Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​‹ትንሽ እሳት ጫካ ታነድ ትንሽ ዕውቀት አገር ታፈርስ!›

ሰላም! ሰላም! አንዱ መጣና “ከሜሲና ከሮናልዶ ማን ይበልጣል?” ብሎ አፈጠጠብኝ። ማን ይበልጣል ልበለው? ማንን እንደሚያስበልጥ በምን አውቃለሁ? አሁን እስኪ ቁስ ከሰው በበለጠበት ዘመን ሰው ከሰው በለጠ አልበለጠ ምን ፋይዳ አለው? እያልኩ ተጨነቅኩ።  ካልነገርከኝ ብሎ ሰቅዞ ሲይዘኝ እንደ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ካልተሆነ በቀር ምርጫው ለተመራጩም ለተሸናፊውም እንዳልጠቀመ አስታውሼ “ይለፈኝ” አልኩት። ‹ስንቱን አሳለፍኩት?› አለ መሐሙድ አህመድ። ቆይ ግን እንዲህ በፍርኃት ዘለዓለም ዓለማችን አጣብቂኝ ምርጫ ውስጥ እየገባን በይለፈኝ የመምረጥ ዕድላችን የምናሳልፈው እስከመቼ ነው? ልብ አድርጉ፣ ከክርስቲያኖ ሮናልዶና ከሜሲ ማን ይበልጣል ዓይነቱን ምርጫ ማለቴ ነው። ደግሞ የተቆጠረ የፀደቀ ምርጫ አስታውሳችሁ ወደ ሌላ ነገር እንዳትገቡ አደራ። ታዲያላችሁ በስንተኛው ቀን ሙሰኛ አፀዳለሁ በሚል ቀዳሚ አጀንዳ አዲስ ፕሬዚዳንት በመረጠችው በናይጄሪያ በሜሲና በሮናልዶ ወዳጆች መሀል በተነሳ የእኔ ይበልጣል የእኔ ይበልጣል አተካራ ታናሹ ታላቁን ገደለው ሲባል ሰማሁ። የሚቀጥለው ፕሬዚዳንት ኳስ ደጋፊ አጠፋለሁ ብለው ብቻ ሲወዳደሩ እንዳንሰማ እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው!

 ዜናውን የሰማ ወዳጅ ዘመድ ‘እንኳን እግዜር አዳነህ’ ሊለኝ ቤቴ ድረስ መምጣት ጀመረ። ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት የሆኑ አንዳንድ የልማት ተባባሪ ምልምል ወጣቶችም ይኼ ዜና በኢትዮጵያ እንዳይዘገብ በገለልተኝነት የቀረበልኝም ምርጫ ማለፌን አድንቀው ሰርተፊኬት ሰጡኝ። ይኼ በሆነ በስንተኛ ቀኑ የጠያቂዎቼ ቁጥር እየተመናመነ ሲመጣ የተራቆተ ኪሴን ለመሙላት ከቤት ወጣሁ። ባሻዬም መንገድ ቢያገኙኝ “አደራ ልጄ አሁንም ጠንቀቅ እያልክ። ሰው እንሆነ የሚያስመርጥህንም የሚመርጠውንም አላውቅ ብሏል፤” ካሉኝ በኋላ፣ “ለመሆኑ ሜሲና ሮናልዶ አፍሪካውያን ናቸው?” ብለው ጠየቁኝ። አንዱ ደቡብ አሜሪካዊ አንዱ አውሮፓዊ እንደሆነ ስነግራቸው፣ “አይ አፍሪካ ምናለበት ዛሬ እንኳ የራሷን ሰዎች ሐሳብ፣ ዝናና ክብር አነፃፅራ ብትጋደል?” ብለውኝ ተጓዙ። አሁን ይኼን ጉድ ሜሲም ሮናልዶም ቢሰሙ ኳስ ማንከባለል እርግፍ አድርገው ትተው ገዳም አይገቡም ትላላችሁ? ለነገሩ ገዳም በሳምንት ያን  ያህል ደመወዝ አይቆርጥ!

