቦዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁን ሰን ደግሞ፣ ‹‹ወንዶች ለራሳቸው የመብት ጥበቃ የሚያደርግ ተቋም ማቋቋም አለባቸው፣ እኔም የተቋሙ የክብር ፕሬዚዳንት ሆኜ ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡
ካምቦዲያ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴተኛ አዳሪዎች ማረፊያና መሸጋገሪያም ናት፡፡ ሆኖም ሰን፣ በዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የወንዶች መብት እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ብዙ ሴቶች ባሎቻቸው ‘ቆንጆ ሴት ያይብናል’ ብለው ስለሚፈሩ የሰርግ ግብዣ ላይ እንዲገኙ አይፈቅዱም፡፡ ኢ-ፍትኃዊነቱ ማክተም አለበት›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሚስቶች እባካችሁ የባሎቻችሁን ልቦና ተረዱላቸው›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዕለቱን አስመልክተው በምሥል በለቀቁት መልዕክት፣ ሴቶችን አወድሰዋል፣ አመስግነዋል፡፡ ‹‹የሴቶች ክብርና ይቅር ባይነት የሩሲያዊነት ተምሳሌት ነው›› ብለዋል፡፡
ሴቶች ሕይወት ይሰጡናል፣ በፍቅራቸው ያሞቁናል፣ ይንከባከቡናል ይደግፉናል ያሉት ፑቲን፣ ‹‹እናንተ ለዓለም ደግነትን፣ ውበትን፣ ብርሃንንና ተስፋን አምጥታችኋል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ፑቲን በመልዕክታቸው፣ ሴቶችን ደግፈው፣ የይቅርታ ተምሳሌት፣ የሩሲያም መገለጫ ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹ከመንፈሳችሁ ጥንካሬና ከጀግንነታችሁ እውነተኛ ወንድ መሆንን፣ በተቃርኖ የሚመጣብንን ሁሉ ማሸነፍን ተምረናል›› ብለዋል፡፡
ለሴቶች በላኩት ግልጽ ደብዳቤም፣ ‹‹ሴቶች የድብቅ ኃይል ባለቤቶች›› ሲሉ አወድሰዋል፡፡
****************************
ፌስቡክና ሙታን በምዕት ዓመቱ ማብቂያ
ፌስቡክ በምዕት ዓመቱ ማብቂያ በሕይወት ካሉት ይልቅ የሌሉት አባላቱ እንደሚበዙ ጥናት አመለከተ፡፡ ኢንዲፔንደንት ጥናቱን ጠቅሶ እንደሚለው፣ ፌስቡክ በምዕት ዓመቱ ማብቂያ፣ በሕይወት ኖረው ከሚጠቀሙት ይልቅ፣ ዲጂታል የሙታን መታወሻ ይሆናል፡፡
ማኅበራዊ ድረ ገጹ እ.ኤ.አ. በ2098 በሕይወት ከሚኖሩት፣ በማይኖሩት አካውንት ይሞላል ሲሉ በማሳቹሰትስ ዩኒቨርሲቲ ዶክትሬታቸውን እየሠሩ የሚገኙት ሃሺም ሳዲቅ ተናግረዋል፡፡ የድረ ገጹ ተጠቃሚ የነበሩና የሞቱ ቁጥርም እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
የፌስቡክ ተጠቃሚው ሲሞት የአካውንቱን ሙሉ መረጃ የሚያውቅ ካልሆነ፣ ማንም ከድረ ገፁ ሊያጠፋው አይችልም፡፡ በመሆኑም የሙታን አካውንት ከቋሚዎች እየበለጠ ይሄዳል ሲሉ ገልጸዋል፡፡