Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች የደረጃ ጥያቄ

የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች የደረጃ ጥያቄ

ቀን:

አውቶቡስ ተራ በሻጭና ገዥ ግርግር ተውጣለች፡፡ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ ያሉ መንደሮችም ሩጫ ውስጥ ባሉ ሰዎች ተጨናንቋል፡፡ በመንደሩ ውስጥ ካሉ ቤቶች በአንዱ ግን ፀጥታ ሰፍኗል፡፡ ቤቱ በዕድሜ ብዛት ዘመም ብሏል፡፡ መግቢያው ላይ የተቀመጡት አዛውንት አራት መዓዘን ያለው መጠነኛ ሳጥን ይሠራሉ፡፡ ሳጥኑ ውስጥ ረዘም ያለ እንጨት ከተቱና መታ መታ አደረጉት፡፡ አዛውንቱ መሰንቆ እየሠሩ ነበር፡፡ አጠገባቸው የተጠገኑ አሮጌ ክራሮችና መሰንቆዎች እንዲሁም አዳዲስ ምርቶች ይስተዋላሉ፡፡

የ62 ዓመቱ የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ሠሪና ጠጋኝ አቶ ታደሰ እጅጉ ናቸው፡፡ ወደ ሙያው ከገቡ ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ ዕድሜ ቢጫናቸውም ሙያቸውን አልተውትም፡፡ የተወለዱት አጋሮ ነው፡፡ ለቡና ለቀማ ከ18 ጓደኞቻቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም፣ የሙዚቃ ፍቅር አሸነፋቸው፡፡ በወጣትነታቸው ከለማ ገብረሕይወት፣ ወረታው ውበትና ከድምፃዊት ባለቤታቸው ከበቡሽ አየለ ጋርም በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ለዓመታት መሰንቆ ተጫውተዋል፡፡

የሙዚቃ መሣሪያ ሥራ የለመዱት ከጎረቤታቸው ነው፡፡ ጎረቤታቸው ሲሞቱ ከባለቤታቸው ጋር በሚኖሩበት መጠነኛ የቀበሌ ቤት ውስጥ መሥራት ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ጥገና ገቡ፡፡ ከቀድሞዎቹ ኤልያስ  ተባበል፣ ዓለሙ በላይና ሌሎችም ሙዚቀኞች ደንበኞቻው ነበሩ፡፡ አሁን በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ እየተጋበዘ መሰንቆ የሚጫወተውና ‹‹ቱፓክ›› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ፣ በእሳቸው የተሠራ መሣሪያ ተጠቃሚ ነው፡፡

የሙዚቃ መሣሪያ ሲሠሩ፣ ለተጫዋቾች ይመጥናል ባሉት መጠን ነው፡፡ መሣሪያዎቻቸው ተመሳሳይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ መሰንቆና ክራር ለመሥራት የሚጠቀሙበትን ዋንዛ፣ ጥድ፣ የፈረስ ጭራ፣ የፍየል ቆዳ፣ ሰሀን፣ ገበቴና የዓሳ ማጥመጃ ለማግኘት መርካቶ ኮርቻ ተራ ይሄዳሉ፡፡ ለጥገናም የተለያዩ የእንጨት ሥራ መሣሪያዎች ይጠቀማሉ፡፡ የመሰንቆ ጭራ ሲያልቅ ወይም የክራር ሳጥን ቆዳ ሲቀደድ እንደ ጉዳቱ መጠን ያስከፍላሉ፡፡ ቀድሞ መሰንቆ በ70 ብር፣ አሁን በ700 ብር፣ ክራር ቀድሞ በ300 ብር አሁን በ1,000 ብር ይሸጣሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ገበያ ላይ ካሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ሰፊ የደረጃ (ስታንዳርድ) ልዩነት አለ፡፡ ከመጠን አንስቶ እስከ ጥሬ ዕቃና አሠራር ወጥነት ይጎላቸዋል፡፡

በአንድ መንገድ የሙዚቃ መሣሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሲያልፉ፣ የነሱ አሠራር አብሯቸው ያልፋል፡፡ የመሣሪያዎች አሠራር ደረጃ ቢኖረው ባለሙያዎች አንድ ዓይነት መርሕ በመከተል ተመሳሳይ መሣሪያ እንዲሠሩ ከማስቻሉ ባሻገር ለተጫዋች ምቹ እንደሚሆን ያምናሉ፡፡

