Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​የመኖር ሁለተኛ ዕድል

​የመኖር ሁለተኛ ዕድል

ቀን:

ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 221 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር አሚባራ የምትባል ከወረዳ ነች፡፡ በወረዳዋ ወደ ድሬዳዋ፣ ሐረርና አፋር ጂቡቲ የሚወስዱ መንገዶች ለሁለት ተከፍለው፤ ወደ አፋር ጂቡቲ ከሚወስደው ዋናው መንገደ 1.2 ኪሎ ሜትር ገንጠል ብሎ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ፣ የኢትዮጵያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ ይገኛል፡፡

ማሠልጠኛው የተቋቋመው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ በተለያዩ ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙና በተለያየ ምክንያት ጎዳና የወጡ ወገኖችን ማስተማርና አሠልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት አንዱ ዓላማው ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዴቨሎፕመንት አሶስዬሽን ጋር በመተባባር እየሠራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደርጉ የነበሩትን ያሠለጠነ ሲሆን፣ ዘንድሮም በሦስተኛ ዙር 10,375 ጎዳና ተዳዳሪዎችን አሠልጥኖ አስመርቋል፡፡

ወጣት አብነት ገመቹ፣ አዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ አባቱን አያውቅም የኖረው ከእናቱ ጋር ነው፡፡ እናቱ በሞት ሲለዩ በልጅነቱ ጎዳና ወጣ፡፡ ወደ ማሠልጠኛው የገባው በጎዳና ሕይወት በተማረረበት ወቅት ነበር፡፡ ከእሱ በፊት ጎዳና ላይ ይኖሩ የነበሩና ማሠልጠኛ የገቡ ልጆች ሕይወት ተለውጦ በመመልከቱ ተመዝግቦ ሥልጠናውን እንዲቀላቀል እንዳደረገው ይናገራል፡፡ አሥራ ስምንት ዓመታትን በናዝሬት፣ በዝዋይ፣ በአዋሳ መጨረሻም በአዲስ በጎዳና ላይ አሳልፏል፡፡ አስከፊነቱ ከዚህ እስከዚህ ነው በማይባለው የጎዳና ሕይወት መከራ አይቷል፡፡ በተለያዩ ነገሮች ለጊዜው ራሱን ለማረጋጋት ቢሞክርም መከፋት የሁልጊዜው ነው፡፡ ምን እበላለሁ? እንዴት አድራለሁ? በየቀኑ ጥያቄው ነው፡፡ በጎዳና ሕይወት ‹‹እንቅልፍ እንቢ አለኝ ይህ ምግብ  እንደዚህ ነው፣ ይህ ልብስ ጠቦኛል፣ ሰፍቶኛል ቆሽሿል የሚባል ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ እኔ ጠዋት እነሳለሁ ሽቀላ ካለ ዞር ዞር እላለሁ፡፡ ቁርሴንም ምሳዬንም ያገኘሁት ሆቴል ትርፍራፊ በመልቀም ሁሉም ሱስ ስላለብኝ ጫትና ሲጋራዬን ካገኘሁም ጋንጃዬን ይዤ እስከማታ ወደ ቦታዬ እመለሳለሁ›› በማለት የነበረበትን አስከፊ ሁኔታ ያስታውሳል፡፡ ሲመሽ ደግሞ ጨብሲ የግድ ነው፡፡ ጠላ አረቄ እሱንም ወስዶ እንቅልፍ እምቢ ካለ ማስቲሽና ቤንዚል በማሽተት ለማንቀላፋት ሳይሆን ራሱን ለመሳት ይሞክራል፡፡ አንዳንዴ ሁሉም ነገር ሲጠፋ ደግሞ ወደ ሌብነትና ማጅራት መምታት ይሄዳል፡፡ በዚህ የተለያዩ እስር ቤቶችን ጎብኝቷል፡፡ ‹‹ማንም ዞር ብሎ የሚጠይቀኝና የሚያየኝ ስለሌለ እስሬን እየጨረስኩ ነበር የምወጣው፤›› ይላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እሱ እንደሚለው ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ የጎዳና ልጆች ጋር ፀባያቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም እንዳገኙ የዛሬን ብቻ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ብዙ ብር ተቀብለው ባህር ተሻግረው ወደ ውጪ ለመሄድ ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር ቤተሰቦቻቸውን በድጋሚ ላለማየት አፍረው ጎዳና የሚቀላቀሉ አሉ፤ ቤተሰብ እንደሞቱ የሚያስባቸውና እርም ያወጣባቸውም መኖራቸውን ይናገራል፡፡ ‹‹በጣም ሱሰኛ በመሆኔ ሱሴን ለማሳካት የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ሁሌ ስለምደባደብ ከፊቴ ላይ ጠባሳ አይጠፋም፡፡ የገለጽኩትን የአንድ ቀን ውሎዬን ላለፉት 18 ዓመታት አሳልፌዋለሁ፤›› በማለት በ60 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ባረፈው አዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ ሆኖ አስከፊውን ጊዜ ያስታውሳል፡፡

