Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​ከስድስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ተሰጠ

​ከስድስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ተሰጠ

ቀን:

በአገራችን ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በስፋት የሚታየውን የማህፀን በር ካንሰር በሽታ ለመከላከል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከስድስት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተርና የክትባት ኬዝ ቲም አስተባባሪ እንደገለጹት፣ ሚኒስቴሩ በሁለት ዓመት የሚተገበረውን የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የሙከራ ፕሮጀክት የጀመረው ጋቪ (Gavi) ከተባለው አጋር ድርጅት ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ ክትባቱም በትግራይ ክልል ዓዲ ኣህፈሮም ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ጎማ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ፣ ከዘጠኝ ዓመት እስከ 13 ዓመት የዕድሜ ክልል ባሉና አራተኛ ክፍል ተማሪዎች ይተገበራል፡፡

አንዲት ታዳጊ ልጃገረድ በስድስት ወራት ልዩነት ውስጥ በዓመት ሁለት ዶዝ ክትባት ማግኘት ስለሚኖርባት፣ ክትባቱ የሚካሄደው በሁለት ዙር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ካለፈው ታህሳስ ጀምሮ በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ ላይ አንደኛውን ዶዝ ክትባት ለ7217 ታዳጊ ልጃገረዶች ለመስጠት ታቅዶ 6681 ማለትም 92.6 በመቶ ያህሉ ተከትበዋል፡፡

በሌሎች አገሮች በሙከራ ፕሮጀክት እንዲተገበር ከሚያዘው ዕቅድ ውስጥ ቢያንስ 50 ከመቶ ያህል ሽፋን ማግኘት ከተቻለ እንደ ከፍተኛ ውጤት ተደርጎ እንደሚወሰድ፣ ከዚህ አንፃር በመጀመሪያው ዙር ክትባት ለመድረስ ይጠበቅ የነበረው የሽፋን መጠን 80 ከመቶ እንደነበር ሆኖም የአገሪቱ የጤና ሥርዓት በጥሩ ሁኔታ ላይ በመገኘቱ ከተጠበቀው የበለጠ ውጤት ሊገኝ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

ክትባቱ ከዘጠኝ እስከ 13 የዕድሜ ክልል ሊወሰን የቻለው አንዲት ልጅ ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ከመጋለጥዋ በፊት ክትባቱን ማግኘት ስላለባት ነው፡፡

በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉ ልጃገረዶችን ማግኘት የሚቻለው በትምህርት ቤቶች ውስጥ በመሆኑ ክትባቱ የተሰጠው በየትምህርት ቤቶች በመዘዋወርና ልጃገረዶቹ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳሉ ነው፡፡

ወ/ሮ ሊያ እንደሚሉት፣ የመጀመሪያው ዙር የክትባት ሥራ የተከናወነው ከክልል ትምህርትና ጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ በዚህም ተጠቃሚ የሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች ሁለተኛውን ዶዝ የመከላከያ ክትባት በመጋቢት 2008 ዓ.ም. በሚከናወነው ሁለተኛው ዙር ዘመቻ ይከተባሉ፡፡ ይህ ሲከናወን ልጃገረዶቹ የመከላከል አቅም አላቸው ተብሎ ይወሰዳል፡፡

የመጀመሪያው ዓመት የሙከራ ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛው ዓመት ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም. ከመጀመሩ አስቀድሞ ግን፣ በመጀመሪያው ዓመት የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች፣ የሽፋን መጠኑና ለዚህም ማስፈጸሚያ የወጣው ወጪ ይገመገማል፡፡ ግምገማውም ያስገኘው ውጤትና የተደረሰበት ጠንካራ ጎን ለቀጣዩ ዓመት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ በግብዓትነት ይወሰዳል፡፡ የቀጣዩም ዓመት አፈጻጸሙ ከተገመገመ በኋላ አዋጭነቱ ታይቶ ወደማስፋፋቱ ስትራቴጂ ይኬዳል ብለዋል፡፡

ለሙከራ ፕሮጀክት ተግባራዊነት ሁለቱ ወረዳዎች የተመረጡት በምን መስፈርት ነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አስተባባሪዋ እንደመለሱት፣ የሙከራ ፕሮጀክቶች በሚተገበርበት ጊዜ ሁለት ነገሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ግድ ይላል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ፕሮጀክቱ የሚተገበሩባቸው የአገር አቀፍ ሁኔታዎችን የሚያሳዩ ቦታዎች መሆን ሲኖርባቸው ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ሽፋኑ በተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት አለበት ብለዋል፡፡

ይህም አካሄድ ተማሪዎቹን በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳሉ ለማግኘትና በቀጣዩም ዓመት ለሚከናወነው የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በአንድ ወረዳ ላይ ብቻ እንዲሆን ያልተደረገበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ለማነፃፀር እንዲረዳ በማሰብ ነው፡፡ በሁለቱ ወረዳዎች ያለው የትምህርት ሽፋንና የጤና ልማት ሠራዊት ግንባታዎቻቸው አንድ አይደሉም፡፡ ሌሎችም የተለያዩ በዝርዝር ሊገለጹ የሚችሉ ልዩነቶች ስላሉ የኢትዮጵያን ሁኔታ ሊያሳይ ይችላል፣ በቀጣይም በመደበኛ ክትባት ለመስጠት እንደማሳያ ስለሚያገለግል ስፍራዎቹ መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ሊያ፣ የሙከራ ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ሥፍራዎች ዩኒቨርሲቲዎች መኖር ያለባቸው ዩኒቨርሲቲዎቹ በቅርብ ርቀት ሆነው ጥናት ለማካሄድ፣ የሚሠራውን ሥራ ለመመልከትና ለመገምገም እንዲሁም ግብረ መልስ ለመስጠትና ከዚያ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ቀጣይ ሥራ ለማከናወን ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...