የአቶ ታደሰን ሐሳብ የሚጋሩ የሙዚቃ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ዓለም ላይ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲሠሩ ደረጃ ይከተላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ዝግጅት ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ መሣሪያዎቹ ሲሠሩ የሚከተሉት ወጥ ደረጃ ባለመኖሩ የተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ያመርታሉ፡፡ ወጥነት አለመኖሩ በሙዚቃ ሥራዎቻቸው ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸው የሚናገሩ የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች አሉ፡፡ በሌላ በኩል የሙዚቃ መሣሪያዎቹን ለመጠገንም ፈታኝ እንደሚያደርገው ያክላሉ፡፡

ክራር ተጫዋቹ ፋሲካ ኃይሉ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲሠሩ በተመሳሳይ ደረጃ አለመሆኑ ሙዚቀኞችን እንደሚፈትን ይናገራል፡፡ ላለፉት 18 ዓመታት ቤዝ ክራርና ሊድ ክራር በተለያዩ ቦታዎች እንዲሁም የባህል ባንዶች የተጫወተ ሲሆን፣ ለዓመታት የተደቀነበትን ፈተና ለመወጣት ባለ 12 ክር ክራር መሥራቱን ይናገራል፡፡ የሙዚቃ ፍቅር ካደረበት ጊዜ ጀምሮ ከአጥር ላይ ሠንሠል በመቁረጥ ባለአንድ ገመድ ክራር አዘጋጅቷል፡፡ ከብረት ሰሀንና ከመርቲ ቆርቆሮም ክራር ሠርቷል፡፡ ወደ ፕሮፌሽናል የሙዚቃ ዓለም ሲገባ ደግሞ ባለሙያዎች በትዕዛዝ እያሠራ ራሱም እያዘጋጀ ተጠቅሟል፡፡

‹‹በባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ዝግጅት ይሄ ነው የሚባል ቀመር የለም፤ በየዘመኑ የተለያየ ክራር ስለሚሠራ የታዋቂ ክራር ተጨዋቾችን ሥራ ዳግም ለመሥራት ያስቸግራል፤›› ይላል፡፡ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በደረጃና በመስፈርት እንዲሠሩ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች ቢኖሩም፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት  አናሳ በመሆኑ እስከዛሬ ተጨባጭ ለውጥ እንዳልመጣ በመሆኑም የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ተጨዋቾች ትርዒት ሲያቀርቡ እንደሚፈተኑ ፋሲካ ይናገራል፡፡

እሱ በተጫወተባቸው መድረኮች ዋሽንት፣ መሰንቆና ከበሮ ተጨዋቾች ለመናበብ ሲቸገሩ አይቷል፡፡ የሚፈልጉትን ድምፅ ለማግኘት ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ ‹‹ደረጃና መስፈርት የግድ ያስፈልጋል፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ሙያተኞች መሰብሰብና መወያየት፣ የሚመለከታቸው ተቋሞችም ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፤›› ይላል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችም መሣሪያዎች ባህላዊ ይዘታቸውና ድምፃቸው ሳይቀየር በደረጃና መስፈርት እንዲሠሩ መገፋፋት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡

ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የባህል ሙዚቃ መምህር የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ፈንታ፣ የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች አሠራር ጥናት እንደሚጎለው ይናገራሉ፡፡ እሳቸው የመሣሪያዎቹን አሠራር ደረጃ ለማስያዝ የተለያዩ ጥናቶች ቢሠሩም ወደ ተግባር አልተለወጡም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከማይነቅዝ ዋንዛና ሸንበቆ፣ ድምፅ ከሚያነጥር ጥቁር እንጨት ይሠራሉ፡፡ ከጅማት የተሰፉ፣ በፈረስ ጭራ የሚሠሩና በቆዳ የተወጠሩም ናቸው፡፡ ግብዓቶቹ ተመሳሳይ ቢሆኑም አሠራራቸው የተለያየና ዘልማዳዊ ነው፤ ስናስተምር በድምፅ እየተከተልን እንቃኛለን እንጂ፣ የመሣሪያዎቹ በመጠን መለያየት ችግር ይፈጥራል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