መቼም እንደ መፍረድ ቀላል ነገር የለም። ‹ከበሮ…› ይላል ያገሬ ሰው። ‹በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር›። ድሮ ነበር እንጂ በከበሮ መደናገር ዛሬ በሰው እጅ ስናየው እያደናገረን ያለው ገንዘብ ብቻ ሆኗል። ‘ከየት? እንዴት? ትናንት የማኪያቶ እኔ እየከፈልኩለት?’ የሚያስብለን አንዳንዱ ‘ኦቨርናይት’ የሚያሳየው ለውጥ ይባላል እንዴ? ከበሮንማ ገንዘብ ይኑር እንጂ ከፍሎ ማስደለቅ ይቻላል። አይቻልም እንዴ? አስደላቂዎችን እዩ ከተጠራጠራችሁ። ጊዜው ተቀይሯሏ። ገንዘብ፣ ገንዘብ፣ ገንዘብ። ገንዘብ ካለ ጠፈር ላይ ‹ቫኬሽን› አለ። ዕድሜ ለገንዘብ። አሁን ይኼን ሁሉ ያመጣሁት መፍረድ ቀላል ነው ብዬ ነው አይደል? አዎ። ልብ ብላችሁ ስሙኝ ታዲያ። መቼም በፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ልባችሁን ከሚጠቧችሁ ‹ዳያስፖራም ሆኑ ላሜቦራ› ፖለቲከኞች የእኔ ይሻላችኋል። ለራስ አልቆርስ ብለን ዳቦው እያለቀ ጠኔ ገደለና!

እንግዲህ ለሰው ልጅ የውድቀቱ ሁሉ መነሻው ቁንፅል እውቀት ነው ይባላል። ደግሞም እውነት ነው። ባይሆን ኖሮ ምልክቶቹን አናይም ነበር። ከምልክቶቹም አንዳንዶቹ በአርሰናልና በማንችስተር ምክንያት ትዳር ማፍረስ፣ በሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ ፀብ ነፍስ ማጥፋት፣ አድለው የጨረሱትን ቤት መልሶ ለማን ነው ያስረከብኩት እያሉ ቆጠራ፣ የፌስቡክ ኮሜንቶች ስድብና ዛቻ፣ በመልሶ ማልማት የለማውን አፍርሶ መልሶ ማልማት፣ ወዘተ ብዙ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ታዲያ የጥፋቱ ጥፋት የሚብሰው ትንሽ ማወቃችን ሳያንሰን ከእኛ በላይ የለም ብለን አገር ይያዝልኝ ስንል መዋላችን ጭምር ነው። ለምሳሌ በቀደም፣ “ኧረ ይኼ ልክ አይደለም፤” ይለዋል አንድ ላብ አደር የአንድ ሀብታም ቅንጡ አውቶሞቢል ጎማ እየቀየረ። ቀያሪው እኮ ላብ አደሩ ነው። ያ አፈር አይንካኝ ባዩ ሀብታም ፌስቡክ ላይ ከዘጠና ሰዎች ጋር ቻት እያደረገ በመሀል በመሀል “ገልብጠው! . . .  የለም! . . .  አሁን ነው የምታስረው?” እያለ ጣልቃ ይገባል። እኔ ኮንዶሚኒየም ቤት ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ቆሜ እታዘባለሁ። ሥራዬ ብለው ከታዘቡ እኮ ስንት ያለቦታው የተቀመጠ ዕቃ ይታዘባሉ መሰልዎ!

አያለሁ ብያችኋለሁ። ጎማው ተገልብጦ ነው የታሰረው። ልጁ የሚያደርገው ጠፍቶት ከባለቤቱ አላውቅም ብሎ ዝም ብሎ ገጥሞታል። በዚያ ላይ ቡሎኖቹን በጣም አታጥብቅ ስለተባለ እንደነገሩ ሰካክቷቸዋል። ባለመኪናው ጎማው ገጥሞ ብቻ ሲያይ አሥር ብር ወርውሮለት ሊያሽከረክር ገባ። በዚህ ቅፅበት ሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ ሙሽራ እስኪመስል ሽቅርቅር ብሎ የለበሰ ጎልማሳ ጥጉን ይዞ ሽንቱን ይሸናል። አንድ መንገደኛ፣ “ምናለበት እንደ አለባበስህ አስተሳሰብህን ብታሳምረው?” ብሎት አለፈ። “አንተ አትሸናም? በመንፈስ ነው የምትኖረው?” ጎልማሳው እየተሳደበ ሳይጨርስ ያ ፊት ለፊቴ ቆሞ የነበረ መኪና በቅጡ ያልተገጠመውና ያልታሰረው ጎማ በሮ ሹፌሩ የሚያደርገው ጠፍቶት ሲደነባበር፣ መሪውን ወዳልሆነ አቅጣጫ አዞረውና ጎልማሳው ላይ ወጣ።