የአካባቢው ሙቀት እስከ 38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል፡፡ በተከሰተው ድርቅ በአካባቢው ያሉ ግራሮች ደርቀው በረሃነቱ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ማሠልጠኛ ወደ ጂቡቲ ከሚወስደው ከሚወስደው ዋና መንገድ 1.2 ኪሎ ሜትር ገባ ያለ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ማሠልጠኛው 10,375 የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩን አሠልጥኖ እንደሚያስመርቅ ያደረገው ዝግጅት ከመግቢያው ያስታውቃል፡፡ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ደግሞ ከግቢ ውጪ ያለውን በረሃ የሚያስረሳ ነገር ይመለከታሉ፡፡ የተተከሉ የዛፍ ችግኞች ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ ይህ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ቦታውን አረንጓዴ አላብሷል፡፡ የውስጥ ለውጥ መንገዶች፣ የተማሪና ያስተማሪ ማደሪያ ቤቶች፣ የተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች እንደየደረጃቸው ተገንብተው ይታያሉ፡፡ የውኃ ችግር እዛው በተቆፈሩ ጉድጓዶች የተቃለለ ሲሆን፣ ግቢው ፅዱ ነው፡፡ በሠልጣኞች የተዘሩ የበቆሎና የተለያዩ ማሳዎችም የሚናገሩት ብዙ ነገር ያለ ይመስላል፡፡

በቅጥር ግቢው ጥብቅ ሥነ ሥርዓት አለ፡፡ ማንም ሰው ያለ ሥራ በማይመለከተው ቦታ ሲዘዋወር አይታይም፡፡ እያንዳንዱ የተሰጠውን ኃላፊነት ይወጣል፡፡ ከፍተኛ የዲሲፕሊንና ሥነ ምግባር በተማሪውም  በአስተማሪውም ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ሠልጣኞቹ ማሠልጠኛውን የበረሃ ገነት አድርገው ይመለከታሉ፡፡

በማሠልጠኛው አካባቢ ምንም ዓይነት የጫት መደብር ወይም መጠጥ ቤቶች አይታዩም፡፡ ይህ ለተማሪዎቹ ሥልጠና ውጤታማነት ከፍተኛ አወንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ ማሠልጠኛወ ያለ ብዙ ወጪ መኖሪያ አካባቢን ምቹ ማድረግ እንደሚቻል በተግባረ ማሳየቱን የሚመሰክሩ በርካታ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሠልጣኞች አፈሩን በማስተካከልና በደረጃ መልክ በመሥራት ልክ እንደ ስታዲየም የሠሩት መቀመጫ ለምርቃት ዕለት ለታዳሚዎች መቀመጫ፤ እንዲሁም ደግሞ ለስፖርት መመልከቻ ሆኗል፡፡ በዚህ መልኩ የተሠሩት መቀመጫዎች 5,000 ሰው ያስተናግዳሉ፡፡