የመሣሪያዎቹ ወጥ አለመሆን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዳያገኙም ያደርጋል ይላሉ፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዎች ደረጃ ወጥቶላቸው በፋብሪካ መሠራት እንዳለባቸውም ይመክራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ካላቸው ረዥም ዕድሜና በዘርፉ ያሉ ተቋማት ዕድሜ አንፃር እስከዛሬ ስታንዳርድ አለመበጀቱ ለዘርፉ አነስተኛ ቦታ ተሰጥቶታል የሚለውን ሐሳብ አስተያየት ሰጪዎች ይጋራሉ፡፡ ባህላዊ ሙዚቃ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠውና ዘልማዳዊ አካሄዱ ሊቀየር እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ መሣሪያዎቹ የሚዘጋጁበት ግብዓትና ለመሥሪያ የሚውሉ ቁሳቁሶች መለያየት በሙዚቃው ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ የበለጠ አሳሳቢ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቅርሳችን፣ እሚያስከብሩንና የማንነታችን መገለጫ ለሆኑት የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች አሠራር ደረጃ ለመስጠት የባለሙያዎች ርብርብ ይሻል፤›› ይላሉ፡፡

የደረጃ አለመኖር የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ችግር ቢሆንም፣ መሣሪያዎቹን በየራሳቸው መንገድ በመሥራት ለገበያ የሚያቀርቡ ጥቂት አይደሉም፡፡ ሲሳይ በገና የዜማ ማሠልጠኛ፣ አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ባለው ወርክሾፑ ውስጥ በገና፣ ክራር፣ መሰንቆ አልፎ አልፎም ዋሽንትና ከበሮ ይዘጋጃል፡፡ በወርክሾፑ ለእንጨት ሥራ የሚውሉ የተለያዩ መሣሪያዎች ይገኛሉ፡፡ የተቋሙ ምርት ክፍል ኃላፊ ፍፁም ግሩም እንደሚናገረው፣ መሣሪያዎቹን የሚያዘጋጁበት የራሳቸው ደረጃ አውጥተው ይሠራሉ፡፡

መሰንቆ በ80 ሳንቲሜትር ቁመት፣ የሳጥኑን ጎን 28 በ28፣ ውፍረቱን 11 በ11 በማድረግ ከፍየል ቆዳና ከፈረስ ጭራ ሠርተው በ1,000 ብር ይሸጣሉ፡፡ ለክራር የሚጠቀሙት እንጨት ፅድ ሲሆን፣ ደጋኑ ከቀረሮ ይሠራል፡፡ ሳጥኑን ከብረት ሰሀን ይሠሩ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን በእንጨት ገበቴ ይጠቀማሉ፡፡ በገናን በ1፡30 ቁመትና 50 ሳንቲ ሜትር የጎን ርዝመት በዋንዛ ይሠራሉ፡፡ ሳጥኑ ከበሬ ቆዳ፣ አውታሩ ከበግ አንጀት ተዘጋጅቶ 3,000 ብር ይሸጣል፡፡ ዋሽንት የሚያዘጋጁት በተለያየ መጠን ሲሆን፣ ለሚፈለገው ቅኝት የሚሆን ዋሽንት ከሸንበቆ ይሠራል፡፡ መሣሪያዎቹ የሚዘጋጁት ለጥገና በሚመች መንገድ እንደሆነ ፍፁም ይናገራል፡፡ መለዋወጫዎች ተዘጋጅተውም እንደየአስፈላጊነቱ ይጠገናል ይላል፡፡

የዜማ መሣሪያዎቹን ለዓመታት የሠራውና አጨዋወታቸውን የሚያስተምረውም የትምህርት ቤቱ ባለቤት ሲሳይ ደምሴ፣ ከዓመታት ጥናት በኋላ በትምህርት ቤቱ ደረጃ ቢፈጥርም፣ ከትምህርት ቤቱ በዘለለ ለኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች እንደማይሠራ ያስረዳል፡፡ በባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ዝግጅት ላይ ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችና በሙዚቃው ዘርፍ የሚሠሩ መንግሥታዊም ይሁን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጥምረት ካልሠሩ ለውጥ እንደማይመጣም ይናገራል፡፡

እሱ፣ የመሣሪያዎቹን አሠራር ራሱን በራሱ አስተምሯል፡፡ በ1989 ዓ.ም. የበገና ደርዳሪ ዓለሙ አጋ አልበም ፖስተር ላይ ያለውን በገና ተመልክቶና ከቁመታቸው ጋር አመጣጥኖ በግምት የመጀመርያ በገናውን ሠራ፡፡ መሣሪያዎቹን መጫወት ስለሚችል በራሱ ልኬት እየተመራ መሥራቱን ገፋበት፡፡ ሆኖም አቅጣጫ የሚያመላክት ጽሑፍ ያለመኖሩ የመሣሪያዎቹን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል ይላል፡፡

ስለመሣሪያዎቹ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ቢደረግ በሙያቸው ለደረጃ መፈጠር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ አካላትን እንደሚያነቃ ያምናል፡፡ ‹‹በኢንጂነሪንግ፣ በፊዚክስና ሌላም ሙያ የተሰማሩ ተማሪዎች በመሣሪያዎቹ መጠን ድምፅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ችግር ሲያዩ የሚፈታበትን መንገድ ይጠቁማሉ፤›› ይላል፡፡ ከትምህርት ቤቱ በዘለለ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ሙያተኞች ጊዜ፣ ገንዘብና የሰው ኃይል ተጣምሮ መፍትሔ እንዲሰጥም ያሳስባል፡፡

ዋሽንት ተጫዋቹ ጣሰው ወንድም፣ ከሌሎቹ የተለየ ሐሳብ አለው፡፡ በእሱ እምነት፣ ወጥ ደረጃ ለመፍጠር ሲሞክር የመሣሪያዎቹ የመጀመሪያ ይዘት ሊጠፋ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ያሉ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ፋብሪካ ሳይገቡ በእጅ ይሠራሉ፡፡ እንደየአስፈላጊነታቸውም ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እሱ 30 ዋሽንት አለው፣ አንድ ሙዚቃ ሲጫወት እስከ አራት ዋሽንት ሊጠቀም ይችላል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ይህ መንገድ ሙዚቀኞችን ይፈትናል ቢሉም ጣሰው አይስማማም፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሣሪያዎች እንደመጠናቸው ልዩነትና አሠራራቸው የተለያየ ቅላፄ ይፈጥራሉ ይላል፡፡ በትግራይ፣ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ያለውን ክራር ልዩነት እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ ለባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ደረጃ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሚሆንና ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ሊጋፉ እንደሚችልም ያምናል፡፡ ‹‹የተለያየ ሸንበቆ በመጠቀም የተያየ ዋሽንት ሲሠራ ያለው ተፈጥሯዊ ቃና ልዩ ነው፡፡ ብዙዎች ለምን ይኼን ሁሉ ዋሽንት ይዘህ ትሄዳለህ? ይሉኛል፡፡ አንዱ ሸንበቆ ግን ከሌላው ይለያል፡፡ የምፈልገውን ድምፅ የሚሰጠኝን እየቀያየርኩ መጫወት እመርጣለሁ፤›› ይላል፡፡

በ2000 ሐበሻ የባህል ሙዚቃ ተጫዋቹ በኃይሉ ዘርዓይ በበኩሉ፣ የመሣሪያዎች ደረጃ አለመኖር፣ ቶሎ እንዲበላሹ፣ ለጥገና ምቹ እንዳይሆኑ ያደርጋል ይላል፡፡ ዛሬ ላይ አምራቾች ስለወጥነት ወይም ስለሚጠቀሙበት ጥሬ ዕቃ ሲጨነቁ አይስተዋልም፡፡ ለመሣሪያዎቹ መለዋወጫ ማግኘት የሚቸግራቸውም በአንድ ተቋም በወጥነት ስለማይመረቱ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

‹‹ደረጃ አለመኖሩ የተለያየ ሰው በተለያየ መንገድ እንዲሠራው አድርጓል፡፡ በዚህም ሙዚቀኛው ይፈተናል፡፡ የአንድ ሙዚቃ መሣሪያ ችግር በትርዒት ወቅት ሌሎችንም ይረብሻል፤ አንዳንዴ በሙዚቀኞች መካከል አለመግባባትም ይፈጥራል፤›› ይላል፡፡ በዚህ ረገድ መጠነኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ተቋሞች ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጋር ይስማማበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...