ዓይኔ እያየ፣ ዓይኔ እያየ፣ ጎልማሳው በዚያው አንቀላፋ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? የነገሮችን አነሳስ ሳይ ስለቆየሁ ደንግጬ ራሴ ሲዞር ለወሬ ከተሰበሰበው ሰው መሀል አንዱ በቦታው ላልነበረ ሰው ትዕይንቱን ሲያብራራ እሰማለሁ። “እንዲህ ሆኖ እንዲያ ስሆን አሽቀንጥሮ ቢጥለው አስፓልቱ አናቱን ተርትሮ ጣለው፤” ይላል። “እና ሞተ?” ይጠይቃል ሰሚው ደንግጦ። “እና ሊቀርለት ነው? ድብን ነዋ፤” አይለውም? ‘አንተ እንዴት እንደዚህ ይባላል?’ የሚለው ሰው ካለ ብዬ ስጠባበቅ ደንበኛዬ ደረሰና ተያይዘን ወደ ጉዳያችን ሄድን። ኋላ ለባሻዬ ነገሩን ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው አብራርቼ ሳጫውታቸው ያ በኩራትና በተበቃይ ድምፀት ሞቱን ያረዳ የነበረ መንገደኛ ገርሟቸው ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው? “አንበርብር ተፈራርተንና የሚጀምርልን አጥተን ነው እንጂ ያላበደ የለም ዘንድሮ፤” አሉኝ። ሁሉን እናውቃለን እያልን በሁሉ ነገር ከከሰርን ዘንዳ ድሮስ ሊቀርልን ኖሯል ባሻዬ!

ታዲያላችሁ ባሻዬ እንደ ቀልድ የተናገሯት ነገር እያደር ትከነክነኝ ጀመር። አብሬያቸው የምውላቸውን ሰዎች ባህሪና አነጋገር መታዘብ ጀመርኩ። “በተለምዶ እብደት የምንለው የአዕምሮ ሕመም በአገሬ ባህላዊ ማስታመሚያ መንገድ ስላለው እንጂ፣ ውጭ ቢሆን መንግሥት ዛሬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይሆን ይገነባ የነበረው የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ነበር፤” የሚለኝ ደግሞ የባሻዬ ልጅ ነው። እሱ ደግሞ የማይለው የለም። “እንዴት? ምንድነው ባህላዊ ሕክምናው ብዬ እጠይቃለሁ። “አለማመን ይባላል። እሱ እኮ ተቆጪ ነው። እሱ እኮ ተናዳጅ ነው። እሱ ሲናገር እንዳመጣለት ነው፣ ለዛሬ ለነገ አይልም። አብሾ አለበት። ሰይጣናም ናት። ምን የማንለው አለ? የአዕምሮ ሕመም በሽታ እንደሆነ አናውቀውም፣ ስለዚህ አናምነውም። ለዚህ እኮ ነው ሕግ መጣስ፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ወላ ወደፊት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ሙሉ ለሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ የሚያደርገውም ዋናው ችግር ይኼ ነው” ብሎ አስረዳኝ።

ካዳመጥኩት በኋላ ተሻለ ሲባል እያደር በጉልበት እንጂ በፀባይና በሐሳብ ብልጫ ተሠርቶ የማይኖርባት አገር እየሆነች የመጣችው አገሬ አሳዘነችኝ። “በነውር ጀምረን በነውር መቋጨት እስከ መቼ እንዲያጨነግፈን እንደምንፈቅድ አላውቅም፤” ብዬ ያሻሻጥኩት ኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ኮሚሽኔን ሊሰጠኝ ቢደውል አላነሳ አልኩ። እንደ ዝና እንደ መታወቂያ የደፋናቸው ባህሪያትና መለያዎች ከትዕግሥትና ከጥበበኝነት ይልቅ ለምን ጉልበት ተኮር ሆኑ? ማን እንደ እኛ ደመ ሞቃት? ማን እንደኛ አትንኩኝ ባይ? ማን እንደ እኛ የጀግና አገር? መሸሽ የማያውቅ የማይሸነፍና መሰል የብሔራዊ ስሜት መገለጫ ስሞች ዕውን ከአዋቂነት፣ ከአስተዋይነትና ከጥበበኝነት የፈለቁ ናቸው? ወይስ ከግትርነት? እያልኩ እንደ ባለዕዳ ስብከነከን ቆይቼ ወዲያው ረስቼው ገንዘቤን ልቀበል በረርኩ። ኋላ የቤት ኪራይ የምከፍለው ባጣ ዜብራ ላይ ስንከባለል ልገጭና ልሙት ታዲያ?! ዜብራ ላይ የሚሻገሩ ቀርፋፋ ተሻጋሪዎች ቤት አልባ ናቸው ሲባል ስለሰማሁ ነው ይቅርታ!