በቡድን በቡድን ሆነው የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወደሚካሄድበት ቦታ ከሚተሙት ሠልጣኞች ከላይ ታሪኩን የነገረንን አብነት ገመቹን ምን ተሰማህ? አልነው ‹‹ወደዚህ ስመጣ ለጥቂት ቀን ይሆነኛል ብዬ ፓኮ ፓኮ ሲጋራ ይዤ ነበር እዚህ ማስገባትም ማጨስም እንደማይቻል በመንገር በር ላይ ተቀበሉኝ፡፡ የተቀበሉኝ ግን ሲጋራውን ብቻ ሳይሆን ከ18 ዓመት በላይ የያዝኩትን ሱስና መጥፎ ባህሪዬን ነበር›› በማለት መለሰ፡፡ ይህ ዕድል ለራሱ፣ ለአገሩና የበደለውን ኅብረተሰብ ለመካስ የመኖር ሁለተኛ ዕድል እንደሆነም ይናገራል፡፡

ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዴቬሎፕመንት አሶስዬሽን የአዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ አጋሮች ናቸው፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠልጣኞቹን የመመዝገብና ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸው የማድረግ ኃላፊነትን ይወጣል፡፡ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱል ፈታህ አብዱላሂ በቁጥቁጥ ነገርና እንዲሁም የተበታተነ አሠራርን የሚያስተካክልና የዚህ ዓይነቱን እንቅስቃሴ የሚደግፍ አዲስ የማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲ መውጣቱ በዚህ ረገድ ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ፖሊሲው እየተፈጸመ ሲሄድ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች እየተፈቱ ስለሚሄዱ እንደ ተመራቂዎቹ በማኅብራዊ ኑሮ የተጎዱ የሚጠቀሙበትና ወደ መደበኛው ኑሮ የሚመለሱበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

አቶ የማነ ወልደማርያም የኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዴቨሎፕመንት አሶስዬሽን መሥራችና ኃላፊ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ በፊት በልመና የተሰማሩን ከመንገድ ላይ በመሰብሰብና ወደ ቀያቸው በመመለስ እንዲቋቋሙ ማቋቋሚያ በመስጠት ልመና ሳይወጡ ባሉበት ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ይሠራ እንደነበር አስታውሰው፡፡ ችግሩ የከፋው ግን የጎዳና ልጆች ላይ መሆኑን በመመልከት ፕሮጀክት በመቅረጽ ሙሉ በሙሉ ከአገር ውስጥ በሆነ ወጭ እንዲሠለጥኑና ሕይወቻው እንዲቀየር በጋራ መንቀሳቀሳቸውን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ልጆቹን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ወደ ማዕከላችን እናመጣለን ብዙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይመጣሉ፡፡ ማስተርስ ዲግሪ ያለው፣ ውጭ አገር የኖረና በሱስ ምክንያት ቤተሰቡን የበተነ የጎዳና ተዳዳሪ ወደ እኛ በሚመጡበት ወቅት ሁሉም በር ላይ ደስ በሚል አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ አዲስ ልብስና አዲስ መኝታ በእኩል እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ሙሉ የጤና ምርመራና ከሁለት እስከ ሦስት ወር የሥነ አዕምሮ ምርመራ ይከታተላሉ፡፡ የሥነ ምግባር ትምህርትም ይከታተላሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ወደ ትምህርትና ሥልጠና የሚገቡት፡፡ በግቢው ውስጥ ከስምንት እስከ ዘጠኝ ወር ቆይታ ይኖራቸዋል፡፡ ኤልሻዳይም በዚህ ቆይታቸው የምግብና የአንዳንድ ወጪዎችን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ሠልጣኝ ነች፡፡ ፀሐይ ዳኜ ትባላለች፡፡ ጎንደር ከተማ ፒያሳ አካባቢ ጎዳና ተዳዳሪ ነበረች፡፡ ጎዳና ላይ ከወጣች ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የጎዳና ሕይወት በተለይም ለሴት ልጅ አስከፊ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ እንደ ብዙዎቹ እሷም ሱሰኛ ነበረች፡፡ እሷ ለሥልጠናው ስትመዘገብ ጓደኛዋ ግን እምቢ ብሎ መቅረቱን ትናገራለች፡፡ ‹‹መጀመሪያ ፈርቼ ነበር ወንዶችን ሳይና ብዛታችንን ስመለከት ውትድርና የምንሄድ ነበር የመሰለኝ፡፡ ከዚያ እንደምንም ገባሁ ከጎዳና ሕይወት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሰው መጠለያ ውስጥ ገላዬን ታጠብኩ፡፡ ጥሩ አቀባበል አገኘሁ፡፡ የሕክምና ምርመራ ተደረገልኝ፡፡ የአንድ ወር ጽንስ እንደያዝኩ ተነገረኝ፡፡ እየተንከባከቡኝ ከሁለት ወር በፊት ሴት ልጅ በሰላም የተገላገልኩት›› በማለት ሥልጠናዋን እንዳላቋረጠች ትናገራለች፡፡ ከእርሷ ጋር የነበሩ ሦስት ልጆች ግን ተመልሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደማንኛውም ሠራተኛ ተቀጥሬ ልጄን ይዤ መኖር እችላለሁ ብላ ታምናለች፡፡

ሰለሞን ፍፁም በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ ነዋሪ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሥራ አጥ ሆኖ እናትና አባቱ ጋር ይኖር ነበር፡፡ አሁንም ኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዴቨሎፕመንት አሶስዬሽን ሥራ አጥ ወጣቶችን ሲመዘግብ ተመዝግቦ አሁን በአዲስ ራዕይ ማሠልጠኛ አስተማሪ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

ሠልጣኞቹ የተማሩትን በተግባር ያውላሉ፡፡ ሲኦሲ ፈተና የተሰጣቸው ሲሆን፣ ብዙዎቹ ማለፋቸው ተገልጿል፡፡

የኢፌዴሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ፅጋቡ ፈትለ በአንድ ወቅት አገራችን የሥልጣኔ ማማ ላይ ደርሳ እንደነበር ዛሬ የሚታዩት ቅርሶቻችን ምልክት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ተንሸራተን እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችንን፣ በድህነት አንገታችንን መድፋታችንን ግልፅ ነበር፡፡ ዛር ግን ኢትዮጵያዊነት ኩራት መሆኑን ሕዝባችንና መንግሥታችን በሚሠሩት ሥራ እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡ እኛም አስታዋሽ ያሉ ዜጎችን ሕይወት የሚለውጡ ፕሮጀክቶች በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተግባራዊ እየሆኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለዚህ ሁሉ አንቀሳቃሹ ሰው ነውና በሰው ኃይል ልማቱም ማተኮር ያስፈለጋል፤›› ብለዋል፡፡ ለሠልጣኞቹ የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም የራሱን ኃላፊነት ከተወጣ በድህነት ጎዳና ላይ የሚወድቅ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በግቢው የነበረው ድባብ የተለየ ስሜት የሚፈጥር፣ የሰዎች አዕምሮ ሁሌም ለመልካም ነገር ዝግጁ መሆኑን የሚመሰክርም ነበር፡፡ በሌላ በኩል ቁጥራቸው ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ተማሪዎች ተፋፍገው መኖራቸውና ከአካባቢው የአየር ፀባይ የማይስማሙ ቆርቆሮ ቤቶች ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰዎች ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት፣ ለኅብረተሰቡ ሰላም፣ ለአገሪቱም ትልቅ እገዛ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ዕርምጃ ለብዙ ተቋማት ትምህርት የሚሆን ነው፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...