 በሉ እንበተን እስኪ። ከዚህ በላይ ተሰብስቦ ማሽሟጠጥ የአገር ልማት ማደናቀፍ ነው። እስኪ አንዳንዴ ሥራ ባንፈጥር ወሬ እየቀነስን ልማቱን እናግዝ? ልላችሁ ስል የባሻዬ ልጅ ደውሎ አቋረጠኝ። “ምንድነው?” ስለው፣ “ፈጥነህ ድረስ እኔና አንተ የምንመራው ስብሰባ አለ፤” አለኝ። ከራሴ በላይ አጥብቄ ስለማምነው ተነካክቶ አየነካካኝም እያልኩ እንዳለኝ ፈጥኜ ደረስኩ። ጉዳዩን ሲያስጨብጠኝ ‘የሠፈራችን ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ከሌላ ሠፈር ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ወደኋላ መቅረቱን’ አጫወተኝ። “እና እኔና አንተ ምን አገባን?” ስለው፣ “መንግሥት የሚናገረው ነገር ሁሉ የመንግሥት ንብረትና ራዕይ እየመሰለ ልማቱን ስለጎተተው በእናንተው አንደበት አበረታቱዋቸው፤” ተብሎ ነው አለኝ። እያቅማማሁ ሺሕ ወጣት ወዲያ፣ እኔና የባሻዬ ልጅ ወዲህ ሆነን ተቀመጥን። “ይኼ ሁሉ ወጣት ሥራ የለውም?” ብዬ ግሮሰሪ ያለሁ መስሎኝ ልቀደድ ስል ‘ኧረ እንዳታስበላኝ አንተ ሰውዬ’ በሚል ቁንጥጫ መዘለገኝ። እውነት እውነት እላችኋለው በልጅነቴም እንዲያ ያለ ቁንጥጫ አላጋጠመኝም። ታዲያ ይኼን እያየሁ የመናገርና የመፃፍ ሙሉ ነፃነቴ ተጨቆነ ብል ከባሻዬ ልጅ ልጀምር ነው ማለት ነው? ጉድ ነው!

በአጭሩ የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነታቸው ለምን ዝቅተኛ እንደሆነ ወጣቶቹ አስረዱ። አንዱ ተነስቶ፣ “የልብስ ስፌት መኪናን የፈለሰፈው ሰው የሞተው ታርዞ፣ በብርድና በቁር ኩርትም ብሎ ነው። እእ . . .  ራዲየም የተባለውን ጨረር በምርምር ያገኘችውና የኖቤል ተሸላሚ መሆን የቻለችው ሜርኩሪ የሞተችው ጨረሩ ባደረሰባት አደጋ ነው። ስለተመጣጠኝ ምግብና ለሰውነታችን ስለሚኖረው ዓይነተኛ ጥቅም ለመጀመርያ ግዜ በመጽሐፍ ያሳተመውም የምግብ ተመራማሪ ምሁር የሞተው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው። ታዲያ እኛ ይኼን ሁሉ እያወቅን በፈጠራ ላይ ጊዜ የማናጠፋው መኖር ስለምንሻ ነው” ብሎ ሲቀመጥ ገረመኝ። የገረመኝ የሰጣቸው ምሳሌዎች እውነት መሆን በባሻዬ ልጅ ሲረጋገጥ እንጂ በወጣቶቹ ድምዳሜ አልነበረም።

ወዲያው የባሻዬ ልጅ ‘በካውንተር አታክ’ ስለቶማስ ኤድሰን ጨለማ ፈሪነት፣ ስለኦሊቨር ራይት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አለማጠናቀቅ፣ ወዘተ ብዙ ምሳሌ ደርድሮ በማሱት ጉድጓድ ያልወደቁ ስመጥር ተመራማሪዎችን ዘርዝሮ አሳመናቸው። የአንተ ድርሻ ምንነበር? አላችሁኝ። አለማወቄን አውቄ ዝም ብሎ ማዳመጥ ነዋ። ዘንድሮ እኮ የበጠበጠን ያለ ዕውቀት ሲከፋ ደግሞ በቁንፅል ዕውቀት ትዳር ካላሳመርን፣ አገር ካልመራን፣ መኪና ካልነዳንና ሕዝብ ካላግተለተልን ባይነት ሆኗል። ከስብሰባው በኋላም እኔና የባሻዬ ልጅ ወደተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አምርተን የተሰበሰብነው በዚሁ ዙሪያ ነው። እስኪ እናንተም አውሩበት። ትንሽ እሳት ጫካ ታነድ እንዳይሆን፡፡ ትንሽ ዕውቀት አገር ታፈርስ እንዳይተረት እንወያይበት። መልካም ሰንበት!

    

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት